"በአንድ ሀገር ውስጥ እስከ አፍንጫቸው የታጠቁ ክልሎች ሊኖሩ አይገባም" ፕሮፌ. ብርሃኑ ነጋ

ፕሮፌ. ብርሃኑ ነጋ

የአርበኞች ግንቦት 7 ሊቀመንበር የሆኑትና የምጣኔ ሀብት ባለሙያው ፕሮፌ. ብርሃኑ ነጋን በጽህፈት ቤታቸው አግኝተናቸው በወቅታዊ የሀገሪቱ ጉዳዮች ላይ ቆይታ አድርገናል።

ቢቢሲ አማርኛ፡ አንዳርጋቸው ታፍኖ መወሰዱን ባወቅክባት ቅፅበት ምን ተሰማህ?

ፕሮፌ. ብርሃኑ ነጋ ፡ አንዳርጋቸው የተያዘ ጊዜ ኒው ዮርክ ነበርኩ። እንደተያዘ እዚያው የመን እያለ ነው የሰማሁት፤ በተያዘ በግማሽ ወይንም በአንድ ሰዓት አብረው ሲበሩ ከነበሩ ሰዎች ውስጥ ነው የሰማሁት። እዚያ ያሉ እኛን የሚያውቁ ሰዎች እንደዚህ አይነት ነገር አለ ተከታተሉ ብለው የነገሩን ያኔ ነው።

በዚያ በኩል እንደሚሄድም አላውቅም ነበር፤ በሌላ በኩል እንደሚሄድ ነበር የማውቀው። ያው መጀመሪያ ላይ ትደነግጣለህ። የመጀመሪያ ሥራህ የሚሆነው ወደ ኢትዮጵያ እንዳይሄድ ወይንም ችግር እንዳይደርስበት ማድረግ የሚቻለውን ለማድረግ ለተለያዩ መንግሥታት፣ አቅም ላላቸው ሰዎች፣ መንገርና አንድ ነገር እንዲያደርጉ መሞከር ነበር።

ቢቢሲ አማርኛ፡ እርሱ እስር ቤት በነበረበት ወቅት እርሱን በተመለከተ ምን አይነት ስሜቶችን አስተናገድክ?

ፕሮፌ. ብርሃኑ ነጋ፡ ከአንዳርጋቸው ጋር ለረዥም ጊዜ ነው የምንተዋወቀው። ብዙ አውርተናል። ምን እንደሚፈልግ አውቃለሁ። እኔም ምን እንደምፈልግ ያውቃል። ሲታሰር የተወሰነ የድርጀቱን ሥራ ኃላፊነት እርሱ ስለነበር የወሰደው ኢትዮጵያ መምጣቱን ካወቅሁ ጊዜ ጀምሮ ለእኔ ግልፅ የሆነልኝ በምንም አይነት እንደማይፈቱት፣ እንደማይገድሉትም አውቅ ነበር።

ጥያቄው ያለው እንዴት ታግለን ቶሎ ይህንን ነገር እናሳጥራለን የሚል ነው። ከዛ በኋላ ብዙ ጊዜ አልፈጀብኝም ሥራዬን ሁሉ ትቼ እርሱ የጀመራቸውን ሥራዎች ወደ መቀጠል ነው የገባሁት። በእንዲህ አይነት የትግል ወቅት አንዳርጋቸው ሲታሰር ምን ይፈልጋል? ማንም ሰው ቢለኝ፤ የታገለለትን አላማ ከዳር እንድናደርስለት ነው እንጂ የሚፈልገው ሌላ ለግሉ እንዲህ አይነት ነገር ይደርስብኛል የሚል የስሜት ስብራት ውስጥ እንደማይገባ አውቅ ስለነበር፤ ያለኝን ጠቅላለ ጉልበቴን ያዋልኩት እንዴት አድርገን ይህንን ትግል በቶሎ ገፍተን እርሱንና በየቦታው የሚታሰሩትን ጓዶቻችንን ነፃ እናወጣለን ወደ ሚለው ነው።

ከዚያ ባሻገር ግን የታገልንለትን አላማ፣ ኢትዮጵያን ዲሞክራሲያዊ የማድረግ አላማ፣ ከዳር እንዴት እናደርሳለን የሚለው ነው፤ ከዚያ ውጪ ሌላ አልነበረም። ከመጀመሪያው አንድ ቀን ሁለት ቀን ውጪ ጠንካራ የሆነ የስሜት መዋዠቅ ውስጥ መግባት አይገባም ብዬ ነው ለራሴ የነገርኩት።

አሁን ሥራው ይህንን ነገር ከዳር ማድረስ ነው። በእንዲህ አይነት ትግል ውስጥ ችግሮች ይፈጠራሉ፤ ግን እያንዳንዱ ችግር ላይ ከፍተኛ የሆነ የስሜት መዋዠቅ ካስቀመጥክ ሥራ አትሰራም። ሁሉን ነገር ዘግቼ ይህንን ነገር እንዴት ከዳር እናደረሳለን የሚለው ላይ ነው ጊዜዬን ያጠፋሁት።

ቢቢሲ አማርኛ፡ አሁን ያለው ለውጥ የሚሾፈረው በኢህአዴግ መሆኑ ምን አይነት ስሜት ነው የሚፈጥረው?

