ቻይና ውስጥ ካናዳዊ እስረኛ መብራት ማጥፋት ተከለከለ

ማይክል ኮርቪርግ

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ማይክል ኮርቪርግ የተባለ የቀድሞ ካናዳዊ ዲፕሎማት ቻይና ውስጥ በቁጥጥር ስር መዋሉ ተሰምቷል። ምንጮች እንደሚሉት፤ ግለሰቡ ጠበቃ ማቆም የተከለከለ ሲሆን፤ ምሽት ላይ መብራት ማጥፋት አትችልም ተብሏል።

የ 'ኢንተርናሽናል ክራይሲስ ግሩፕ' (አይሲጂ) ሠራተኛ የሆነው ካናዳዊው፤ በቁጥጥር ስር የዋለው ብሔራዊ ደህንነትን አደጋ ላይ በመጣል ተጠርጥሮ ነበር።

ቻይና እስረኛው በሕግ መሰረት ማግኘት ካለበት ምንም አላጓደልኩም እያለች ነው። የአይሲጂ ቃል አቀባይ ካርሚን ለቦር ለቢቢሲ እንደገለጹት፤ እስረኛው ጠበቃ አላገኘም። እስሩም ፍትሐዊ አይደለም።

የቀድሞው የካናዳ ዲፕሎማት በሰሜን ምሥራቃዊ እስያ መሥራት ከጀመረ ዓመት ተቆጥሯል።

ምንጮች እንደሚሉት ግለሰቡ የታሰረው በውል በማይታወቅ ቦታ ሲሆን፤ ጠዋት ማታ በምርመራ ጥያቄ እየተጣደፈ ይገኛል። ምንጮች አክለውም፤ ምሽት ላይ ሲተኛ መብራት ማጥፋት ተከልክሏል ብለዋል።

የቻይና የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ቃል አቀባይ ሁዋ ቹንይንግ፤ የቀድሞው ዲፕሎማት በአግባቡ መያዙን ተናግረዋል።

የካናዳ አምባሳደርና ሁለት የካናዳ ዲፕሎማቶች እስረኛው ማይክል ኮርቪርግን መጎብኘት የቻሉት ያለፈው ታህሳስ 14 ለግማሽ ሰአት ብቻ ነበር።

ከማይክል ኮርቪርግ በተጨማሪ ማይክል ስፔቨር የተባለ ነጋዴም ቻይና ውስጥ የታሰረ ሲሆን፤ ካናዳ ሁለት ዜጎቿ በቻይና መታሰራቸው እንዳሳሰባትና በአፋጣኝ መለቀቅ እንዳለባቸውም ተናግራለች።

ካናዳ በያዝነው ወር መባቻ ላይ የሁዋዊን የገንዘብ ዝውውር ክፍል የሚመራ ቻይናዊ ማሰሯ ይታወሳል። እስሩ አሜሪካና ቻይና የገቡበትን የንግድ ሽኩቻ ተከትሎ፤ አሜሪካ ለካናዳ ያቀረበችውን ጥያቄ የተከተለ ነበር።

ቻይና፤ የሁለቱ ካናዳውያን እስር ከቻይናዊው የሁዋዌ ሠራተኛ እስር ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም ብትልም፤ ተንታኞች እንደሚሉት ቻይና ለካናዳ የመልስ ምት እየሰጠች ነው።