ሊቨርፑል ከአርሴናል፡ ማን ያሸንፋል ብለው ይገምታሉ?

የፎቶው ባለመብት, David Price
የአምናው ባለድል ማንቸስተር ሲቲ ከአራት ጨዋታዎች በሦስቱ ሽንፈት ቀምሷል፤ ሊቨርፑል ማሸነፉን ቀጥሎበታል፤ በፖቸቲኖ የሚመራው ቶተንሃም ሁለተኛ ሥፍራውን ተቆናጦታል፤ ዩናይትድ ደግሞ በሶልሻየር እየተመራ ወደ መነቃቃት የተመለሰ ይመስላል።
እንግሊዞቹ 'ፌስቲቭ ፒሪየድ' እያሉ የሚጠሩት የበዓል ሰሞን ፍልሚያ አሁንም ቀጥሏል።
ቅዳሜ እና እሁድ ከሚደረጉ ጨዋታዎች ሊቨርፑል በአንፊልድ አርሴናልን የሚያስተናግድበት ጨዋታ ይጠበቃል። እንደተለመደው የቢቢሲው ውጤት ገማች ማርክ ላውረንሰን ግምቱን እንዲህ አስቀምጧል።
ቅዳሜ
ብራይተን ከኤቨርተን
ኤቨርተን በርንሌይን 5-1 ረምርሞ፤ ብራይተን ደግሞ ከአርሴናል ጋር በነበረው ፍልሚያ እጅግ አስፈላጊ ነጥብ ተጋርቶ ነው ለዚህ ጨዋታ የሚገናኙት።
የማርኮ ሲልቫ ኤቨርተን የበርንሌይ ሜዳ ላይ ያሳየውን ነፃነት መድገም ከቻለ ያሸንፋል ባይ ነኝ።
ግምት፡ 1 - 2
ፉልሃም ከሃደርስፊልድ
ፉልሃም ከዎልቭስ ጋር ከነበረው ጨዋታ አንድ ነጥብ ማግኘት ችሏል፤ ሃደርስፊልድ ደግሞ ኦልድ ትራፎርድ ላይ ሽንፈት ቀምሷል።
ሁለቱም ቡድኖች የወራጅ ቀጣና ውስጥ የሚገኙ ቢሆኑም ፉልሃም በአሰልጣኝ ክላውዲዮ ራኒዬሪ እየተመራ ይህንን ጨዋታ ይረታል ብዬ አስባለሁ።
ግምት፡ 2- 0
ሌይስተር ከካርዲፍ
የበዓል ሰሞን ጨዋታዎች ከሌይስተር እስካሁን ስድስት ነጥብ ይዘው መጥተዋል፤ ሊያውም ትላልቅ ከሚባሉት ቡድኖች።
ቼልሲን ስታንፎርድ ብሪጅ ላይ፤ በሜዳው ደግሞ ሲቲን መርታት የቻለው የክሎድ ፑዌል ቡድን ከርዲፍን መርታት ያቅተዋል የሚል ስጋት የለኝም።
ግምት፡ 2 - 0

የፎቶው ባለመብት, BBC Sport
ቶተንሃም ከዎልቭስ
11 ጎሎች በሁለት ጨዋታ፤ ቶተንሃም እየገሰገሰ ይገኛል።
እርግጥ ነው ዎልቭስ በዚህ ጨዋታ የተወሰኑ ዕድሎችን ሊፍጥሩ ይችላሉ፤ ነግር ግን ያሸንፋሉ የሚል እምነት የለኝም።
ግምት፡ 2 - 0
ዋትፎርድ ከኒውካስትል
ኒውካስትሎች በሊቨርፑል ደህና ተደርጎ ተቀጥቅጧል።
የቤኒቴዝ ልጆች ዋትፎርድ በኒውካስትል ሜዳ እንደልቡ እንዲፈነጭ እንደማይፈቅዱለት ባስብም ከዚህ ጨዋታ ነጥብ ይዘው ይወጣሉ ብዬ ግን አላስብም።
ግምት፡ 2 - 1

የፎቶው ባለመብት, BBC Sport
ሊርፑል ከአርሴናል
እውነት ለመናገር አሁን ሁለቱም ቡድኖች ያላቸውን አቋም በማየት ማን እንደሚያሸንፍ መገመት አይከብድም።
የኳስ ቁጥጥር በአብላጫው በቀያዮቹ እንደሚያዝ አስባለሁ፤ ይህ ደግሞ በርካታ ዕድሎች እንዲፈጠሩ ክፍተት ይሰጣል።
ሊቨርፑል አርሴናል ላይ ጎል ያስቆጥራል? አዎ! አርሴናል ሊቨርፑል ላይ ጎል ያስቆጥራል? በጭራሽ!
ግምት፡ 2 - 0
እሁድ
ክሪስታል ፓላስ ከቼልሲ
የክሪስታል ፓላስ ችግር ሜዳቸው ላይ ጎል ማስቆጠር አለመቻላቸው ነው፤ ምንም እንኳ በርካታ ዕድሎችን መፍጠር ቢችሉም።
ቼልሲ ከሌይስተር ጋር በነበረው ጨዋታ ባልተጠበቀ ሁኔታ ተረቷል። ነገር ግን ይህንን ጨዋታ ከመርታት ወደኋላ ይላል ብዬ አላስብም።
ግምት፡ 0 - 2
በርንሊ ከዌስትሃም
በርንሊ ውጤታቸው እያሽቆለቆለ እየመጣ ነው። በኤቨርተን 5-1 በገዛ ሜዳቸው የተሸነፉበት ፍልሚያን እንደምሳሌ መውሰድ ይቻላል።
ዌስትሃም ደግሞ በጉዳት ምክንያት የሳሳ ይመስላል። ለዚህ ነው ይህን ጨዋታ በርንሊ ሊያሸንፍ ይችላል ብዬ የምገምተው።
ግምት፡ 2 - 0
ሳውዝሃምፕተን ከሲቲ
የአምናው ባለድል ማንቸስተር ሲቲ ከአራት ጨዋታዎች በሦስቱ ሽንፈት ቀምሷል፤ ለዚያውም ከወገብ በታች በሚገኙ ቡድኖች።
ነገር ግን ለሳውዝሃምፕተን እጁን አሳልፎ ይሰጣል ብዬ አላሳብም።
ግምት፡ 0 - 3

የፎቶው ባለመብት, BBC Sport
ማንቸስተር ዩናይትድ ከበርንመዝ
የዩናይትዱ አዲሱ ጊዜያዊ አሰልጣኝ ከሁለት ጨዋታ ሁለት መርታት ችሏል። ተጨዋቾቹ ብቃት እንዳላቸው አውቃለሁ።
መልካም ጅማሮ አሳይቶ የነበረው በርንመዝ ውጤቱ ማሽቆልቆል ይዟል። ከዚህ ጨዋታም የተሻለ ነጥብ ይዞ ይወጣል ብዬ አልገምትም።
ግምት፡ 2 - 0

• የዩናይትድ ቀጣይ ቋሚ አሰልጣኝ ማን ይሆን?
ሞሪኒሆን የሚተካው የዩናትዶች ቋሚ አሰልጣኝ ማን ይሆን? ፖቼቲኖ? ዚዳን? ወይስ ሲሞኔ?