ፕሮፌ. ብርሃኑ ነጋ- አንዱ ትልቁ ጥያቄ ኢህአዴግን የምናየው የድሮው ኢህአዴግና የአሁኑ ኢህአዴግ አንድ ነው፤ ወይንስ ቢያንስ ያንን ለውጥ ካመጡ ሰዎች በኋላ በመሰረታዊ መልኩ ለውጥ አድርጓል የሚለውን መመለስ አለብህ።

የትግል ለውጥ ስትራቴጂ ለውጥ ስናደርግ የወሰንነው ይህንን ለውጥ ለማምጣት የመጡት ሰዎችን፤ በእንዲህ አይነት የተቃውሞ ፖለቲካ ውስጥ ስትሆን አንዱ ሥራህ የመንግሥት ስልጣንን በያዘው ኃይል ውስጥ ያለውን ነገር ማጥናት ነው።

ስለዚህ በኢህአዴግ ውስጥ የሚደረጉትን ለውጦች እንከታተል ነበር፤ እና አንዱ ትልቁ ጥያቄ የነበረው እነ ዐቢይ ሲመጡ ኢህአዴግን በአዲስ መልኩ ለማስቀጠል የመጡ ሰዎች ናቸው ወይንስ እውነተኛ ለውጥ ፈልገው የመጡ ናቸው የሚለውን መመለስ ነበር። እነዚህ ሰዎች ዝም ብሎ በፊት የወያኔ ሥርዓት ይከተል የነበረውን ነገር ለማስቀጠል የሚያስቡ ሰዎች እንዳልሆኑ ስንረዳ ብዙ ጊዜ አልወሰደብንም።

ምክንያቱም በከፊል የመጡትም በህዝብ ትግል ነው። ሀያ ምናምን ዓመት ያልተቋረጠ ትግል ሲካሄድበት የነበረው ከዛም ሦስት ዓመት ደግሞ ያላቋረጠና የተጋጋለ ሰፊ የህዝብ ትግል ሲካሄድበት የነበረው ነው። ኢህአዴግ በነበረበት ሊቀጥል እንደማይችል ግልፅ የሆነበት ጊዜ ነው። በዚያን ጊዜ የመጡት እነዚህ ሰዎች ኢህአዴግን ሸውደን ሌላ አዲስ መልክ አምጥተን እናስቀጥል ብለው የሚያምኑ ሳይሆኑ በርግጥም የበፊቱ ሥርዓት ተሸንፎ የመጡ ናቸው።

ይህንን አንዴ ከወሰንክ በኋላ፣ ተጋግዘህ ያንን ሥርዓት ለማቆም ትሞክራለህ እንጂ በፊት የነበሩት ሰዎች እንዲህ ነበሩና በመሳሪያ ልቀጥል የምትለው ነገር አይደለም። እኛ በምንም አይነት፣ መቼም ቢሆን የመሳሪያ ትግልን እንደጥሩ ነገር አድርገን ገብተንበት አናውቅም። ምርጫ አጥተን የገባንበት ነው። ያን አላስፈላጊ የሚያደርግ ነገር ሲፈጠር ደቂቃም አልፈጀብንም። ተመልሰን ወደ እውተኛ ሰላማዊ እንቅስቃሴ፣ ወደ እውነተኛ ዲሞክራሲያዊ መንገድ መሄድ የተሻለ ነው ብለን ነው የገባንበት።

በኢህአዴግ ውስጥ ወጥ ነው ማለት ባይቻልም ለውጡን ይዘው የመጡት ኃይሎች በርግጥም ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት የሚፈልጉ መሆናቸውን እናምናለን። ያንን ሥርዓት ለማምጣት ከእነርሱ ጋር አብረን እንሰራለን፤ ከዚያ በኋላ ኢህአዴግ ካሸነፈ፤ እኛ እኮ በፊትም ኢህአዴግ ለምን አሸነፈ አይደለም፤ የሕዝብ ፍላጎት የህዝብ ፈቃድ አግኝቶ ያሸንፍ ነው የምንለው።

