ጣሊያን ውስጥ የሁለት ዓመት ሕፃኑ ሲገረዝ ህይወቱ አለፈ

የሕክምና ባለሙያ ግርዛት እንዴት እንደሚፈፀም በአሻንጉሊት ላይ ሲያሳይ

በጣሊያን ስደተኞች በሚኖሩበት አካባቢ ግርዘት የተፈፀመበት የሁለት ዓመት ህፃን በደም መፍሰስ ምክንያት ህይወቱን አጣ።

የዚህ ብላቴና መንትያ በተመሳሳይ ግርዘት የተፈፀመበት ሲሆን ባጋጠመው ከፍተኛ የደም መፍሰስ ሮም በሚገኝ ሆስፒታል ውስጥ ተኝቶ እየታከመ መሆኑ ተነግሯል።

እንደ ጣሊያን የወሬ ምንጮች ከሆነ የ66 ዓመት አዛውንት በነፍስ ማጥፋት ተከሰዋል።

በነፍስ ማጥፋት ተጠርጥረው የተያዙት ግለሰብ አሜሪካዊ ዜግነት ያላቸው ሊቢያዊ እንደሆኑ ማወቅ ተችሏል።

በምድረ ጣሊያን በየአመቱ 5ሺህ ግርዛቶች የሚፈፀሙ ሲሆን ቀላል የማይባል ቁጥር ያላቸው በህገወጥ ስፍራዎች ደህንነታቸው ባልተጠበቁ መሳሪያዎችና ባለሙያ ባልሆኑ ግለሰቦች የሚፈፀሙ መሆናቸውን በጤና ላእ የሚሰራ በጎ አድራጎት ድርጅት ይናገራል።

ሁለቱ ህፃናት ስማቸው ያልተገለፀ ሲሆን በ2017 በጣሊያን ከናይጄሪያዊ እናታቸው የተወለዱ ናቸው። ይህች ናይጄሪያዊ እናት 5 ልጆች ያላት ካቶሊክ ብትሆንም የናይጄሪያውያን ሙስሊሞችን ባሀል በጠበቀ መልኩ ለማስገረዝ ልጆቿን ወደዚያ መውሰዷ ተነግሯል።

በጣሊያን ለግርዛት የሚከፈለው ገንዘብ ከ60 ሺህ ብር በላይ ሲሆን ይህንን መክፈል የማይችሉ ዜጎች በህገወጥ ስፍራዎች በ1500 ብር ገደማ ልጆቻቸውን ያስገርዛሉ።

በአሁኑ ሰዓት በጣሊያን ግርዛት በህዝብ የጤና ተቋማት አይሰጥም።

ግርዛት ቀላል ቀዶ ህክምና ቢሆንም ሁሌም ግን ከስጋትና ከአደጋ ነፃ ነው ማለት እንደማይቻል የጤና ባለሙያዎች ይገልፃሉ።

በመላው አውሮፓ የወንድ ልጅ ግርዛት ህጋዊ ቢሆንም ክርክር ግን አያጣውም።