ሀውስ ኦፍ ካርድ ላይ ፍራንክ አንደርውድን ሆኖ የሚተውነው ኬቨን ስፔሲ በፆታዊ ትንኮሳ ክስ ተመሰረተበት

ኬቨን ስፔሲ

የፎቶው ባለመብት, YouTube / @KevinSpacey

ሀውስ ኦፍ ካርድስ የተሰኘው ተከታታይ ፊልም ላይ ፍራንክ አንደርውድ በሚል ገፀ ባህርይ የሚታወቀው ታዋቂው አሜሪካዊ ተዋናይ ኬቨን ስፔሲ ማሳቹሴትስ በሚገኝ መጠጥ ቤት ውስጥ የ17 ዓመት ልጅ ላይ ፆታዊ ትንኮሳ በማድረሱ ክስ ተመስርቶበታል።

ይህንን ፈፅሟል ተብሏል የተጠረጠረው ከሁለት ዓመታት በፊት ሲሆን ታህሳስ 29 ፍርድ ቤት እንደሚቀርብ ቢዘገብም ተዋናዩ በምላሹ ሰኞ ዕለት ምንም ስህተት እንዳልሰራ በመናገርም መልዕክቱን በተንቀሳቃሽ ምስል (ቪዲዮ) አስተላልፏል።

"ምንም ባላጠፋሁት ጉዳይ ዋጋ ልከፍል አይገባም። ያለ ማስረጃ እንዴት ታምናላችሁ። እውነታውን ሳያገናዝቡ ለፍርድ መቸኮል አይገባም" ብሏል።

ይህ 'ግልፅ ልሁን' የሚል መጠሪያ የተሰጠው ቪዲዮ የፆታዊ ትንኮሳ ውንጀላ ከቀረበበት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የታየበት ነው።

በቪዲዮው ላይ በሴረኛው ፍራንክ አንደርውድ የአነጋገር ዘዬን በመጠቀም " አንዳንዶች ሁሉንም ነገር ያምናሉ። እንድናዘዝም በጉጉት እየጠበቁ ነው" ብሏል።

ትንኮሳውን ይፋ ያደረገችው ጥቃቱ የደረሰባት ወላጅ እናት የቀድሞ የዜና አቅራቢ ሄዘር ኡንሩህ ስትሆን ጊዜውም ባለፈው አመት ነው።

በዛን ጊዜ አስራ ስምንት አመት ያልሞላውን ልጇን መጠጥ ከመግዛት በተጨማሪ እንደጎነታተለው በማሳወቅ ወንጅላዋለች።

በኔትፍሊክስ በሚተላለፈው ተከታታይ ፊልም ከስድስተኛው ክፍል ቀድሞ ከመገደሉ በፊት ፍራንክ አንደርውድ የተሰኘው ገፀባህርይ በሴረኛነቱ የሚታወቅ ሲሆን ጋዜጠኛንና ፖለቲከኛን ገድሏል።

የፎቶው ባለመብት, Netflix

ይህ ውንጀላ ከቀረበበት በኋላ አንቶኒ ራፕ የተሰኘው ተዋናይም በአውሮፓውያኑ 1986 ፆታዊ ትንኮሳን በማድረስ የወነጀለው ሲሆን ሌሎች ፆታዊ ትንኮሳዎችም ይፋ በመሆን ላይ ናቸው።

ተዋናዩ ምንም እንደማያስታውስ ቢናገርም እንደ ሌሎች ውንጀላዎች ፈፅሞ አልካደም ነገር ግን በይፋ ይቅርታ ጠይቋል።

ውዝግቡ የሙያ ህይወቱን የጎዳው ሲሆን 'ሀውስ ኦፍ ካርድስ'ን ጨምሮ 'መኒ ኢን ዘ ወርልድ' የተሰኘው ፊልምም ያለ እሱ ተዋናይነት እንደገና እንዲቀረፅ ተደርጓል።

እሱ የሚተውንበት ቢሊየነር ቦይስ ክለብ የተሰኘው ፊልም ነሀሴ ወር ላይ ሲኒማ ቤት በታየበት በመጀመሪያው ቀን 126 ዶላር ገቢ ብቻ በማስገባት የዝቅተኛ ገቢ ሬከርድ ሰብሯል።