ማንም የህዝብ ፍቃድ አግኝቶ ያሸንፍ የህዝብ መብት ይከበር፣ ሰብዓዊ መብቶች ይከበሩ። የህግ ልዕልና ይኑር። እነኚህ ናቸው ጥያቄዎቹ። ማን ስልጣን ያዘ አይደለም። ዋናው ጥያቄ በምን መልክ ስልጣን ይያዛል? የህዝብ ፈቃድ አግኝቶ ነወይ? ህዝብ በፈለገ ጊዜ ሊያወርደው የሚችል ነወይ? ከዛ በተጨማሪ ደግሞ እውነተኛ ነፃ የሆኑ ተቋማት አሉ ወይ? ፍርድ ቤቱ በነፃነት ይሰራል ወይ? ጦር ኃይሉ በርግጥም ህብረተሰቡን የሚጠብቅ ነው ወይስ የአንድ ፓርቲ መሳሪያ? የምርጫ ተቋሞቹ እርግጥም ነፃና የህዝብ ፍላጎት የሚንፀባረቅባቸው ምርጫዎች ለማድረግ ፈቃደኞች ናቸው? እነዚህ ናቸው ጥያቄዎቹ። ያንን ለማድረግ ፍላጎት ያለው አካል እስከመጣ ድረስ እኛ ምንም ችግር የለብንም።

ቢቢሲ አማርኛ፦ ሥርዓቱን ሰው ባይጥለው ኢኮኖሚ ይጥለዋል ትል ነበር። አሁን ያለውንስ መንግት?

ፕሮፌ. ብርሃኑ ነጋ፡ ይኼ አዲሱ የለውጥ ኃይል ከነበረው የወጣ ነው ብለህ ብታስብ፣ ፕሮፓጋንዳውን ምናምኑን ትተህ የተረከበው ኢኮኖሚ ደንበኛ የዝርፊያ ሥርዓት የሽፍታ ኢኮኖሚ ሥርዓት ነበር። ዝም ብለህ ያገኘኸውን ዘርፈህ የምትሄድበት። የነበሩትን ፕሮጀክቶች ይካሄዱ የነበሩትን እንዳለ ብታይ ከዝርፊያ ጋር የተያያዙ ናቸው።

የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ምናምን ብለህ አንድ ጤነኛ ሰውና ስለከተማ ትራንስፖርት የሚያውቅ ሰው እንዲህ አይነት የከተማ ትራንስፖርት፣ በዚህን ያህል ወጪ አውጥቶ አይተክልም ነበር። በጣም ቀላል የሆኑ፣ በቀላሉ የከተማዋን የትራንስፖርት ችግሮች የሚፈቱ፣ እንደዚህ ከተማዋን ለሁለት ከፍለህ አስቀያሚ ሳታደርገው ልትፈታ የምትችልባቸው መንገዶች ነበሩ።

ፕሮጀክቶቹ በአንድ መልኩ ወይም በሌላ ለመስረቂያ ተብለው የተዘረጉ ናቸው። ለዚህ ነው ማለቅ ያልቻሉት። ለዚህ ነው ከአስር ከሃያ እጥፍ በላይ ወጪ የሚያስወጡት። እነኚህ ሁሉ የሆኑት ደግሞ በሕዝብ ስም በሚገኝ ብድር ነው። ይህ ሁሉ ብድር ሀገሪቱ ላይ ተከምሮ ወደ ሰላሳ ቢሊየን ዶላር ብድር ያለባት ሀገር ነች።

ይህ የሆነው ያ ሁሉ ብድር ከተሰረዘ በኋላ፣ በተለይ ከምርጫ 97 በኋላ የመጣ ይህንን የዘረፋ ሥርዓት ለማቆየት የተዘረጋ ሥርዓት ነው። ይኼ ነገር መጥቶ መጥቶ በተወሰነ ደረጃ ኢኮኖሚውን ዝም ብሎ ያራግበዋል። ምክንያቱም ዝም ብሎ ገንዘብ ኢኮኖሚ ውስጥ ስላለ። በኋላ ላይ ግን ተንገራግጮ መቆሙና ችግር ውስጥ መጣሉ የማይቀር ነው። እና በዚህ ምክንያት ይህንን ሥርዓት የተረከቡት ሰዎች በጣም ከባድ የሆነ ችግር ይገጥማቸዋል። አንደኛው እዳውን መክፈሉ፤ ሁለተኛ በአጠቃላይ የንግድ ሥራን በሚመለከት ያለው ባህል ተበላሽቷል። ሁሉም በስርቆት በማጭበርበር በምናምን አገኛለሁ ብሎ የሚያስብ የኢኮኖሚ ክላስ ነው የተፈጠረው።

ሀብታም የሚባሉትን፣ በአጭር ጊዜ ቢሊየነር ሚሊየነር ሆኑ የሚባሉትን፣ አይነት ግለሰቦችን ብታይ ቁጭ ብለው አስበው ምን ያዋጣል ለህብረተሰቡ የተሻለ እቃ እንዴት እናቅርብ በማለት አይደለም። ወይ መሬት ዘርፈው፣ ወይ ከባንክ ገንዘብ ተበድረው ያገኙት ነው። በዚያ አይነት መሰረት ላይ የቆመ ኢኮኖሚ ሁል ጊዜ ችግር ይገጥመዋል። ይህንን ሁሉ መቀየር በማክሮ ኢኮኖሚ ደረጃ ያሉብህን ችግሮች መፍታት ብቻ ሳይሆን የንግድ አመለካከቱን ባህሉን ራሱ መቀየር በጣም ሰፊ ሥራ የሚጠይቅ ነገር ነው።

