አትላንቲክን በበርሜል ለማቋረጥ ያለመው አዛውንት ፈረንሳያዊ

አትላንቲክን በበርሜል ለማቋረጥ ያለመው ፈረንሳዊ

የፎቶው ባለመብት, AFP

ፈረንሳያዊው አትላንቲክን በበርሜል ቅርፅ በተሰራ ክብ መሳይ ጀልባ ለማቋረጥ ጉዞውን ጀምሯል። ይህ ፈረንሳያዊ ሀሳቡ የንፋስ ግፊትን በመጠቀም ያሰበበት መድረስ ነው ።

ይህ የ71 ዓመቱ አዛውንት ከስፔኗ ደሴት ተነስቶ በሶስት ወር ውስጥ ካሪቢያን ደሴቶች ላይ የመድረስ ብርቱ ምኞት በልቡ አኑሯል።

በበርሜል ቅርፅ የተሰራው ጀልባው ውስጥ እንቅልፉ ቢመጣ የሚያሸልብበት፣ ቢርበው የሚያበስልበት እና እቃዎቹን ሸክፎ የሚያስቀምጥበት ቦታ አለው።

እግረ መንገዱን አትላንቲክ ውቅያኖስ ላይ የንፋስ አቅጣጫን አጥኚዎችን እንዲረዳ በማለት በሚያልፍበት ሁሉ ምልክቶችን ያስቀምጣል።

ጉዞውን በጀመረበት ዕለት "እስከ ቅዳሜ ድረስ የአየር ጠባዩ ሸጋ ነው፤ መጓጓዣዬም በጥሩ ሁኔታ ላይ ትገኛለች" በማለት ለፈረንሳዩ የዜና ወኪል ተናግሯል።

ይህ የ71 ዓመቱ ብርቱ አዛውንት በጉብዝናው ወራት ወታደር ሆኖ ያገለገለ ሲሆን በኋላም የፓርክ ዘብ እንዲሁም አውሮፕላን አብራሪ ሆኖ አገልግሏል።

የውቅያኖስ ላይ የንፋስ ሞገድ ግፊት አንከብክቦ ያሰበበት የካሪቢያን ደሴቶች ጋር እንደሚያደርሰው እምነቱ የፀና ነው።

የፎቶው ባለመብት, AFP

"ባርቤዶስ ወይንም ከፈረንሳይ ደሴቶች በአንዱ የምደርስ ይመስለኛል" ሲል ቀልዷል።

ሶስት ሜትር ርዝመትና ሁለት ነጥብ አስር ሜትር ስፋት ያለው በርሜሉ አዛውንቱ የባህር ውስጥ እንስሳትን ማየት እንዲችል የሚያደርግ ወለል ተገጥሞለታል።

ለመጪው የፈረንጆች አዲስ አመት ከወዳጅ ዘመዶቹ ተነጥሎ በውቅያኖስ ላይ በንፋስ እየተገፋ ቀኑን ሲገፋ እንዳያዝን በማሰብ ነጭ ወይን ተቀምጦለታል።

እኝህ አዛውንት 71 ዓመቱን ፉት ብሎ ጨርሶ 72ን አሃዱ ብሎ የሚጀምረው እዚሁ ውቅያኖስ ላይ ነው።