የእርቀ-ሰላም እና ይቅርታ ኮሚሽን ከደቡብ አፍሪካ እስከ ኢትዮጵያ

እርቀ-ሰላም እና ይቅርታ፡ ከደቡብ አፍሪቃ እስከ ኢትዮጵያ

የፎቶው ባለመብት, Stefano Montesi - Corbis

የእርቀ ሰላም እና ይቅርታ ጉዳይ የአትዮጵያን በር ካንኳኳ ወራት ተቆጠሩ፤ ሕዝብን በይፋ ይቅርታ በመጠየቅ በኩል ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ የመሪነቱን ሥፍራ ይወስዳሉ።

ምንም እንኳ የተወሰኑ የምክር ቤቱ አባላት ሕዝብ ከሕዝብ ስላልተጣላ የኮሚሽኑ መቋቋምም አስፈላጊ አይደለም በማለት ቢከራከሩም፤ ታኅሳስ 16 ቀን 2011 ዓ.ም የሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት የብሔራዊ ዕርቀ ሰላም ኮሚሽን ያቋቋመው።

በተለያዩ ፖለቲካዊና አስተዳደራዊ በደሎች ሕዝብ ተከፍቷልና፤ እውነተኛ ይቅርታ በመጠያየቅና የተበደሉ ወገኖችን ሕመም በመጋራትና በማከም የቁርሾ ታሪክን ተዘግቶ ወደፊት ለመራመድ ከፍተኛ ፋይዳ ይኖረዋል ሲሉ ለኮሚሽኑ መመስረት አስፈላጊነት የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ተስፋዬ ዳባ ይከራከራሉ።

ኮሚሽኑ በደል የደረሰባቸው ሰዎች በሚያቀርቧቸው ቅሬታዎች ላይ በመነሳት ሥራውን እንደሚያከናውን ተሰምቷል።

ወጣም ወረደ ኢትዮጵያ ከሌሎች ሃገራት ተሞክሮ መማር እንዳለበት እሙን ነው። እርቀ-ሰላሙ እና ይቅርታው ለይስሙላ አለመሁኑን ማስጠበቅ ደግሞ ፈተናዋ ይሆናል።

ይህን መሰሉን የእርቅና የይቅርታ ኮሚሽን በማቋቋም ሌሎች የአፍሪካ ሃገራትም በተለያዩ ጊዜያት የተፈጸሙ በደሎች እልባት እንዲያገኙ አድርገዋል።

ደቡብ አፍሪካ

የዛሬ 32 ዓመት ገደማ ነበር ደቡብ አፍሪካ የሃቅ እና የእርቀ ሰላም ኮሚሽን ያቋቋመችው።

በጊዜው ሃገሪቱ ከአፓርታይድ አገዛዝ ገና መላቀቋ ነበርና ያለፈውን ለመርሳት እና ወደፊት ለመጓዝ በሚል ነበር የኔልሰን ማንዴላ መንግሥት ኮሚሽኑ እንዲቋቋም የወሰነው።

ለዓመታት ከዘለቀ ዘርን መሠረት ካደረግ የግፍ አገዛዝ በኋላ እንዴት ተኩኖ ነው በጋራ በሰላም ወደመኖር የሚመጣው? ደቡብ አፍሪካ የተጋፈጠችው ትልቅ ፈተና ነበር።

የደቡብ አፍሪካ የሃቅ እና እርቀ ሰላም ኮሚሽን ሥራው ቀላል አልነበረም፤ ሥራው የዘር ፖለቲካ ክፉኛ የተጎዳችን ሃገር ማከም ነበርና።

ዳኛ ሲሲ ካምፔፔ የእርቀ ሰላም ኮሚሽኑ አባል ነበሩ። ዳኛዋ የይቅርታ ኮሚቴ ተብሎ የተቋቋመው ብሔራዊ ጥምረት አባልም እንደነበሩ ያዋሳሉ።

የእርቀ ሰላም አባላት ኮሚቴው በአፓርታይድ ዘመን ደቡብ አፍሪካዊያን ላይ ግፍ ፈፅመዋል የተባሉ ሰዎችን የመመርመር ግዴታ አለባቸው። ነገር ግን ጥፋት ፈፅሟል የተባለው ሰው ጥፋቱን በውዴታ ካላመነ በቀር ፍርድ አይበየንበትም።

ለደቡብ አፍሪካዊያን ትልቁ ፈተና የነበረው የይቅርታ ጉዳይ እንደነበር ዳኛ ሲሲ ይናገራሉ። «እንዴት የሰው ልጅ ላይ አሰቃቂ ግፍ የፈፀመ ግለሰብ ይቅርታ ይደርግለታል? የሚለው ትልቁ ፈተና ነበር» ይላሉ።

በደቡብ አፍሪካው የእርቀ ሰላም ሂደት ውስጥ ትልቅ ሚና እንደተጫወቱ የሚነገርላቸው አርክቢሾፕ ዴዝሞን ቱቱ ናቸው።

በእርሳቸው መሪነት ግቡን ከሞላ ጎደል እንደመታ የሚነገርለት የሃቅ እና እርቀ ሰላም ኮሚሽን ዋነኛ ተግባሩ በሕዝቦች መካከል ሰላም ማውረድ ነበር።