ይህንን ለማስተካከል ግን በመጀመሪያ የፖለቲካው ሥርዓቱ መስተካከል አለበት። ከዚያም ባሻገር ግን ሰላምና መረጋጋቱ ወዲያውኑ መምጣት አለበት። ይህንን የፖለቲካ ነገር ሳታስተካክል የኢኮኖሚውን ነገር ማስተካከል ከባድ ነው። ለዚህ ነው ቅድሚያ የፖለቲካ ማስተካከያዎች መወሰድ ያለባቸው እንጂ፤ ቶሎ ብሎ የእነዚህን የኢኮኖሚ ችግሮች አንድ በአንድ መመልከት ግዴታ ነው። መንግሥትም ይኼን ይገነዘባል ብዬ አስባለሁ። የለውጥ ኃይልም ስለሆነ ከሌሎችም ሀገሮች በተወሰነ መልኩ እዳውን ለመቀነስ ትብብር ያገኛል ብዬ አስባለሁ። ምንም እንኳ ፖለቲካውን የመፍታት እርምጃ መውሰድ ቀዳሚ ቢሆንም የኢኮኖሚውንም ችግር ለመፍታት በአንድ ላይ እርምጃ መወሰድ አለበት።

ቢቢሲ አማርኛ-አንዳንድ የተወረሱብህን ንብረቶች ለማስመለስ ሞክረሃል?

ፕሮፌ. ብርሃኑ፡ እስካሁን አልተመለሱም። ይኼ ለውጥ ስለእኔ አይደለም። 100 ሚሊየን ህዝብ የሚበላው ያጣ ያለበት ሀገር አሁን የእኔን ንብረት መለሱ አትመለሱ በጣም ትልቅ ነገር አይደለም።

የተንቀሳቃሹ ምስል መግለጫ,

ፕሮፌ. ብርሃኑ ነጋ የአርበኞች ግንቦት 7 ሊቀ-መንበር

ቢቢሲ አማርኛ- ከኢኮኖሚ ውጪ የአብይ አስተዳደር ትልቁ ፈተና ከየት ይመጣል?

ፕሮፌ. ብርሃኑ፡ የደህንነት፣ ሰላም የማረጋጋት፣ ባለፈው27 ዓመት የተፈጠረው የክልል አደረጃጀት። የክልል አደረጃጀቱ ደግሞ ዝም ብሎ በዘር ላይ፣ በደም ቆጠራ ላይ መመስረቱ ብቻ አይደለም። በዚያ ላይ የተመሰረተው አከላለል የራሱ ጦር ያለው አገር ነው። አሁን እነዚህ ክልሎች የምትላቸው የራሳቸው ሀያ ሺህ፣ ሰላሳ ሺህ. . . ጦር አላቸው የሚባል ነው።

በአንድ ሀገር ውስጥ እስከ አፍንጫቸው የታጠቁ ክልሎች ሊኖሩ አይገባም። በአንድ ሀገር እንደዚህ አይነት ኃይል ሊኖር የሚገባው የመንግሥት መከላከያ ነው። ለሁሉም እኩል የሆነ፣ ሁሉንም በጋራ የሚያገለግል፣ የሁላችንንም ደህንነት የሚጠብቅ ኃይል። አሁን ግን በሁሉም ክልሎች ያሉ ኃይሎች አሉ።

እነዚህን ሁሉ እንዴት አድርጎ በአንድ ሀገራዊ የመከላከያ እዝ ስር ታደርጋቸዋለህ? በየአካባቢው ከብሔር ጋር በተያያዘ የተነሱ ግጭቶችን እንዴት ታስቆማቸዋለህ? እንደ አገር ወይ ከዚህ ችግር ወጥተን እንበለፅጋለን። ወይ እንደሃገር እንፈርሳለን። የተወሰነ ቡድን አልፎለት፣ ሌላው የማያልፍለት አገር ሊኖረን አይችልም።

ሁላችንም ተሰባስበን የምንኖርባት፣ የሁላችንም መብት የተከበረባት፣ የሁላችንም ባህል የሚከበርባት፣ የሁሉም ቋንቋ የሚከበርባት የተረጋጋች ሀገር መፍጠር በጣም ከባዱ ከእነ ዶ/ር አብይ ብቻ ሳይሆን ሁላችንም ይሄንን ዲሞክራሲያዊ ስርዓት በመገንባት ሂደት ላይ የሚገጥመን ችግር ነው።

