ፈረንሳይ ስለሩዋንዳው ፕሬዚዳንት አሟሟት ጀምራ የነበረውን ምርመራ አቋረጠች

በሚሳኤል ተመቶ የወደቀው አውሮፕላን

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የፈረንሳይ ፍርድ ቤት ስለቀድሞው የሩዋንዳ ፕሬዚዳንት ጁቬናል ሀቢሪማናን አሟሟት ያደርግ የነበረውን ምርመራ ማቋረጡን ይፋ አደረገ።

እንደ አውሮፓውያኑ በ1994 ፕሬዚዳንት ጁቬናል ሀቢሪማና በአውሮፕላን እየተጓዙ ሳለ ሚሳኤል ተተኩሶባቸው ሕይወታቸው አልፏል።

ሞታቸው ሩዋንዳ ውስጥ የነበረውን የዘር ጭፍጨፋ አስከትሏል።

የፈረንሳይ መንግሥት ሚሳኤሉን ማን እንደተኮሰ ለማወቅ ምርመራ የጀመረው በአውሮፕላኑ ውስጥ በነበሩ ሠራተኞች ቤተሰቦች ጥያቄ ነበር።

የፈረንሳይ ፍርድ ቤት ተጠያቂ ያደረገው በአሁኑ የሩዋንዳ ፕሬዘዳንት ፖል ካጋሜ የሚመሩ የቱትሲ አማጽያንን ነው። የፕሬዚዳንቱ የቅርብ የሚባሉ ሰዋች ላይም የእስር ማዘዣ ወጥቶ ነበር። ሆኖም ክሱ ባለፈው ሳምንት መቋረጡ ተሰምቷል።

የፈረንሳይ አቃቤ ሕግ ለክሱ በቂ ማስረጃ ባለመገኘቱ ክሱ እንዲቋረጥ የጠየቀው ባለፈው ወር ነበር።

ፕሬዘዳንት ጁቬናል ሀቢሪማና እየተጓዙበት የነበረው አውሮፕላን በሚሳኤል ተመቶ መውደቁን ተከትሎ በተነሳው የዘር ጭፍጨፋ 800,000 ቱትሲዎችና በርካታ ሁቱዎች ተገድለዋል።

ከሁቱ ጎሳ የሆኑት ፕሬዚዳንቱ ከቱትሲ አማጽያን ጋር የሰላም ስምምነት አድርገው ወደ ሩዋንዳ መዲና ኪጋሊ እያቀኑ ሳለ ነበር ሚሳኤሉ የተተኮሰባቸው። በአውሮፕላኑ ተሳፍረው የነበሩ ሰዎች ባጠቃላይ ሕይወታቸው አልፏል።

እንደ አውሮፓውያኑ በ2006 ፈረናሳዊው ዳኛ ዣን-ልዊስ ብሩጊዬሬ፤ ፕሬዘዳንት ፖል ካጋሜ የሚሳኤል ተኩሱን እንዳዘዙ ተናግረው፤ የፕሬዚዳንቱ አጋሮች እንዲታሰሩ ጠይቀው ነበር።

የፍርድ ቤት ሂደቱ በፈረንሳይና በሩዋንዳ መካከል ያለውን ግንኙነት አሻክሯል። ፕሬዚዳንት ፖል ካጋሜ ፈረንሳይን የሁቱ አስተዳደርን ትደግፋለች፤ በዘር ጭፍጨፋውም እጇ አለበት ብለው ይከሳሉ።

በ2012 ጉዳዩን ከዳኛ ዣን-ልዊስ ብሩጊዬሬ የተረከቡት ሌላ ፈረንሳዊ ዳኛ በሚሳኤል ተኩሱ የሁቱ አክራሪዎች ተጠያቂ ሊሆኑ ይችላሉ ማለታቸውን ተከትሎ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት መሻሻል አሳይቷል።

የፖል ካጋሜ መንግሥት የምርመራ ውጤት የሚያሳየው ሚሳኤሉ የተተኮሰው ከሁቱ ካምፕ እንደነበር ነው።