የፎቶው ባለመብት, Fitsum Arega/twitter

ኡጋንዳ

በኢትዮጵያ ግርጌ ከኬንያ ጋር የምትዋሰነው ኡጋንዳም የተመሳሳይ ዕጣ ፈንታ ተቋዳሽ ነበረች።

ለዓመታት የዘለቀው በመንግሥት እና 'ሎርድስ ሬዚዝስታንስ አርሚ' በተሰኘው የሽምቅ ተዋጊ ቡድን መካከል የነበረው የእርስ በርስ ጦርነት ሃገሪቱን በሰላም እጦት እንድትቆረቁዝ አድርጓት ነበር።

ጭካኔ በተሞላበት ድርጊቱ የሚታወቀው የሎርድስ ሬዚዝስታንስ አርሚ ሽምቅ ተዋጊ ቡድን አቾሊ የተባሉትን ሰሜናዊ ኡጋንዳዊያን ነፃ ለማውጣት የሚታገል ነበር።

ከዓመታት ትግል እና ያልተሳካ የሰላም ድርድር በኋላ ሽምቅ ተዋጊ ቡድኑ በመግንሥት ኃይል ተሸንፎ ሃገር ጥሎ መውጣቱ ተነገረ።

ኋላ ላይ ግን መንግሥት ያቋቋመውን እርቀ ሰላም ከሚቴ ተከትሎ የቡድኑ ተዋጊዎች ወደ ሃገራቸው መመለስ ያዙ፤ 32 ሺህ ገደማ ወታደሮች ከተሰደዱበት ሃገር ተመልሰው ከማሕበረሰቡ ጋር መዋሃድ ያዙ።

'ማቶ ኦፑት' የተሰኘ ባሕላዊ የይቅርታ እና እርቀ ሰላም ኮሚቴ ተቋዉሞ ማሕበረሰቡ ለተዋጊዎቹ ይቅርታ ቢያደርግም በጊዜው ተቀባይነት ግን አልነበራቸውም።

ጋምቢያ

ምዕራብ አፍሪቃዊቷ ሃገር ጋምቢያም ተመሳሳይ ታሪክ መዝገቧ ላይ የሰፈረባት ሃገር ናት።

የቀድሞው የሃገሪቱ ፕሬዝደንት ያህያ ጃሜህ ሃገር ጥለው ቢጠፉም ለሁለት አሥርት ዓመታት ጥለውት ያለፉት አሻራ ግን በቀላሉ የሚፋቅ አይመስልም።

አዲሱ ፕሬዝደንት አዳማ ባሮው የሃቅ፣ የእርቀ-ሰላም እና መልሶ መቋቋም ኮሚሽን ያሻናል ብለው ያቋቋሙት በያዝነው ዓመት ነው፤ "ብሔራዊ ቁስላችን እንዲሽር" በማለት።

ኮሚሽኑ በቀድሞው ፕሬዝደንት ዘመን ተፈፅመዋል የተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን መመርመር እና ተገቢውን ብይን የመስጠት ኃላፊነት ተሰጥቶታል።

ጋምቢያዊው የቢቢሲ ጋዜጠኛ በቀድሞው ፕሬዝደንት አገዛዝ ዘመን 'ፍሪደም' ከተሰኘው እና መንግሥት በጥላቻ ከሚያየው ጋዜጣ ጋር ስሙ ተያይዞ ለእሥር እና ስቃይ ተዳርጓል፤ ሃገሩን ጥሎ ተሰዷል።

«እስከዛሬ ድረስ በብሔራዊ የምርመራ ኤጀንሲ መሥሪያ ቤት በኩል ማላፍ አልችልም» ይላል፤ ስቃይ የቀመሰበት ሥፍራ ነውና።

አሁን ሁሉም ያለፈ ይመስላል፤ የአዳማ ባሮው መንግሥትም የቀድሞውን መሪ ሃጥያት ለማሰረይ ደፋ ቀና እያለ ይገኛል።

ከላይ የተጠቀሱት ሃገራት ብቻ ሳይሆኑ በርካታ የአፍሪካ ሃገራት የእርቀ-ሰላም እና ይቅርታ ኮሚሽን ማቋቋም ግድ ብሏቸዋል።

ሩዋንዳ

ስለእርስ በርስ ጦርነት ሲነሳ እንደምሳሌ የምትጠቀሰው ምስራቅ አፍሪካዊቷ ሃገር ሩዋንዳ 800 ሺህ ዜጎቿን ያጣችው የዛሬ 35 ዓመት ገደማ ነው።

'ጋቻቻ' የተሰኘው እና በሩዋንዳው ዘር እልቂት ወቅት ጥፋት ፈፅመዋል በተባሉ ሰዎች ላይ ፍርድ እንዲበይን የሚተጋው አካል ሁለት ሚሊየን ያክል ሰዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ አድርጓል።

ነገር ግን የሩዋንዳ መንግሥት እርቀ ሰላም እና ይቅርታን በሕዝቡ ዘንድ ከማስረፅ አንፃር ተገቢውን ሥራ አልሠራም ተብሎ በተደጋጋሚ ይተቻል።

ሩዋንዳ ውስጥ አሁንም ድረስ ስለዘር ማውራት ያስነውራል፤ ስለ እልቂቱ ማውሳት ያስወቅሳል። ሬድዮ ጣብያዎች የእርስ በርስ ጦርነቱን አንስተው እንዲነጋገሩበት አይበረታቱም፤ ቴሌቪዥኖች ስለጉዳዩ አያወጉም።

የሩዋንዳ ጎረቤት ሃገር የሆነችው ቡሩንዲ ግን በእርቀ ሰላም ጉዳይ መልካም ምሳሌ ሆና ትነሳለች፤ ምንም እንኳ በእርስ በርስ ጦርነት 300 ሺህ ያህል ዜጎቿን ካጣች ዘመናት ቢቆጠሩም።