ነገር ግን በደንብ መነጋገር ከቻልን በማስፈራራት ሳይሆን ቁጭ ብለው እየተነጋገሩ ህብረተሰቡ ያሉትን አማራጮች እየሰማ የምንነጋገርበት አይነት የፖለቲካ ምህዳር መፍጠር ከቻልን፣ የፖለቲካ ድርጅቶች በምን አይነት የፖለቲካ ሂደት ፖለቲካቸውን እንደሚያስተዋውቁ በደንብ ከተስማሙና ሁሉም ለዚያ ታማኝ ከሆኑ የምንወጣው ችግር ነው። የሚያቅተን አይደለም። አሁን ብዙ ችግር ያለ ይመስላል። ነገር ግን እነዚህን መሰረታዊ ነገሮች ማስተካከል ከቻልን ወደዚያ እንሄዳለን። ግን ትልቁ ተግዳሮት አሁን ያለው ግን ይኼ ነው። ፖለቲካውን ማረጋጋት፣ ፖለቲካውን ወደ ሰለጠነ ፖለቲካ መውሰድ ትልቁ ተግዳሮት ነው የሚመስለኝ።

ቢቢሲ አማርኛ፦ አሁን ያለው የሀገሪቷ ነባራዊ ሁኔታ አንተ ስትሄድ ከነበረው በበለጠ የብሔርተኝነት ስሜት ናኝቶ በኦሮሚያና በአማራ ክልል አንዳንድ ቦታዎች ተቃውሞ ሲገጥማችሁ እያየን ነው። እንዲህ ባለው ሁኔታ የድጋፍ መሰረታችን የት ነው የምትሉት?

ፕሮፌ. ብርሃኑ፦ ሁለት ነገር ማንሳት እፈልጋለሁ። አንደኛ ለእኛ የሚያሳስበን ነገር ምን ያህል የፖለቲካ ድጋፍ የት እናገኛለን የሚለው አይደለም። ትልቁ የሚያሳስበው ጥያቄ ይህችን አገር እውነተኛ ዴሞክራሲያዊ አገር ማድረግ ላይ ነው። ትልቁ ጉልበታችንን የምናፈስበት ጉዳይ እሱ ነው። ሁለተኛ አንድ ነገር እውነታ ሆኗል ማለት አይቀየርም ማለት አይደለም። ኢትዮጵያ እኮ ደሃ ሀገር ነች። ይሄ እውነታ ሁሌም ደሃ አገር ያደርጋታል ማለት አይደለም።

የተለያዩ ፖሊሲዎችንም ያረቀቅነው ይህንን እውነታ ለመቀየር ነው። የኢትዮጵያም የፖለቲካ እውነታ በአብዛኛው ለ27 ዓመት ይሰማው የነበረ ፕሮፓጋንዳ ምክንያት ብሔር ብሔረሰቦች ስሜት ውስጥ ገብተዋል ከሆነ አንደኛ ቁጥሩ ላይ መስማማት አንችልም። ምክንያቱም በተጨባጭ የምናውቀው ነገር የለም። ምን ያህሉ ሰው በዜግነት ፖለቲካ ያምናል? ምን ያህሉስ በብሔር? የሚለው ሁኔታ ላይ በተጨባጭ የተሰራም ሆነ የተሰበሰበ ጥናት የለም።

በአብዛኛው ልኂቅ በብሔር ፖለቲካ ውስጥ እንደተዘፈቀ ግልፅ ነው። ህብረተሰቡ ገብቷል ወይ? የሚለው አጠራጣሪ ነው። ሁለተኛ ብዙ ሰው ዘንግቶታል እንጂ በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ ኢትዮጵያ ማህበረሰቧ የተደባለቀ ነው። ንፁህና ያልተቀላቀለ ማህበረሰብ ለማግኘት አዳጋች ነው። ሦስትና አራት ትውልድ ብንቆጥር ሁላችንም ከተለያየ ብሔር ጋር የተደባለቅን ነን። እሱ ቀርቶ በአንድ ትውልድ እንኳን አባት አንድ ብሔር እናት ሌላ ብሔር ሆና የተወለደው በትክክለኛ መንገድ ቢቆጠር ከማንኛውም ከአንድ ብሔር ነኝ ከሚለው የሚበልጥ ይመስለኛል።

ይሄ ሁሉ ከዚህ የብሔር ፖለቲካና ከመጣው ግጭት መውጣት የሚፈልግ የማህበረሰብ አካል ነው። እኛ የምንለው አንደኛ እነዚህ ሃሳቦች በነፃነት የሚገለፁበት፣ ህብረተሰቡ ከስሜት ወጥቶ ለአገራችን፣ ለህዝባችን፣ ለራሳችን የሚጠቅመን የቱ ነው ብሎ በደንብ ማሰብ በሚጀምርበት ጊዜ እነኚህ ነገሮች ይቀየራሉ። የፖለቲካ ስሜት የማይቀየር በድንጋይ ላይ የታተመ ነገር አይደለም። ሁልጊዜም ይቀያየራል።

