አሜሪካዊው ብቻውን ተወዳድሮ አንታርክቲካን በማቋረጥ ጨረሰ

ኮሊን ኦ የሚተኛባት ትንሿ ድንኳን

የፎቶው ባለመብት, Colin O'Brady

የ33 ዓመቱ አሜሪካዊ የማንንም እርዳታ ሳይሻ አንታርክቲካን በማቋረጥ ብቸኛው ሆኗል።

አሳሹ ኮሊን ኦ ብራዲ ውድድሩን በሀምሳ ሶስት ቀናት የጨረሰ ሲሆን፤ አብሮት ጉዞ የጀመረውን የአርባ ዘጠኝ ዓመቱ የእንግሊዝ ጦር መሪ ሊውስ ሩድን በቀናት ቀድሞ ጨርሷል።

በጥቅምት 24 ጉዟቸውን የጀመሩት ሁለቱ ግለሰቦች ከሁለት ዓመት በፊት የቀድሞ የእንግሊዝ የጦር መሪን የገደለ ጉዞ መሆኑ ምንም አይነት ተፅእኖ አላመጣባቸውም።

1ሺ 482 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ ያለው ይህ ጉዞ በምድር ላይ ቀዝቃዛ የሚባለውና በጣም በከፍተኛ ሁኔታ ፈታኝ የአየር ፀባይ ያለበት ነው።

ፕሮፌሽናል አትሌት የሆነው ኮሊን ጉዞውን በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ያጋራ ሲሆን በተለይም ከባድ በሚባለው ቀንም ላይ ከቢቢሲ ጋር ቆይታ አድርጎ ነበር።

"ከመጠን ባለፈ መልኩ ደክሞኛል፤ ተሰላችቻለሁ። ነገር ግን በየቀኑ ወደ መዳረሻ እየቀረብኩ እንደሆነ አውቃለሁ" በማለት ከሳምንት በፊት በበረዶ ግግር ተሸፍኖ በሳተላይት ስልኩ አማካኝነት ተናግሯል።

"170 ኪሎ ግራም የሚመዝን እቃዬን እየጎተትኩ በቀን ውስጥ ከ12-13 ሰዓታት ድረስ በአለም ላይ ቀዝቃዛ በሚባለው ቦታና ፈታኝ በሆነ ቦታ ላይ እየተጓዝኩ ነው" የሚለው አሳሹ፤ በከፍተኛ ሁኔታ ክብደት እንደቀነሰና እጁ ላይ ያለው ሰአትም ሊሆነው እንዳልቻለው ገልፆ ሰውነቱን ራቁቱን ማየት እንደሚያስፈራው ገልጿል።

የበረዶ ላይ እሽቅድምድም

ሁለቱ ግለሰቦች የተገናኙት ቺሊ ውስጥ በሚገኝ መጠጥ ቤት ሲሆን፤ ያለማንም እገዛ ለብቻቸው ውድድር ለማድረግ ተስማምተው ተለያዩ።

አሳሹ ኮሊን በኦውሮፓውያኑ 2008 ታይላንድ በነበረበት ወቅት ቃጠሎ ደርሶበት ተመልሶ መራመድ ሊከብደው እንደሚችል ቢነገረውም ከጥቂት ጊዜ በኋላ አገግሞ ሰሜንና ደቡብ ፖልን ጫፍ ላይ ወጥቷል።

የፎቶው ባለመብት, Colin O'Brady

ሊውስ ሩድ የሶስት ልጆች አባት ሲሆን አንታርክቲካን ለማቋረጥና ልምምዶችን ለማድረግ ከጦሩ እረፍት ወስዷል።

ይህንንም ለማድረግ ያነሳሳው የስራ ባልደረባውና ጓደኛው አንታርክቲካን ለማቋረጥ ሲል በመሞቱ ነው።

ሁለቱም ግለሰቦች ከምግብ የሚያገኙትን ካሎሪ በቁጠባ መጠቀም ያለባቸው ሲሆን በረዶ በማሞቅም ለሚጠጣ ዉሃ ሲጠቀሙበት ነበር።

ከመተኛታቸው በፊት እርጥብ ልብሳቸውን በሚተኙበት ድንኳን ውስጥ ጠቅልለው ከላዩ ላይ መተኛት ያለባቸው ሲሆን ይህም የሰውነታቸው ሙቀት ልብሱን እንዲያደርቀው ነው።

አሁን ግን ያ ፈታኝ ጉዞ አልቆ ወደ ሞቀ አልጋቸውና ቤታቸው የሚመለሱበት ጊዜ ሩቅ አይደለም።