የኢትዮ-ኤርትራ ድንበር ስለመዘጋቱ መረጃ የለኝም፡ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም

ባለፉት ጥቂት ቀናት እንደተዘጋ ስለሚነገረው የኢትዮጵያ እና ኤርትራ ድንበርን በተመለከተ መረጃ እንደሌላቸው የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ መለስ ዓለም ተናገሩ።

ቃል አቀባዩ ይህንን የተናገሩት ዛሬ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ነው። አቶ መለስ ጨምረውም ስለጉዳዩ ዝርዝር መረጃ ይዘው በቅርቡ አስተያየት እንደሚሰጡ ተናግረዋል።

በተያያዘም በኢትዮጵያ የኤርትራ አምባሳደር አቶ ሰመረ ርዕሶም የሹሙት ደብዳቤያቸውን ዛሬ ለፕሬዚዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ማቅረባቸውን፤ በቅርቡ በፕሬዚዳንቷ በአምባሳደርነት የተሾሙት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ መለስ አለም አሳውቀዋል።

አቶ መለስ በመግለጫቸው ያነሱት ሌላኛው ነጥብ በመጭው ታህሳስ 22/ 2011 ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቀውን የኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ተለዋጭ አባልነት ነው።

ለሁለት ዓመታት ያህል ተለዋጭ አባልነቱን ይዛ የቆየችው ኢትዮጵያን በመተካት ደቡብ አፍሪካ ቦታውን ትረከባለች።

ኢትዮጵያ የተለዋጭ አባልነቱን ስትይዝ በታሪኳ ለሦስተኛ ጊዜ ነበር። አቶ መለስ የኢትዮጵያን የቆይታ ጊዜ "ስኬታማ" እና "የሐገር ጥቅም ያስጠበቀ" ነበር ሲሉ ገልፀውታል።

የአፍሪቃ ቀንድ ደህንነት እንዲሁም ዓለም አቀፍ ሰላም የማስጠበቅ እንቅስቃሴዎች ኢትዮጵያ በተለዋጭ አባልነቷ ወቅት ትኩረት ሰጥታ የሠራችባቸው ጉዳዮች ናቸው ብለዋል አቶ መለስ።

በተለይም በደቡብ ሱዳን እና በሶማሊያ ጉዳይ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታውም ምክር ቤት ይከናወኑ በነበሩ ውይይቶች እና የውሳኔ ኃሳቦች ላይ የኢትዮጵያ ግብዐት ፋይዳው ላቅ ያለ ነበር እንደቃል አቀባዩ አነጋገር።

ቃል አቀባዩ እንደተናገሩት ባለፉት ስድስት ወራት ባህር አቋርጠው ወደ ሳዑዲ አረቢያ የተጓዙ እና የጉዞ ሰነድ የሌላቸው 44500 ኢትዮጵያዊያንን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከሌሎች አካላት ጋር በመተባበር ወደ ሀገር ቤት እንዲመለሱ አድርጓል።

ህይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠው ወደ ሳዑዲ አረቢያ የሚሄዱ ዜጎች ቁጥር እየቀነሰ ያለመሆኑን የገለፁት አቶ መለስ ጅዳ የሚገኘው ቆንስላ ሁለት ባለሞያዎችን ለዚሁ ጉዳይ መድበዋል ብለዋል።

ባለፉት ሁለት ሳምንታት ብቻ ከአራት ሺህ በላይ ዜጎችን ከተለያዩ የአፍሪካ እና የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት እንዲመለሱ ተደጓርል ሲሉም አክለው ተናግረዋል።

ህጋዊ የስራ ስምሪት ስምምነት ከተለያዩ አገራት ጋር መፈራረም መጀመሩን የተናገሩት ቃል አቀባዩ ህገ ወጥ የሰው ዝውውር መስመሮች ሦስት መሆናቸውን አውስተዋል።

በዋናነት ከደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ በመነሳት፤ በኬንያ በኩል መዳረሻውን ደቡብ አፍሪካ የሚያደርገው የመጀመሪያው መስመር ሲሆን አዲስ አበባን እና አማራ ክልልን ማዕከሉ አድርጎ በሱዳን ወደ ሊብያ እና ከዚያም ወደ አውሮፓ የሚሄደው ሌላኛው መስመር ነው።

አማራና ትግራይ እንዲሁም አፋርን ማዕከል ያደረገ እና በየመን ወደ ሳዑዲ አረቢያ የሚያቀናው ደግሞ ሌላኛው መስመር ነው ተብሏል።