በጎልፍ ጨዋታ ወቅት የሞቱት ኮሪያውያንና ሌሎች አጫጭር ዜናዎች

የጎልፍ ተጫዋቾች መኪና

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ኢትዮጵያ

• በኢትዮጵያና ኤርትራ ድንበር ከራማ ወደ መረብ የሚወስደው መተላለፊያ መዘጋቱን የመረብ ለኸ ወረዳ አስተዳዳዳሪ አቶ ፅጌ ተስፋይ ለቢቢሲ ገልጹ።

በኢትዮጵያ ድንበር በኩል "ከፌደራል መንግሥት ፈቃድ መያዝ አለባችሁ" የሚል ምላሽ እንተደተሰጣቸውና ከኤርትራ በኩልም የይለፍ ወረቀት እየተዘጋጀ መሆኑን" ቢቢሲ ያናገራቸው ነዋሪዎች ገልፀዋል።

ዴሞክራቲክ ኮንጎ

• የዴሞክራቲክ ኮንጎ የምርጫ ቦርድ የፊታችን እሁድ የሚካሄደውን ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ በኢቦላ በሽታ ወረርሽኝ ምክንያት በአራት ከተሞች አራዝማለው ማለቱ ተቃውሞ አስነሳ።

ውሳኔው የመንግስት ሴራ ነው በማለት ሰልፍ የወጡ ምርጫው የተራዘመባቸው ከተሞች ነዋሪዎች ከፖሊስ ጋር የተጋጩ ሲሆን፤ ፖሊስ አስለቃሽ ጭስ ተጠቅሟል ተብሏል።

ናይጄሪያ

• ናይጄሪያ የቀድሞ የመከላከያ ሚኒስተሯን በመግደል ወንጀል የጠረጠረቻቸውን ሁለት ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ማዋሏን ገለጸች።

የቀድሞው ሚኒስትር ባለፈው ሳምነት ነበር ወደ ቤታቸው ሲመለሱ ባልታወቁ ሰዎች ተተኩሶባቸው ህይወታቸው ያለፈው።

አሜሪካ

• ፕሬዝዳንት ትራምፕና ባለቤታቸው በኢራቅ የአሜሪካ ወታደራዊ ካምፕ ውስጥ ድንገተኛ ጉብኘት አደረጉ።

5000 የሚጠጉ ወታደሮች የሚንቀሳቀሱበት የአል አሳድ የአየር ሃይል ግቢ በከባድ ጥበቃ ስር እንደነበረ ተገልጿል።

ቻይና

• የቀድሞው የቻይና የደህንነት ሃላፊ የነበሩት ማ ጂያን ከሙስና ጋር በተያያዘ የእድሜ ልክ እስራት ተፈረደባቸው።

ሃላፊው ከፈንጆቹ 2015 ጀምሮ ምርመራ እየተደረገባቸው የነበረ ሲሆን፤ ከሃገሪቱ ኮሚዩኒስት ፓርቲም ተወግደዋል።

ታይላንድ

• ሁለት ኮሪያውያን በፈረንጆ የገና በአል ዕለት የጎልፍ ጨዋታ ሲጫወቱ ባጋጠማቸው አደጋ ሰጥመው መሞታቸውን ፖሊስ አስታወቀ።

ወደ ውሃ የተጠጋች ኳሳቸውን ለማምጣት በሄዱበት የሌሎች ተጫዋቾች ተሽከርካሪ ከኋላ ገጭቷቸው ወንዝ ውስጥ እንደገቡ ተገልጿል።

ጀርመን

• ጀርመን የጦር ኃይሏን እንደገና ለማደራጀት በልዩ የሙያ ዘርፎች የተሰማሩ አውሮፓውያንን ልትመለምል እንደምትችል ተገለጸ።

ህክምናና አይቲን በመሳሰሉ ዘርፎች ያለውን የባለሙያ እጥረት ለመቅረፍ በአውሮፓውያኑ 2025 ተጨማሪ 21 ሺህ ብቁ ወታደሮችን ለመልመል አቅዳለች ተብሏል፡፡

ፈረንሳይ

• የ71 ዓመቱ ፈረንሳያዊው አዛውንት በበርሜል ቅርፅ በተሰራ ክብ ጀልባ አትላንቲክን ለማቋረጥ ጉዞ መጀመሩ ተሰምቷል።

ከስፔኗ ደሴት ተነስቶ በሶስት ወር ውስጥ ካሪቢያን ደሴቶች ላይ የመድረስ እቅድ የያዘው ግለሰብ የንፋስ ግፊትን በመጠቀም ነው የሚጓዘው።

• ከከባድ የአየር ንብረት መለዋወጥ ጋር በተያያዘ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች መሞታቸውን ክርስቲያን ኤድ የተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት አስታወቀ።

እስካሁንም ከ10 ቢሊየን ዶላር በላይ ገንዘብ ችግሩን ለመዋጋት እንደዋለ ድርጅቱ ጨምሮ አስታውቋል።