ከአርባ አመት በፊት ሁላችንም ሶሻሊስቶች ነበርን። የሶሻሊዝም ርዕዮተ ዓለም በተግባር ሲታይ ምን እንደሆነ ካየ በኋላ ነው ሰው ሁሉ የሚያዋጣ አለመሆኑን ተረድቶ የተቀለበሰው።

ከ27 ዓመት በፊት ይሄ የዘር ፖለቲካ ሲመጣ፤ ብሔር ብሔረሰቦች በሰላም የሚኖሩበት ብልፅግና ያለበት ሁሉም እኩል የሚሆንበት ተብሎ ነበር። አሁን ስናየው ግን ሰላምና እኩልነት የሌለበት፣ ብሔርና ብሔረሰቦች ራሳቸውን ማስተዳደር ያልቻሉበት፣ የውሸት እንደሆነ ማህበረሰቡ ተገንዝቦታል።

አሁን እንግዲህ መጪውን ጊዜ ሰው ቁጭ ብሎ ማሰብ የሚጀምርበት ጊዜ ነው። በነፃነት ማሰብ፣ መወያየትና ሃሳቦቹን ለህብረተሰቡ ማቅረብ ከቻልን እኔ ብዙሃኑ ኢትዮጵያዊያን በዜግነት ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ ይመርጣሉ ብዬ አስባለሁ። ስለዚህ አያስፈራኝም!

ስለዚህ ትልቁ ነገር እኛ እንደ ፓርቲ ምን ያህል ድምፅ እናገኛለን፣ የቱጋ እናሸንፋለን የሚለው አይደለም፤ ጥሩ የፖለቲካ ምህዳር ተፈጥሮ ሁሉም ሃሳቦች በነፃ የሚንሸራሸሩበት፤ በውሸት ስሜት ህብረተሰብን ማነሳሳት የሚቀርበት ሁኔታ እንዲፈጠር እንፈልጋለን።

ስሜት፣ መገፋፋትና ዘላቂ ጥቅምህን ማወቅ የተለያዩ ነገሮች ናቸው። ቀስ ብለው ሰዎች መወያየት ሲጀምሩም ነው ለእኔ፣ ለቤተሰቤ የሚበጀኝ፤ ዘላቂ ጥቅሜ ምንድን ነው? ብለው ማሰብ የሚችሉት። በዚያ ጉዳይ ላይ የዜግነት ፖለቲካ ከምንም ነገር በላይ ለዚች ሀገር ዘላቂ ሰላምና ብልፅግና መሰረት እንደሆነ ጥያቄ የለንም። ለዚሀም ነው ዛሬ ባይሆን መቼም ወደፊትም የዜግነት ፖለቲካ የበላይነት ጥያቄ ውስጥ የማናስገባው።

ቢቢሲ አማርኛ፡ ኤርትራውስጥ ስትንቀሳቀሱ በነበረበት ወቅት ኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) ጋር የነበራችሁ ግንኙነት ምንድን ነው?

ፕሮፌ. ብርሃኑ፡ ኤርትራ በነበርንበት ጊዜ ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር አመራር ጋር ተገናኝተን አናውቅም። ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር አባላት ጋር [ማለትም] ከተራ አባላት ጋር በአንድ ወይም በሌላ ምክንያት ከተለያዩ ሰዎች ጋር እንገናኛለን። ከኦሮሞ ነጻነት ግንባር የመጡ ብዙ የኦሮሞ ተወላጅ አባሎች ነበሩን፤ አሉን።

ከብሔር ውጪ የሆነ ለሁሉም ኢትዮጵያዊ ክፍት የሆነ ድርጅት ስለሆነ ከየትም አማራም፣ ትግሬም፣ ኦሮሞም የሚገባበት ድርጅት ነው። ብዙም ችግር ስላልነበረ ብዙ የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ታጋዮች የነበሩ አባሎች ነበሩን። እኛም ጋር አባል ሳይሆኑ ኤርትራ ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ብዙ የኦሮሞ ወገኖቻችን ጋር በጓደኝነት፣ በወዳጅነት ስንሠራ ነበር።

ከኦነግ ከወጡት ከእነ ከማል ገልቹ፣ ኮለኔል አበበ ጋር ብዙ ጉዳዮች ላይ አብረን እንወያያለን። ለሀገራችን የሚሻለው ምንድን ነው? የሚሉ ነገሮች ላይ እንወያያለን። እንደ ድርጅት ከዚህ በፊት ጀምሮና እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስም ከሌሎች የኦሮሞ ድርጅቶች ጋር አብረን እንሠራ ነበር። ከኦሮሞ ዲሞክራቲክ ፍሮንት ጋር በጋራ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ንቅናቄ የሚል ፈጥረን ስንንቀሳቀስ ነበር። ከነከማል ገልቹ ጋርም ተመሳሳይ ነበር።

