በምዕራብ ኦሮሚያ ሁለት የፌደራል ፖሊስ አባላት ተገደሉ

በምዕራብ ኦሮሚያ የፌደራል ፖሊስ አባላት ተገደሉ

የፎቶው ባለመብት, Wazema Radio

ሁለት የፌደራል ፖሊስ አባላት በምዕራብ ኦሮሚያ ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ውስጥ መነ ቤኛ ተብሎ በሚጠራ ስፍራ ላይ በጥይት ተመተው መገደላቸውን የአካባቢው ባለስልጣናት ለቢቢሲ ተናገሩ።

የዞኑ የኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ተረፈ፤ የተገደሉት ሁለቱ የፌደራል ፖሊስ አባላት የፊንጫአ ኃይል ማመንጫ እና ጌዶ ከተማ ላይ የሚገኝ የኃይል ማከማቻ ጠባቂዎች ነበሩ ብለዋል።

''መኪና ላይ ሆነው ወደ ፊንጫአ እየተጓዙ ሳሉ ተኩስ ተከፈተባቸው'' በማለት አቶ ደሳለኝ ሁኔታውን ያስረዳሉ።

ጥቃቱን ማን እንደሰነዘረ አልታወቀም የሚሉት አቶ ደሳለኝ የፌደራል ፖሊስ አባላቱ ትናንት እኩለ ቀን ገደማ መገደላቸውን ተናግረዋል።

በምዕራብ ኦሮሚያ አከባቢዎች የጸጥታ መደፍረስ ካጋጠመ ሰንብቷል።

የክልሉ መንግሥት በአከባቢው ለሚደርሱ ጥቃቶች የኦሮሞ ነጻነት ግንባርን ተጠያቂ ያደርጋል። በቅርቡ የኦዲፒ መአከላዊ ኮሚቴ አባል እና የገጠር ፖለቲካ አደረጃጀት ዘርፍ ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ በሰጡት መግለጫ ኦነግ የመንግሥት ባለስልጣናትን ይገድላል፣ የአስተዳደር ስርዓቱን ያፈራርሳል፣ ዘረፋ እና ሚሊሻዎችን ጦር ያስፈታል ሲሉ ኦነግን ከሰዋል።

በሌላ በኩል የኦነግ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ ድርጅታቸው ከመንግሥት ጋር ከስምምነት ላይ የደረሰባቸው ጉዳዮች በመንግሥት እየተጣሱ ነው በማለት ቅሬታቸውን ይናገራሉ።