የዓመቱ የአፍሪካ አነጋጋሪ የኢንስታግራም ፖስቶች

በሪሀና ኢንስታግራም ገጽ ዝናን የተቀዳጁት ታዳጊዎች

የፎቶው ባለመብት, The Ikorodu Talented Kids

ኢንስታግራም ላይ አንድ ቪድዮ መልቀቅ ከመላው ዓለም ለመተዋወቅ አቋራጭ መንገድ ከሆነ ሰነባበተ። ግሩም ድምጽ ያላቸው ታዳጊዎች፣ ምርጥ ተወዛዋዥ ወጣቶች በኢንስታግራም አማካኝነት ዝናን ተቆናጥጠዋል። በአንድ ጽሁፍ ወይም በአንድ ፎቶ ዝነኛ የሆኑትንም ቤቱ ይቁጠራቸው።

ሊገባደድ ቀናት በቀሩት የአውሮፓውያኑ 2018 አፍሪካ ውስጥ አነጋጋሪ የነበሩ የኢንስታግራም ፖስቶች የሚከተሉት ናቸው።

1. የሪሀና ኢንስታግራም ገጽ ዝና ያቀዳጃቸው ታዳጊዎች

ድምጻዊቷ ሪሀና አራት ታዳጊ ናይጄሪያውያን ሲደንሱ የሚያሳይ ቪድዮ በኢንስታግራም ገጿ ያጋራችው በመጋቢት ወር ነበር። ቪድዮው ሦስት ሚሊዮን ወዳጆች ሲያገኝ፤ 'ታዳጊዎቹ እነማን ናቸው?' የሚል ጥያቄ የሚጠይቁ ተበራከቱ።

ታዳጊዎቹ 'ኢኮሮዱ ታለንትድ ኪድስ' ይባላሉ። ሌጎስ ውስጥ ዝቅተኛ ገቢ ካላቸው ቤተሰቦች የተወለዱ ታዳጊዎች ሲሆኑ፤ የሪሀና ፖስት ከብዙዎች ህሊና እንዳይረሱ አድርጓቸዋል።

2. የ 11 ዓመቷ ዲጄ

'ዲጄ ስዊች' የ 11 ዓመቷ ታዳጊ ኤሪካ ታንዶህ የመድረክ ስም ነው። በመላው ጋና እውቅ የሆነችው በወርሀ ሰኔ ነበር። ኢንስታግራም ላይ 140,000 ተከታዮች ያሏት ታዳጊ፤ ሥራዎቿን የምታስተዋውቀውም በኢንስታግራም ገጿ ነው።

ኤሪካ በጋና ታሪክ የዲጄዎች ውድድርን ያሸነፈች በእድሜ ትንሿ ልጅ ናት።

3. የኬንያው ፊልም በካንስ ፊልም ፌስቲቫል

በዋኑሪ ካዩ የተሰራው 'ራፊኪ' ፊልም ካንስ ፊልም ፌስቲቫል ላይ በመታየት ግንባር ቀደሙ ኬንያዊ ፊልም ሆኗል።

ፊልሙ 'የተመሳሳይ ጾታ የፍቅር ግንኙነትን ያስተዋውቃል' ተብሎ በኬንያ መንግሥት እገዳ ተጥሎበት ነበር። ፊልም ሰሪዋ ዋኑሪ ስለ ፊልሙ ኢንስታግራም ገጿ ላይ ስትጽፍ፤ ኬንያዊቷ የሆሊውድ ተዋናይት ሉፒታ ኒዮንጎ የ'እንኳን ደስ አለሽ' መልእክት በኢንስታግራም ገጿ አስተላልፋለች።

የኬንያ መንግሥት ፊልሙ ላይ የጣለው እገዳ ለአንድ ሳምንት አንስቶ፤ ፊልሙ የኦስካር እጩ ሲሆን ብዙዎች ደስታቸውን የገለጹትም በኢንስታግራም ነበር።

4. የናኦሚ ካምቤልና የቡሀሪ ጉዳይ

የፎቶው ባለመብት, Instagram

መጋቢት ላይ እንግሊዛዊቷ ሞዴል ናኦሚ ካምቤል የናይጄሪያው ፕሬዘዳንት ሙሀመዱ ቡሀሪ በግሏ ጥሪ እንዳደረጉላት ገልጻ ከፎቶ አባሪ ጋር በኢንስታግራም ገጿ ለጥፋለች።

ሆኖም የመንግሥት ቃል አቀባይ፤ በግል ጥሪ እንዳልተደረገላት ገልጸው ፖስት አደረጉ። ሞዴሏ ብዙም ሳትቆይ የፋሽን ትርኢት ለመታደም ሌጎስ መገኘቷን ገልጻ ፖስት ያደረገችውን አስተካከለች። ይህ ፖስት የማኅበራዊ ሚዲያ ተከታታዮችን ትኩረት የሳበ ነበር።

