የዛላምበሳ ድንበር ከፌደራል መንግሥት ፍቃድ ላልያዙ ተጓዦች ተከለከለ

የፎቶው ባለመብት, Yonas Fisehaye
በዛላምበሳ መስከረም ወር ላይ የነበረው አዲስ አመት አከባበር
ባለፈው የመስከረም ወር የተከፈተው የዛላምበሳ ድንበር ባልታወቀ ምክንያት ከፌደራል መንግሥት ፍቃድ ለሌላቸው ተጓዦች መከልከሉን የጉሎመኸዳ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ ገብረህይወት ገብረየሱስ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ድንበር በኩል "ከፌደራል መንግሥት ፈቃድ መያዝ አለባችሁ" የሚል ምላሽ እንተደተሰጣቸውና ከኤርትራ በኩል ደግሞ የይለፍ ወረቀት እየተዘጋጀ መሆኑን" ቢቢሲ ያናገራቸው ነዋሪዎች ገልፀዋል።
የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚናገሩት ይህ መመሪያ ከመውጣቱ በፊት ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ወደ ኤርትራ የሚመላለሱ መንገደኞች ያለችግር ገብተው መውጣት ይፈቀድላቸው ነበር።
በአሁኑ ወቅት ግን ያለ ይለፍ ወረቀት ከሁለቱም በኩል መንቀሳቀስ አይችልም።
በተጨማሪም በኤርትራ በኩልም ድንበር ጥበቃውን እንዲያጠናክሩ በድንበር ጥበቃ ላይ ለተሰማሩ ከላይ መመሪያ እንደተሰጣቸውም ምንጮች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በዚህ ጉዳይ ከኤርትራ መንግሥት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም።
ዛሬ ደግሞ በኢትዮጵያና ኤርትራ ድንበር ከራማ ወደ መረብ የሚወስደው የራማ-ክሳድ ዒቃ መተላለፊያ መዘጋቱን የመረብ ለኸ ወረዳ አስተዳደር አቶ ፅጌ ተስፋይ ለቢቢሲ ገልፀዋል።
ማለፍ የሚችሉት ከፌደራል መንግስት የይለፍ ወረቀት ያላቸው ሰዎች ብቻ እንደሆኑ ተገልጿል።