የሪፐብሊኩ ጠባቂ ሃይል መቋቋም ምን ያመለክታል?

የሪፐብሊኩ ጠባቂ ሃይል አባላት

የፎቶው ባለመብት, የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት

ህገመንግስቱንና ህገመንግስታዊ ስርዓቱን ሊሰነዘሩ ከሚችሉ ጥቃቶች እንዲጠብቅ የተቋቋመው የሪፐብሊኩ ጠባቂ ሃይል ምስረታ ይፋ ሆኗል።

እሁድ ታህሳስ 14 ቀን 2011 ዓ.ም የጥበቃ ሃይሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በተገኙበት ትርኢት አሳይቷል።

ይህ የሪፐብሊኩ ጠባቂ ሃይል ከፍተኛ ባለስልጣናትንና ቤተሰቦቻቸውን ከተለያዩ ጥቃቶች እንደሚጠብቅም ተገልጿል።

የዚህ አይነቱ የሪፐብሊክ ጠባቂ ሃይል በአፍሪካ የተለመደ እንዳልሆነ በደረግ የኤርትራ ገዥ የነበሩት ከዚያም ከስምንት በላይ የሚሆኑ የአፍሪካ አገራትን በፀጥታ ጉዳይ ያማከሩት ሻለቃ ዳዊት ወ/ጊዮርጊስ ይናገራሉ።

ሻለቃ ዳዊት ከ33 ዓመታት ስደት በኋላ ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱት ከጥቂት ቀናት በፊት ነው።

ቢሆንም ግን የዚህ አይነት ተቋማት በአንዳንድ አገራት መኖራቸውን ይገልፃሉ። በዚህ ረገድ በግርማዊ ቀዳማዊ ሃይለ ሥላሴ ክቡር ዘበኛ ተብሎ የተቋቋመውን ቡድን በቀዳሚነት ይጠቅሳሉ።

መደበኛ ሰራዊት ስራውን ሲሰራ ክቡር ዘበኛ ደግሞ የመንግስትንና የንጉሱን ደህንነት ይጠብቅ እንደነበር ፤ በተመሳሳይ በኢራን የገዥው ፓርቲንና መንግስትን የሚጠብቅ የሪፐብሊክ ጠባቂ ቡድን እንዳለ ይናገራሉ።

የኢራኑ የሪፐብሊክ ጠባቂ ሃይል ግን በብዙ ውጊያዎች ላይ እንደሚሰማራ ገልፀዋል።

የእንግሊዙን የንጉሳዊያን ጠባቂ ሃይልን በምሳሌነት ይጠቅሳሉ። እነዚህ የጥበቃ ሃይላት ዋንኛ ስራቸው መንግስትንና ባለስልጣናትን መጠበቅ ነው።

ትናንት ትርኢቱን ያሳየው የኢትዮጵያው የሪፐብሊክ ጠባቂ ቡድንም ከዚህ የተለየ ተልዕኮ እንደማይኖረው ነግረውናል።

በሌላ በኩል የአሜሪካ ፌደራል መንግሥት ሕግ አስከባሪ ኤጀንሲዎች መካከል ልዩ ኃይል የሆነው ሴክሬት ሰርቪስ ከሪፐብሊኩ ጠባቂ ኃይል ጋር ተመሳሳይ ተግባራት አለው። የአሜሪካው ሴክሬት ሰርቪስ ፕሬዝዳንቱን እና ቤተሰቦቻቸውን ብቻ ሳይሆን ምክትል ፕሬዚዳንት፣ የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዝዳንቶችን፣ ዕጩ ፕሬዝዳንቶችን እና ቤተሰቦቻቸውን እንዲሁም በአሜሪካ ጉብኝት የሚያደርጉ የሃገራት መሪዎች ደህንነትን ይጠብቃል።

የሪፐብሊኩ ጠባቂ ሃይል መቋቋም ምን ይጠቁማል?

ከለውጡ በፊት በዚሁ መንግስት ተቋቁሞ የነበረው የአጋዚ ጦር ከሞላ ጎደል መሰል ተልዕኮ ይወጣ እንደነበር ሻለቃ ዳዊት ይናገራሉ።

"አጋዚ ግን እነ መለስን እና ሌሎች የህዝባዊ ወያነ ሃርነት ትግራይ ባለስልጣናትን ነበር የሚጠብቀው" የሚሉት ሻለቃ ዳዊት፤ የአጋዚ አደረጃጀት ከአንድ የፖለቲካ አመለካከት ብቻ የሚቀዳ ፤ የተልኮ ትኩረቱም አንድ ወገን ላይ ብቻ ስለነበር እሱን ከማቆየት መሰል ጦር የማቋቋም ፍላጎት እንደመጣ ይገልፃሉ።

በአጠቃላይ በፌደራል ደረጃ የተቋቋመው ጦር ሃይል አመራሩ በአብዛኛው ከአንድ ወገን የመጣ በመሆኑ ይለወጥ ቢባል እንኳን ጊዜ ይወስዳል ፤ ከዚህ ባሻገርም ለውጡን ያለመቀበል ነገር መኖሩም ሌላ የማያስኬድ ነገር እንደሆነ ያስረዳሉ።

ስለዚህም በዚህ ሁኔታ ውስጥ ይህን የሪፐብሊክ ጠባቂ ሃይል ማቋቋም አስፈላጊና ተገቢ እንደሆነ ያምናሉ።

ውሳኔው በአጠቃላይ "ለመንግስትና ለባለስልጣናት የግል ጥበቃ ጦሩ እንደማያስተማምን" ማሳያ ሊሆን እንደሚችልም ምልከታቸውን አስቀምጠዋል።