ስለዚህ ለእኛ ኦሮሞ ሆነ፣ ትግሬ ሆነ፣ አማራ ሆነ፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ነው። እንደ ድርጅት የሀገሪቱን አንድነትና ለሁሉም ሕዝቦቿ እኩል የሆነች ሀገር እንድትሆን የሚፈልግ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ጋር አብረን እንሰራለን። አሁንም የኦሮሞ ወገኖቻችን ድርጅታችን ውስጥ አባል ናቸው።

አሁን ካለው በአቶ ዳውድ ኢብሳ ከሚመራው ኦነግ ጋር ኤርትራ ከገባን ሳይሆን ከሰባት፣ ስምንት ዓመት በፊት እንዴት በጋራ አብሮ እንደሚሠራ ውይይት ነበረን። ከዚያ በኋላ እዛም ውስጥ ችግሮች ነበሩ። እኛ ከበፊትም የነበረን ግልጽ የሆነ አንድ አቋም ነው። ለአገር አንድነት ቅድሚያ መስጠት አለብን። እንደ ሀገር አንድ ካልሆንን በጋራ ፖለቲካ መሥራት አንችልም የሚል አቋም ነው። ከማንኛውም ድርጅት ጋር ስንሠራ የምንለው በኢትዮጵያ ሀገራዊ አንድነት ታምናለህ? በዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ታምናለህ? ነው። ከዚያ በኋላ ሌላውን ውይይት ማድረግ፤ መደራደርም እንችላለን።

ለመጨረሻ ጊዜ አቶ ዳውድን ያገኘሁት ወደ ኤርትራ ለአንድ ጉዳይ ስመለስ ኤርፖርት ውስጥ ነው። ሰላም እንባባላለን። እዚህም ተገናኝተናል። በፖለቲካ ፓርቲ ድርጅቶች ውይይት ውስጥ ገንቢ የሆነ ውይይት እናደርጋለን ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። ይቺ አገር የጋራችን ነች። ለሁላችንም የምትሆን ሀገር መፍጠር ነው። የተሻለ ሀሳብ አለን የሚሉ ሀሳባቸውን ለማኅበረሰቡ አቅርበው በዚያ በሚደረግ ውይይት ሕዝብ የመረጠውን መቀበል ግዴታችን ነው።

ሁላችንም መረዳት ያለብን በአንድ ሀገር ውስጥ ሦስት ወይም አራት የታጠቁ ኃይሎች ሊኖሩ አይችሉም። ፖለቲካ እንደዛ ሊሆን አይችልም። በሰላማዊ መንገድ ፖለቲካችንን እንሠራለን ብለን ካሰብን፤ ሁላችንም መሳሪያ አውርደን እንገባለን ነው ያልነው። ስለዚህ አውርደን በሰላማዊ መንገድ ፖለቲካው ውስጥ ገብተን ለሀገራችን ይበጃል የምንለውን ለኅብረተሰቡ አቅርበን ሕዝቡ የሚወስነውን መቀበል ነው።

ቢቢሲ አማርኛ፡ ፕሬዘዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ለመጨረሻ ጊዜ ያገኘሀቸውስ መቼ ነው?

ፕሮፌ. ብርሀኑ፡ መጨረሻ የተገናኘነው ነሀሴ ላይ ነው። ወደዚህ ከመምጣቴ በፊት ለመሰነባበት ተገናኝተን በሀገራችን በአካባቢያችን ጉዳዮች ላይ አውርተናል።

ቢቢሲ አማርኛ፡ ምን አይነት ግንኙነት ነበራችሁ?

ፕሮፌ. ብርሀኑ፡ እሳቸው ፕሬዘዳንት ናቸው። እኔ አንድ ታጋይ ነኝ። ስለዚህ ምን ግንኙነት ይኖረናል? አንዳንድ ጊዜ እንገናኛለን። በሀገርና በአካባቢ ጉዳይ እናወራለን። ግን ከእሳቸው በታች ያሉ በእኛ ሥራ ዙሪያ አብረናቸው የምንሠራ ሌሎች ሰዎች አሉ። ፕሬዘዳንቱ ፕሬዘዳንት ናቸው፤ በየጊዜው እየሄድኩ እሳቸውን የማገኝበት ሁኔታ የለም።

ቢቢሲ አማርኛ፡ለወደፊት ጡረታ ወጥተምናልባት በሲቪል ወይም በቢዝነስ ዘርፍ ስትሳተፍ ራስህን ታያለህ?

