አርበኞች ግንቦት 7 ለሰላምና ለህግ የበላይነት እሰራለሁ አለ

አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ

የአርበኞች ግንቦት 7 ንቅናቄ ዛሬ ረቡዕ አዲስ አበባ በሚገኘው ፅሕፈት ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ፤ መሳሪያ ታጥቀው ይንቀሳቀሱ የነበሩ አባላቱ ወደ ካምፕ እንዲገቡ ትዕዛዝ ከሰጠበት ጊዜ አንስቶ ከምንም ዓይነት ግጭት ጋር በተገናኘ ስሜ ተነስቶ አያውቅም ብሏል።

የንቅናቄው ዋና ጸሐፊ አቶ አንዳርጋቸው ፅጌ አርበኞች ግንቦት ሰባት ኤርትራ ውስጥ የነበሩት 300 ያህል ታጣቂዎች ሙሉ ትጥቃቸውን ፈትተው ጎንደርና ወረታ አካባቢ በሚገኝ ካምፕ ውስጥ በመንግሥት ድጋፍ እንደገቡ ገልፀው፤ የተወሰኑት ወደ ቤተሰቦቻቸው መቀላቀላቸውን አክለው ተናግረዋል።

ንቅናቄው ኤርትራ ውስጥ ከነበሩት ታጣቂዎች በዘለለ አገር ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች ተበታትነው ሲንቀሳቀሱ የነበሩ 550 ያህል አባላቱን ወደ ካምፕ ለማስገባት ጥረት ላይ መሆናቸውንም አቶ አንዳርጋቸው ተናግረዋል።

ንቅናቄያቸው ተገፍቶ ወደትጥቅ ትግል ገብቶ እንደነበር አፅንዖት ሰጥተው የተናገሩት አቶ አንዳርጋቸው በአመፅ ላይ የተመሰረቱ ትግሎች ዘላቂ ሰላማዊ እና ዲሞክራሲያዊ ለውጦች ያስገኙባቸው አጋጣሚዎች በዓለም ላይ በጣም ጥቂት መሆናቸው ሲያሳስበን ቆይቷል ብለዋል።

የፖለቲካ ቡድኖች ሰላማዊ እና ህጋዊ በሆነ መንገድ እንዲቀንሳቀሱ ስልጣን ላይ ያለው መንግሥት ሁኔታዎችን በተወሰነ ደረጃ ቢያመቻችም ሂደቱ ባለመጠናቀቁ ታጋሽነትን እንዲያሳዩ አቶ አንዳርጋቸው አሳስበዋል።

የፖለቲካ ቡድን አመራሮች በግልፅ እና በማያሻማ ቋንቋ አባሎቻቸው ከአመፅ እንዲርቁ ማሳሰብ አለባቸውም ሲሉ ተናግረዋል።

ጨምረውም "አመፅን እያጣቀሱ መሄድን የማይፈቅድ ስስ ሁኔታ ላይ እንገኛለን" ብለዋል ዋና ጸሐፊው።

በሻሸመኔ አካባቢ ተፈፀመ ተብሎ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ እየተዘዋወረ የሚገኘውን እና ወጣቶች የዕድሜ ባለፀጋዎችን ሲያጠቁ የሚያሳየውን ቪዲዮ በተመለከተ ለቀረበ ጥያቄ ሌላኛው የፓርቲው ከፍተኛ አመራር አቶ ቸኮል በሰጡት ምላሽ ጥቃቱ የተፈፀመባቸው ግለሰቦች የንቅናቄው አባላት መሆን ያለመሆናቸውን በማጣራትና ጉዳዩንም በመከታተል ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በልዩ ልዩ አካባቢዎች ንቅናቄው እየገጠመው ያለ ችግር መኖር ያለመኖሩን በተመለከተ ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ አንዳርጋቸው፤ በየትኛውም አካባቢ ተንቀሳቅሶ የመስራት መብታቸውን ለማስከበር እንደሚታገሉ ተናግረዋል።

"ሰላም ማስከበር የመንግሥት ኃላፊነት ቢሆንም፤ የመንግሥት ኃላፊነት ብቻ ግን አይደለም። የፖለቲካ ቡድኖች የመንግሥትን ሰላም የማስከበር ኃላፊነት የሚያዳክም ሥራ ከመስራት በመቆጠብ ለውጡን የጀመሩትን የመንግሥት አካላት መደገፍ ያሻል" ሲሉ ገልፀዋል አቶ አንዳርጋቸው።

አክለውም "ህገ መንግሥቱ የግለሰብ መብትን ሳያስቀድም የብሔር፣ ብሔረሰብ እና ሕዝቦችን መብት ያሰከብራል ብለን ባናምንም የመደራጀት እና የፖለቲካ እንቅስቃሴ የማከናወን መብትን የሚነፍግ ባለመሆኑ በዚህ ረገድ ችግር አይፍጥርብንም" ብለዋል።

በተጨማሪም የፍትህ ሥርዓቱንና ሌሎች ተቋማትን በአንድ ጀምበር ፍፁም ማድረግ ባይቻልም ተስፋ ሰጭ እርምጃዎች መስተዋላቸው ግን እሙን ነው እንደአቶ አንዳርጋቸው ገለፃ።

የፌዴራል መንግሥትን የሚቆጣጠሩት አካላት ልዩ ልዩ ተቋማትን ነፃ እና ገለልተኛ ለማድረግ ሥራ እየከወኑ ቢሆንም ወደ ክልል እና ክልሎች ወደሚያስተዳድሯቸው ወረዳዎች ሲወረድ ግን ወገንተኛነት እና ብሔርተኝነት ገንኖ ይታያል ብለዋል።

ክልሎቹ ወገንተኝነት የሚታይባቸው እና በዚያው አካባቢ የተቋቋሙ ሚሊሺያዎች፣ ልዩ ኃይሎች፣ ፖሊሶች፣ የደህንነት ኃይሎች ያሏቸው መሆኑ ለምርጫ መተግበር የሚያስፈልገውን ነፃ ሜዳ በመፍጠር ረገድ ደንቃራ ሊፈጠር እንደሚችል አቶ አንዳርጋቸው ጠቁመዋል።