በሎተሪ ሚሊዮን ስዊስ ፍራንክ የደረሰው ግለሰብ በስህተት ነው ተባለ የሚሉና ሌሎች አጫጭር ዜናዎች

የሎተሪ እድል ቁጥር

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ኢትዮጵያ

• በመንግሥት እና በኦነግ መካከል ባለው ፍጥጫ ምክንያት በምዕራብ ኦሮሚያ ከተሞች ትምህርት ቤቶችን ጨምሮ የመንግሥትና የንግድ ተቋማት አገልግሎት እየሰጡ እንዳልሆነ እየተገለጸ ነው።

ያነጋገርናቸው የደምቢ ዶሎ ነዋሪዎች እንደነገሩን መንገዶች ባይዘጉም፤ ትላንትናና ዛሬ ከተማዋ ተቀዛቅዛ ውላለች።

ሊቢያ

• በሊቢያዋ ዋና ከተማ ትሪፖሊ በሃገሪቱ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ውስጥ በተሰነዘረ ጥቃት ሶስት ሰዎች ሞቱ።

ከሟቾቹ መካከል አንዱ ጥቃት አድራሹ ሲሆን፤ ጉዳዩ በምርመራ ላይ ነው ተብሏል።

ቫቲካን

• የካቶሊኩ ጳጳስ ፖፕ ፍራንሲስ በፈረንጆቹ የገና በአል መልእክታቸው ባደጉት ሃገራት ያሉ ሰዎች ቀለል ያለና መተሳሰብ የሞላበት ህይወት እንዲመሩ አሳስበዋል።

በየመንና በሶሪያ ያለው የርስ በርስ ጦርነትም እንዲያበቃ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

ሜክሲኮ

• በያዝነው ወር የሜክሲኮዋ ፑዌብላ ግዛት አስተዳዳሪ ሆነው የተመረጡት ማርታ አሎንሶና ባለቤታቸው በሄሊኮፕተር መከስከስ አደጋ ህይወታቸው አለፈ።

የአደጋው መንስኤ እየተጣራ ሲሆን፤ የሃገሪቱ ባለስልጣናት ግን ሄሊኮፕተሩ ብልሽት አጋጥሞት ሊሆን ይችላል እያሉ ነው።

ኢንዶኔዢያ

• ኢንዶኔዢያ ውስጥ እሳተ ገሞራ ባስከተለው ከፍተኛ የባህር ውሃ ግፊት ምክንያት የሟቾች ቁጥር 429 መድረሱ ተገለጸ።

እስካሁን 16 ሺ ሰዎች ከመኖሪያቸቀው ሲፈናቀሉ፤ 150 የሚሆኑት ደግሞ የገቡበት አልታወቀም ተብሏል።

ኮስታሪካ

• ሁለት የኮስታሪካ ዜግነት ኣላቸው አሳ አጥማጆች ከጠፉ ከ20 ቀናት በኋላ በጃማይካ የውሃ ክልል ውስጥ ተገኙ።

አሳ ለማጥመድ አነስተኛ ጀልባ ይዘው የወጡት አጥማጆች ድንገተኛ ዝናብና ንፋስ አቅጣጫቸውን እንዳሳታቸው ተገልጿል።

አፍጋኒስታን

• አፍጋኒስታን ውስጥ በሃገሪቱ የማህበራዊ ስራዎች ሚኒስትር መስሪያ ቤት ውስጥ በተፈጸመ ጥቃት 43 ሰዎች ህይወታቸው አለፈ።

25 ሰዎች ጉዳት የደረረሰባቸው ሲሆን፤ ጥቃቱን ያደረሱት ሶስት ታጣቂዎች ደግሞ ተገድለዋል ተብሏል።

ስዊዘርላንድ

• ስዊዘርላንድ ውስጥ በሚሊዯኞች የሚቆጠር የስዊዝ ፍራንክ በሎተሪ ያሸነፈው ሰው ደስታውን ሳይጨርስ በስህተት ነው ተብሏል።

የሎተሪ ድርጅቱ ሰውዬውን ይቅርታ የጠየቀ ሲሆን፤ በወቅቱ ባጋጠመ ችግር የተሳሳተ መረጃ መለቀቁን አምኗል።

እንግሊዝ

• በሰሜናዊ ለንደን አቅራቢያ አንድ ቦክሰኛን በስለት ወግተው የገደሉ ሁለት የ15 ዓመት ታዳጊዎች ክስ ተመሰረተባቸው።

ታዳጊዎቹ ከነብስ ማጥፋት ወንጀል በተጨማሪ የከባድ ዝርፊያ ክስም ተመስርቶባቸዋል።

እስራኤል

• እስራኤል በመጪው ሚያዚያ ወር አጠቃላይ ምርጫ እንደምታካሂድ ገዢው የፓርቲዎች ጥምረት አስታወቀ።

የሙስና ወንጀል ክስ የቀረበባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ ስ መወዳደራቸው ግን እስካሁን አልተወሰነም።