በአሜሪካ ድንበር ላይ ተይዞ የነበረው ጓቲማላዊው ስደተኛ ህፃን ሞተ

ስደተኞች የአሜሪካን ድንበር ሲያቋርጡ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በአሜሪካ ድንበር ላይ ተይዞ የነበረው የስምንት አመቱ ጓቲማላዊ ስደተኛ ህይወቱ ማለፉን የአሜሪካ ኢሚግሬሽን ባለስልጣናት አስታወቁ።

የቴክሳስ የምክር ቤት አባል የልጁ ስም ፌሊፔ አሎንዞ ጎሜዝ እንደሆነም ገልፀዋል።

ሰኞ ዕለት ህፃኑ ህመም ታይቶበት የነበረ ሲሆን፤ ከአባቱም ጋር ሆስፒታል ተወስደው ከፍተኛ ሙቀትና ጉንፋን ስለነበራቸው የህመም ማስታገሻ እንደተሰጣቸው ተገልጿል።

በዛኑ ቀን ወደ አመሻሹ አካባቢ ህፃኑ እያስመለሰው ስለነበር ለተጨማሪ ህክምና ሆስፒታል ተመልሶ ቢሄድም ከሰዓታት በኋላ እንደሞተ ተነግሯል።

የሜክሲኮና የአሜሪካን ድንበር ሊያቋርጡ ሲሉ ተይዘው ከነበሩ ህፃናት መካከል በዚህ ወር ብቻ ይህ ህፃን ሲሞት ሁለተኛው ነው።

ከዚህ ቀደምም ጃክሊን ካል የተባለች የሰባት አመት ህፃን ስደተኛ መሞቷ የሚታወስ ነው። ልጅቷም ከጓቲማላ የመጣች እንደሆነች ተዘግቧል።

የቴክሳስ ምክር ቤት አባል ጃኩይን ካስትሮ የህፃኑ ሞት ላይ ከፍተኛ ምርመራ ሊከፈት እንደሚገባ አስታውቀዋል።

"ስደተኞችም ሆነ ጥገኝነት ጠያቂዎች በአሜሪካ መንግሥት ጥላ ስር እስካሉ ድረስ የሚያስፈልጋቸውን ህክምና ልናሟላ ይገባል። እንደ ሰውም ክብር ልንሰጣቸው ይገባል" ብለዋል።

ባለስልጣኑ ጨምረውም አስተዳደሩ ስደተኞችን ከድንበር መመለሱ ቤተሰቦችንና ህፃናትን አደጋ ላይ እየጣለ ነው ብለዋል።

በሺዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች ከመካከለኛው አሜሪካ በመነሳት የአሜሪካ ድንበሮችን ያቋርጣሉ።

እነዚህ ስደተኞች ድህነትን፣ ግጭትንናና እንግልትን ሸሽተው ሲሆን ብዙዎቹም ከጓቲማላ፣ ሆንዱራስና ኤልሳልቫዶር ናቸው ተብሏል።

ከአሜሪካ ባለስልጣናት በኩል በሕገ ወጥ መንገድ የሚገባ ማንኛውም ሰው እስር እንደሚጠብቀው ቢያስጠነቅቁም አሁንም ብዙዎች የተሻለ ህይወት ፍለጋ ድንበሮችን ያቆራርጣሉ።

ጄክሊን ካል እንዴት ሞተች?

የፎቶው ባለመብት, Reuters

ጄክሊን ከአባቷ ጋር ከብዙ ስደተኞች ጋር በመሆን ድንበሩን አቋርጠው ለአሜሪካ ባለስልጣናት እጃቸውን ሰጡ።

ጄክሊን ከጥቂት ቀናት በኋላ ከፍተኛ ትኩሳት ያጋጠማት ሲሆን፤ ጉበቷ ሙሉ በሙሉ ከጥቅም ውጭ ሆኖ ከቀናት በኋላ ሞተች።

የሞቷን ዜና በመጀመሪያ የዘገበው ዋሽንግተን ፖስት በድንበር ላይ ያሉ ባለስልጣናትን አናግሮ እንደሰራው፤ በከፍተኛ ውሃ ጥምና ድንጋጤ ምክንያት ጉበቷ ሙሉ በሙሉ ከጥቅም ውጭ እንደሆነ ነው።

በተጨማሪም ለቀናት ያህል ምግብና ውሃም እንዳላገኘችም ጨምሮ ዘግቧል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ,

የጄክሊን ካል እናት በልጇ ቀብር ላይ

የጄክሊን አባት አሁንም በአሜሪካ ድንበር ላይ ያለ ሲሆን የመጨረሻ ውሳኔም እየጠበቀ ነው።

የህፃኗ ሬሳ ወደ ጓቲማላ የተመለሰ ሲሆን ቀብሯም በትናንትናው ዕለት ተፈፅሟል።