በምዕራብ ኦሮሚያ በታጠቁ ኃይሎች የተገደሉ ሰዎች ቁጥር 12 ፖሊሶችን ጨምሮ 41 መድረሱ ተገለፀ

የኦሮሚያ ኮሚሽነር አለማየሁ እጅጉ ኩምሳ
የምስሉ መግለጫ,

የኦሮሚያ ኮሚሽነር አለማየሁ እጅጉ ኩምሳ

በምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢ ያለውን አለመረጋጋት ተከትሎ 12 ፖሊሶችን ጨምሮ በአጠቃላይ 41 ግለሰቦች መገደላቸውን የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽነር አለማየሁ እጅጉ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቀዋል።

በዚህም መግለጫ ላይ የፀጥታ ኃይሎችንና ግለሰቦችን በድብቅ ሲያስገድሉ የነበሩት "አባ ቶርቤ" (ባለሳምንት) የተሰኘው ቡድን አባላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናግረዋል።

ኮሚሽነሩ በአካባቢው ግጭቶቹን በማነሳሳት ኦነግ ሸኔን የወነጀሉ ሲሆን፤ 12ቱ ፖሊሶችም የተገደሉት በኦነግ ሼኔ እንደሆነም ተናግረዋል። ከዚህም በተጨማሪ ኦነግ ሸኔን በገንዘብ የረዱ ሰዎችም ምርመራ እንደተጀመረም ኮሚሽነሩ አስረድተዋል።

ኮሚሽነሩ ጨምረውም የኦነግ መሪ የሆኑትን አቶ ዳውድ ኢብሳ በስም ጠቅሰው ከመንግሥት ጋር አብረው ለመስራት የሰላም ስምምነት የፈረሙ ቢሆንም በአንፃሩ ለሰላም እየሰሩ እንዳልሆነ ገልፀዋል።

በኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በመንቀሳቀስ የፀጥታ ኃይሎችንና ግለሰቦችን በድብቅ ሲያስገድሉ የነበሩት "አባ ቶርቤ" (ባለሳምንት) የተባለው ቡድን ተጠርጣሪዎቹ "አባ ቶርቤ" በሚል መጠሪያ በመደራጀት ሰላማዊ ዜጎችን፣ የመንግሥት ባለስልጣናት እና የፀጥታ ኃይሎችን ሲገድሉ እና ተጨማሪ ባለስልጣናትን ለመግደል ሲያሴሩ ተጠርጥረው እንደተያዙ ተገልጿል።

ኮሚሽነሩ በቁጥር ሁለት ሺህ ሰባ (2070) ኤኬ47 የጦር መሳሪያዎች በቄለም ወለጋና ምዕራብ ወለጋ ዞን ከሚገኙ ፖሊስ ጣቢያዎችና ከባንክ ሦስት ሚሊዮን ብር እንደተዘረፈ ገልፀዋል።