5. 'ሹዱ' ደቡብ አፍሪካዊቷ ዲጂታል ሞዴል

እንግሊዛዊው ፎቶ አንሺ ካሜሩን-ጄምስ 'ሹዱ' የተባለች ዲጂታል ሞዴል ያስተዋወቀው የካቲት ላይ ነበር። ሞዴሏ በቀጭን፣ ረዥም አፍሪካዊ ሴት ቅርጽ የተሰራች ስትሆን፤ ፎቶ አንሺው በሥራው ትችት ተከትሎታል።

'ሺዱ' በ20ዎቹ መጨረሻ ያለች ዲጂታል ሞዴል ስትሆን፤ ከ150,000 በላይ የኢንስታግራም ተከታዮች አሏት።

ፎቶ አንሺውን ያሞገሱት እንዳሉ ሁሉ፤ 'ሹዱ' እንደ ነጭ ወንድነቱ ለአፍሪካውያን ሴቶች ያለው የተዛባ አመለካከት ነጸብራቅ ናት ብለው የተቹም ነበሩ።

6. ስዊድናዊቷ ቱሪስትና ኬንያዊቷ ታዳጊ

የፎቶው ባለመብት, Instagram

ጆሳ ጆንሰን የተባለች ስዊድናዊት ቱሪስት በናይሮቢ የተጨናነቁ መንደሮች ያገኘቻትን ታዳጊ ፎቶ ኢንስታግራም ላይ ለጠፈች። ከፎቶው በበለጠ ብዙዎችን ያስቆጣው ከፎቶው ጋር አያይዛ የጻፈችው ነበር።

"ታዳጊዋ በህይወት ዘመኗ እጅግ የተደሰተችበት ቅጽበት እኔና ጓደኞቼን ስታገኝ ነው" ብላ ነበር። ታዳጊዋ ለወደፊት በእድሜ የሚበልጣት ሰው አግብታ በድህነት እንደምትማቅቅ፤ ባሏ ጥሏት ሲሄድ ልጇን ለማሳደግ ሴተኛ አዳሪ እንደምትሆንም ጽፋ ነበር።

በአጸያፊ ንግግሯና ዘረኛ አስተያየቷ ተተችታለች። ጽሁፏ በአጭር ጊዜ ከበርካቶች አሉታዊ ምላሽ አሰጥቷታል።

7. ደቡብ አፍሪካውያኑ ፖሊሶች

የደቡብ አፍሪካ የፖሊስ ሀላፊ ሳኔል ሶጺዝ ኢንስታግራም ላይ ፖስት በምታደርጋቸው ፎቶዎች ምክንያት ብዙ ተከታይ አላት። ከራሷ ፎቶ በተጨማሪ አንዲት የደርባን ኮንስታብል ፎቶዎችን ፖስት ስታደርግ ደግሞ አነጋጋሪነቷ ጨመረ።

ሶዌቶ ውስጥ ያለ አንድ ጋዜጣ 'ሁለት ቆንጆ ፖሊሶች' የሚል ጽሁፍ ሲያስነብብ የማኅበራዊ ሚዲያ መነጋገሪያ ሆኑ። የፖሊሷ ዝና በአጭር ጊዜ ናኝቶ፤ በሥራ ቦታዋ፣ መንገድ ላይም ሰዎች "እሷ ነች! እሷ ነች!" እያሉ ይነጋገሩም ጀመር።

8. የአምስት አመቷ ታዳጊ ፎቶ

ሀምሌ ላይ ናይጄሪያዊቷ ፎቶ አንሺ ሞፊ ባሙይዋ፤ በኢንስታግራም ገጿ ጄር የተባለች የአምስት ዓመት ታዳጊ ፎቶ ፖስት አደረገች። ብዙ ሺ አድናቂዎችም ጎረፉላት።

ልጅቷ 'የዓለም ቆንጆ' የሚል መጠሪያ ተሰጣት። ፎቶ አንሺዋ "በልጅነትና በታዳጊነት መካከል ያለውን ሽግግር ያሳየሁበት ሥራ ነው። ሁለቱም ዘመን የማይገድባቸው እንዲሆኑ እፈልጋለሁ" ስትል ስለ ፎቶው ተናግራለች።

የአምስት ዓመት ልጅን መዋዋቢያ ቀብቶ፣ ዊግ ቀጥሎ ፎቶ ማንሳት ተገቢ አይደለም ብለው ተቃውሞ ያሰሙ ነበሩ።

ሆኖም የልጅቷ እናት ለጄር እንዲሁም ለሁለት እህቶቿ ጆሚና ጆባ የኢንስታግራም ገጽ አውጥታለች። 'ዘ ጄ ስሪ ሲስተርስ' የተባለው ይህ ገጽ 108,000 ተከታዮች አሉት።