ፕሮፌ. ብርሀኑ፡ በጣም አያለሁ። የጀመርነው፣ በጣም ብዙ ሰው የሞተበት፣ የተጎዳበት፣ ይቺን ሀገር ዴሞክራሲያዊ የማድረግ ነገር በደንብ መሰረት ከያዘ በኋላ ለረዥም ጊዜ ፖለቲካ ውስጥ የመቆየት ፍላጎት የለኝም። በ94 [በአውሮፓውያኑ] ስመጣም ፖለቲካ ውስጥ ልገባ አልነበረም። አስተምር ነበር። በኢኮኖሚው ዙሪያ እሳተፍ ነበር። ጋዜጦች ላይ እጽፍ ነበር። የኢኮኖሚ ባለሙያዎች ማኅበር ውስጥ እሠራ ነበር። ፖለቲካ የሚባል ነገር ውስጥ ተመልሼ እገባለሁ አላልኩም።

በልጅነቴ ኢሕአፓ ውስጥ ከገባሁ በኋላ ተመልሼ [ፖለቲካ ውስጥ] እገባለሁ ብዬ አላሰብኩም ነበር። በአንድ መልኩ ወይም በሌላ ፖለቲካ ውስጥ መልሶ ያስገባኝ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ውስጥ ለተማሪዎች ስለ አካዳሚክ ነጻነት ንግግር ካደረግን በኋላ ከፕሮፌሰር መስፍን ጋር ስንታሰር ነው። እንዲህ አይነት ሥርዓት ካለ፣ ነጻነት ከሌለ፣ በነጻነት መነጋገር ካልተቻለ ሌሎች የሚሠሩ ሥራዎችም የውሸት ይሆናሉ።

አካዳሚሽያን [ትምህርታዊ ጉዳዮች ላይ የሚያተኩር ባለሙያ] ነኝ፣ አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ውስጥ አስተምራለሁ ብለህ ነጻነት ከሌለህ፣ የምታስተምረውን ነገር በነጻነት ማስተማር ካልቻልክ፤ የምታስተምረው በተወሰነ ደረጃ የውሸት ነው የሚሆነው። የፖለቲካ ሥርዓቱ ለፖለቲካ ስልጣን ሳይሆን ለዕለት ተዕለት ሥራዎች እንኳ በእኩልነት ላይ የተመሰረተ አይደለም።

ባለፈው 27 ዓመት ውስጥ ነጋዴ ብትሆን የሚያሳብድ ነው የሚመስለኝ። ንግድ ማለት የውድድር ቦታ ከሆነ፤ የኢኮኖሚው ሥርዓት ሙሉ በሙሉ በአድልዎ ላይ የተመሰረተ ከሆነ ምንም ልትነግድ አትችልም። አንተንም ከፀባይህ አውጥተው እንደነሱ አጭበርባሪ ሆነህ የምትኖርበት ሁኔታ ነው የሚፈጠረው።

እንደ አንድ እውነተኛ ዜጋ ለመኖር የፖለቲካ ምህዳሩ ነጻነትህን የሚያከብር፣ በማኅበረሰቡ ውስጥ ሀሳብህን በነጻነት መግለጽ መቻልህ፣ በምትሠራው ሥራ ጣልቃ የማይገባ መሆኑ አስፈላጊ ነው። ከብዙ ሰዎች ጋር የምለየው በዚህ ነው። እነሱ ይሄ ፖለቲካ ውስጥ መግባት ነው የሚመስላቸው። እኔ ፖለቲካ ውስጥ መግባት አልለውም። ይሄ መሰረታዊ የሆነ ዜግነትህን ማስከበር ነው።

ኢትዮጵያዊ ነኝ ካልኩ እንደ ኢትዮጵያዊ ይገባኛል የምለው መሰረታዊ ነጻነት አለ። ያንን ካላገኘሁ ኢትዮጵያዊ አይደለሁም። ከዚህ ጠፍቼ፤ ከዚህ ሸሽቼ አሜሪካና አውሮፓ የምኖር ጊዜ ያለኝ ነጻነት ሀገሬ ውስጥ ካለው ነጻነት የበለጠ ከሆነ እውነተኛ ዜጋ አይደለሁም። ፖለቲካ ውስጥ ያስገባኝ ይሄ ነው።

እስር ቤት ከገባን በኋላ በጣም ብዙ ኦሮሞ ወገኖቻችን ታስረው ሳይ ሀገሪቱ ወደ ምን አይነት አደጋ ውስጥ እየገባች እንደሆነ ነው ያየሁት። አሁንም ለእኔ ፖለቲካ ማለት እነዚህን መሰረታዊ የሆኑ የዜግነት መብቶች ማስከበር፤ ሁሉም የሀገሩ ባለቤት የሚሆንበት ድባብ መፍጠር ነው። ይሄ የምርጫ ጉዳይ ሳይሆን ግዴታችን ነው።

ያንን ማድረግ ካልቻልክ፤ የዜግነት መብትህን እየወረወርክ ነው። ይህንን በፍጹም ማንኛውም ዜጋ ማድረግ የለበትም ብዬ አምናለሁ። ለእኔ ፖለቲካ የሚያያዘው ከዚህ ጋር ነው። ከዚያ በኋላ ያለው ምርጫ ምናምን አድካሚውና በፍጹም የማይረባው የፖለቲካ ክፍል ነው። ዋናው ሥራ ካደረስኩ በኋላ ለጡረታም ደርሻለሁ፤ ትንሽ የማርፍበት ጊዜ ነው።