ብርቅዬ ጦጣ ገድለው የበሉት በቁጥጥር ስር ዋሉ የሚሉና ሌሎች አጫጭር ዜናዎች

ጦጣ

የፎቶው ባለመብት, BARCROFT MEDIA

ናይጄሪያ

• በሰሜን ምስራቃዊ ናይጄሪያ የቦኮ ሃራም ታጣቂዎች ሁለት የመንግስት ወታደራዊ ካምፖችን እንደተቆጣጠሩ ተገለጸ።

ባጋ በተባለችው ከተማ በተሰነዘረው ጥቃት የሟቾች ቁጥር ባይታወቅም፤ የመንግስት ወታደሮች ካምፑን ለማስለቀቅ እየተዋጉ ነው ተብሏል።

ሞዛምቢክ

• ሞዛምቢክ ተማሪዎችን ያበረታታሉ በማለት ነፍሰጡር ሴቶች ከሌሎች ጋር ተቀላቅለው እንዳይማሩ የሚከለክለውን ህጓን አነሳች።

በ2003 በወጣው ህግ መሰረት ነፍሰጡሮች የማታ ትምህርት ብቻ እንዲከታተሉ ነበር የተፈቀደው።

የማደጋስካር

• የቀድሞው የማደጋስካር ፕሬዝዳንት አንድሬይ ራሆሊና በድጋሚ የሃገሪቱ መሪ ሆነው ተመረጡ።

ፕሬዝዳንቱ ተቀናቃኛቸው ራቫሎ ማናናን በመብለጥ 56 በመቶ ድምጽ እንዳገኙ የሀገሪቱ የምርጫ ቦርድ አስታውቋል።

ዴሞክራቲክ ኮንጎ

• በዴሞክራቲክ ኮንጎ እሁድ የሚካሄደውን ምርጫ በአራት ከተሞች መራዘሙን የተቃወሙ ዜጎች በአካባቢው የሚገኝ የኢቦላ ማከሚያ ማእከል ላይ ጥቃት ሰነዘሩ።

የሀገሪቱ የምርጫ ቦርድ በአራቱ ከተሞች የኢቦላ ወረርሽኝ ስጋት አለ በማለት ነበር ምርጫውን እንደሚያራዝመው ያስታወቀው።

ጋና

• ጋናውያን ከብዙ ጭቅጭቅና አለመግባባት በኋላ አዳዲስ ስድስት የአስተዳደር ግዛቶችን ለማቋቋም ህዝበ ውሳኔ አደረጉ።

ህዝበ ውሳኔው በሃገሪቱ ያለውን ያልተመጣጠነ የክልሎች እድገት ለማስተካከል እንደሚረዳ መንግስት አስታውቋል።

አሜሪካ

• የ112 ዓመት ዕድሜ ባለጸጋ የሆኑት በአሜሪካ በእድሜ ትልቁ ሰው ሪቻርድ ኦቨርተን ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ።

ሰውዩው ህይወታቸው ከማለፉ በፊት ዕድሜ ልኬን ሲጋራ ማጨሴ ምንም ጉዳት አላደረሰብኝም ማለታቸው ብዙዎችን አስገርሞ ነበር።

• ታዋቂዋ የሆሊዉድ ፊልም ተዋናይት አንጀሊና ጆሊ ወደፊት ፖለቲካ ውስጥ ልትገባ እንደምትችል ገለጸች።

ተዋናይቷ በአሁኑ ሰአት በተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ልዩ አምባሰደር ሆና በማገልገል ላይ ትገኛለች።

ቬትናም

• በመጥፋት ላይ ያለ የጦጣ ዘር ገድለው ለምግብነት ያዋሉ ስድስት ቬትናማውያን በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋሉ።

ተጠርጣሪዎቹ ጦጣውን ሲገድሉና ሲመገቡ የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል በፌስቡክ ገጻቸው ለቅቀው ነበር ተብሏል።

ሩሲያ

• ሩሲያ ከዩክሬን ጋር በሚያዋስናት ክሬሚያ ድንበር አካባቢ 60 ኪሎሜትር የሚረዝም አጥር ገነባች።

እጅግ የተራቀቀ የጥበቃ መሳሪያ ተገጥሞለታል የተባለው አጥር ማንኛውም አይነት ሰርጎ ገቦችን ለመቆጣጠር ይረዳል ብሏል የሃገሪቱ የደህንነት መስሪያ ቤት።