እንግሊዝ-የገና እለት ወደ ሀገሩ እንዲመለስ የተገደደው ስደተኛ

ኦቲስ ቦላሙ

የፎቶው ባለመብት, HBTSR

ኦቲስ ቦላሙ ይባላል። የተወለደው ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ቢሆንም ከሀገሩ ተሰዶ እንግሊዝ ውስጥ ጥገኝነት ለመጠየቅ ተገዷል።

የኦቲስ ጓደኞች ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ውስጥ ለተቃዋሚዎች በመሰለል ስለተጠረጠረ ከባድ አደጋ እንደተጋረጠበት ሲነግሩት ነበር ወደ እንግሊዝ፣ ስዋንሲያ የተሰደደው።

ኦቲስ እንግሊዝ ውስጥ ጥገኝነት ቢጠይቅም፤ የገና በአል በሚከበርበት የዛሬው እለት ወደ ትውልድ ሀገሩ እንዲመለስ ይደረጋል የሚል ዜና መሰማቱን ተከትሎ መነጋገሪያ ሆኗል።

የኦቲስ የጥገኝነት ጥያቄ በስደተኞች ጉዳይ መርማሪዎች ሳይታይ በአውደ አመት ወደ ኮንጎ ለመመለስ መገደዱን በመቃወምም 3,000 ሰዎች ፊርማቸውን አኑረዋል።

በሀገሪቱ የስደተኞችን ጥያቄ የሚመረምረው አካል፤ ጉዳዩን ከተለያየ አቅጣጫ ተመልክቶ እየፈተሸ መሆኑን ተናግሯል። ሆኖም የተለያዩ ተቋሞች የስደተኛውን መመለስ እየተቃወሙ ነው።

'ሄይ ብሬኮን ኤንድ ታልጋርት ሳንክችወሪ ፎር ሬፍዩጂስ' የተባለ የስደተኞች ተቋም እንደሚለው፤ ኦቲስ እንደ አውሮፓውያኑ ታህሳስ 19 እለት ታግቶ የስደተኞችን ጉዳይ በሚመረምረው አካል ተጠርቷል።

በሌላ በኩል ቃል አቀባይ ማሪያ ዱጋን የኦቲስን ጉዳይ የሚከታተለው ግለሰብ የገና በአል እረፍት ላይ እንደሆነ ተናግረው፤ "ጉዳዩ የት እንደደረሰና ለምን ጥገኝነት አንደተከለከለ አላውቅም" ብለዋል።

የ'ሄይ ፌስቲቫል' ዳይሬክተር ፒተር ፍሎራንስ፤ የጥገኛነት ጥያቄው ሳይመረመር ወደ ትውልድ ሀገሩ የሚመለስበት አካሄድ ግልጽ አይደለም ብለዋል። በተለይም በበአል ወቅት ኦቲስ እንዲመለስ መደረጉ አሳዝኗቸዋል።

'ስታንድ አፕ ቱ ሬሲዝም ዌልስ' በተባለው ተቋም የሚሠሩት አሊስ ጋርድነር፤ ኦቲስ ወደ ሀገሩ ከተመለሰ ለአደጋ መጋለጡ አስግቷቸዋል። "የገና እለት ያለ ፈቃዱ ወደ ሀገሩ እንዲመለስ ይደገራል ተብሏል። ምግብ እየበላ አይደለም። አይተኛም። ድብርት ተጭኖታል።" ሲሉ ያለበትን ሁኔታ ገልጸዋል።

የስደተኞችን ጉዳይ የሚመለከተው ቢሮ ቃል አቀባይ፤ እንግሊዝ ጥበቃዋን ለሚሹ ስደተኞች መጠጊያ መሆኗን ተናግረዋል። በዚህ ተግባርም "የምንኮራበት ታሪክ አለን" ብለዋል።

ኦቲስ ወደ ሀገሩ እንዳይመለስ የፊርማ ማሰባሰብ የተጀመረው ባለፈው አርብ ነበር።