በ2018 ጎልተው የታዩት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ

ጠቅላይ ሚንስትሩ ወታደሮችን ፑሽ-አፕ ሲያሰሩ

የፎቶው ባለመብት, Walta TV

የምስሉ መግለጫ,

ጠቅላይ ሚንስትሩ ወታደሮችን ፑሽ-አፕ ሲያሰሩ

የቢቢሲ 'ሌተርስ ፍሮም አፍሪካ' የአፍሪካውያን ጸሐፍት መልእክት ማስተላለፊያ መድረክ ነው። በቅርቡ ከተነበቡ ጽሑፎች አንዱ የጋናዊቷ ጋዜጠኛ ኤልዛቤት ኦሄን ነው።

ጋዜጠኛዋ ሊገባደድ ቀናት የቀረውን የአውሮፓውያን 2018 ስትቃኝ በጉልህ የምታነሳው ኢትዮጵያን እንዲሁም መሪዋን ነው።

ጋዜጠኛዋ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ዓመቱን አይረሴ አድርገውታል ትላለች።

በዋነኛነት የምታነሳው ጠቅላይ ሚንስትሩ ወታደሮችን ፑሽ-አፕ ያሰሩበትን እለት ነው። ወታደሮች በጉልበት ወደ ቤተ መንግሥት ከገቡ መፈንቅለ መንግሥት ለማድረግ የሚሆንበት እድል ሰፊ ቢሆንም፤ ጠቅላይ ሚንስትሩ ሁኔታውን በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን ጠቁማ፤ "ጠቅላይ ሚንስትሩ ሥልጣን ከያዙ በኋላ ሊሆኑ ይችላሉ ተብለው የማይታሰቡ ነገሮችን አድርገዋል። ስለሳቸውም ሆነ ሥራቸውን ስለሚያከናውኑበት መንገድ ለመገመት አስቸጋሪ ነው" ብላለች።

ከኤርትራ ጋር እርቀ ሰላም ወርዷል

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ,

የኢትዮጵያና የኤርትራ እርቀ ሰላም ተለያይተው ለነበሩ ቤተሰቦች ብስራት ነበር

ኢትዮጵያ በአምባገነናዊ አስተዳደር ትችት ሲሰነዘርባት ቆይቷል። ከኤርትራ ጋር ለዓመታት መኳረፏም ያሳማታል። ጋዜጠኛዋ፤ ጠቅላይ ሚንስትሩ ሥልጣን በጨበጡ በወራት ዕድሜ ከኤርትራ ጋር እርቀ ሰላም መውረዱን፤ ከዓመቱ ጉልህ ክንውኖች አንዱ ትለዋለች።

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መነሳቱ፣ ብዙ የፖለቲካ እስረኞች መፈታታቸው፣ የፖለቲካ ስደተኞች ወደ ሀገር ቤት መመለሳቸው፣ እገዳ ተጥሎባቸው የነበሩ ድረ ገጾችና የቴለቭዥን ጣቢያዎች ነጻ መውጣታቸውም አይዘነጋም።

በኢትዮ-ኤርትራ እርቀ ሰላም፤ ተለያይተው የነበሩ ቤተሰቦች በአይነ ስጋ ለመተያየት በቅተዋል። የአውሮፕላንና የመኪና እንቅስቃሴ ወደነበረበት ተመልሷል። ስልክ መደዋለም ይቻላል።

ቶች በአመራር

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ,

የኢትዮጵያ ፕሬዘዳንት ሳሕለወርቅ ዘውዴ

ጠቅላይ ሚንስትሩ ከካቢኔ አባላቾቻቸው ግማሹን ሴቶች አድርገዋል። ሴት ፕሬዘዳንትም ተሹሟል። የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዘዳንት ወ/ሮ መአዛ አሸናፊን ጨምሮ ሌሎችም ሴቶችም ወደ አመራር የመጡበት ዓመት መሆኑን ጋዜጠኛዋ ታስረግጣለች።

ጋዜጠኛዋ ኤልዛቤት ኦሄን ስለ አመራር ለውጥ ስታነሳ ደቡብ አፍሪካንም ትጠቅሳለች።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ፕሬዘዳንት ጃኮብ ዙማ ሥልጣን እንዲለቁ ከተደረገ በኋላ ሲሪል ራማፎሳ ወደ አስተዳደር መጥተዋል። የሀገሪቱ ራስ ምታት የሆነወን ሙስና ይዋጋሉ ተብሎም ተስፋ ተጥሎባቸዋል።

ጋዜጠኛዋ አዲሶቹን የደቡብ አፍሪካና የኢትዮጵያ መሪዎች ስታነጻጽር "ራማፎሳ ሥራቸውን በፑሽ-አፕ ባይሆንም በዱብ ዱብ ጀምረዋል" በማለት ነው።

ዓመቱ በአፍሪካ ምን ይመስል ነበር?

የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ አፍሪካን የሚያንጓጥጥ ዘረኛ ቃል ከአፋቸው መውጣቱን ተከትሎ ተቺዎቻቸው በእጥፍ ጨምረዋል። ባለቤታቸው ሜላኒያ ትራምፕ ደግሞ ጋና፣ ማላዊ፣ ግብጽና ኬንያን መጎብኘታቸው ይታወሳል።

ጋዜጠኛዋ ትራምፕ ለስደተኞች ያላቸውን የተዛባ ምልከታ፤ ፈረንሳይ ከሚኖረው ማሊያዊ ስደተኛ ማማዶ ጋሳማ ስኬት ጋር ታነጻጽረዋለች።

ጨቅላ ህጻንን ከፎቅ ከመውደቅ የታደገው ስደተኛ፤ ከፈረንሳዩ ፕሬዘዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የክብር ዜግነት ማግኘቱ ይታወሳል። ስደተኞች በበጎ እንዲታዩ ያስቻለ የዓመቱ ክስተት ነበር።

በሌላ በኩል ዩጋንዳዊው ሙዚቀኛና የሕዝብ እንደራሴ በዓመቱ ጎልተው ከወጡ ግለሰቦች መካከል ይጠቀሳል።

ሀገር በመክዳት ተከሶ ታስሮ የነበረው፤ ቦቢ ዋይን የዩጋንዳን መንግሥት በመተቸት ይታወቃል። በእስር ላይ ሳለ ከደረሰበት እንግልት ካገገመ በኋላ በአንድ መድረክ ማቀንቀኑንም ይታወሳል።

ኮንጓዊው ዶክተር ዴኒስ ሙክዌጌ የኖቤል የሰላም ተሸላሚ የሆኑት በዚሁ በ2018 ነበር። በተለይም ለተደፈሩ ሴቶች በሚሰጡት ህክምና ዶክተሩ ተመስግነዋል።

የፎቶው ባለመብት, EPA

የላይቤሪያው ፕሬዘዳንት ጆርጅ ዊሀ የቀድሞ አሰልጣኛቸው አርሰን ቬንገርን ወደ ትውልድ ሀገራቸው መጋበዛቸውን ጋዜጠኛዋ በጽሁፏ አካታለች።

"ቬንገር የዊሀን የእግር ኳስ ህይወት ስኬታማ በማድረጋቸው የላይቤሪያ ትልቅ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል"

ኔልሰን ማንዴላ በህይወት ቢኖሩ ዘንድሮ 100ኛ ዓመታቸውን ያከብሩ ነበር። ልደታቸው ታስቦ በዋለበት እለት የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዘዳንት ባራክ ኦባማ ወደ ደቡብ አፍሪካ ማቅናታቸው ይታወሳል።

በጸረ አፓርታይድ ትግሉ የሚታወቀው ታዋቂው ጃዝ ሙዚቀኛ ሂዊ ማሳኬላ እንዲሁም ዊኒ ማንዴላም ከዚህ ዓለም በሞት የተለዩበት ዓመት ነው።

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ,

የኮፊ አናን የቀብር ስርዐት

በ2018 የቀድሞው የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊና ዲፕሎማት ኮፊ አናን በ80ኛው አመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት ተለይተዋል።

የቀብር ስነ ስርዐታቸው በትውልድ ሀገራቸው ጋና ውስጥ ተከናውኗል

"የቻይናና አፍሪካ ፍቅር እንደቀጠለ ነው" ትላለች ጋዜጠኛ ኤልዛቤት ኦሄን። ቤዢንግ ውስጥ በተካሄደ ኮንፈረንስ ላይ የቻይናው ፕሬዘዳንት ዢ ዢፒንግ ለአፍሪካ 60 ቢሊዮን ዶላር ለመለገስ ቃል መግባታቸውንም ታጣቅሳለች።