የዴሞክራቲክ ኮንጎ ምርጫ መጓተት ህዝቡን አስቆጥቷል

መራጮች

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ,

መሪያቸውን ለመምረጥ የተሰለፉ የዴሞክራቲክ ኮንጎ ዜጎች

በዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ ኦፍ ኮንጎ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ መጓተትና በአንዳንድ ቦታዎች ተራዝሟል መባሉ ብዙ የሃገሪቱ ዜጎችን አስቆጥቷል።

ለምርጫው መጓተት በምክንያትነት ከቀረቡት መካከል ደግሞ የምርጫ መቆጣጠሪያው መሳሪያ በትክክል መስራት አለመቻሉ ነው።

ዴሞክራቲክ ሪፓብሊክ ኦፍ ኮንጎ በአውሮፓውያኑ 1960 ነጻነቷን ከገኘች ወዲህ በሰላማዊ መንገድ ስልጣን ለመረካከብ የመጀመሪያው በሆነው ምርጫ የሃገሪቱ ዜጎች ድምጻቸውን ለመስጠት ከትላንት ጠዋት ጀምሮ ተሰልፈው ነበር።

ለ17 ዓመታት ሃገሪቱን የመሩት ፕሬዚዳንት ጆሴፍ ካቢላ ደግሞ ስልጣናቸውን በሰላማዊ መንገድ በመልቀቅ በምርጫው ለሚያሸንፈው ሰው ሥልጣናቸውን የሚያስረክቡ ይሆናል ተብሏል።

የምርጫው ውጤትም በመጪው ሳምንት እንደሚገለጽ ታውቋል።

ፕሬዚዳንታዊ ምርጫው ከሁለት ዓመት በፊት መካሄድ የነበረበት ቢሆንም፤ መንግሥት ለምርጫው መሟላት የነበረባቸው አቅርቦቶች እጥረት አጋጥሞኛል በማለት ነበር ያራዘመው።

በምርጫው ለመሳተፍ ከተመዘገቡት 40 ሚሊዮን ዜጎች በአራት ከተሞች የሚኖሩ 1.26 ሰዎች መምረጥ አይችሉም መባሉ ደግሞ ብዙዎችን ያስቆጣ ሲሆን፤ ነገሮች ተባብሰው ወደ አመጽ ተቀይረው ነበር።

ምንም እንኳን የምርጫ ሂደቱ 11 ሰአት ላይ ቢጠናቀቅም፤ የመምረጥ እድል ያላገኙ ብዙ የሃገሪቱ ዜጎች እስከ ምሽት ድረስ ተሰልፈው ነበር ተብሏል። ይህ ደግሞ የሃገሪቱ ዜጎች ምን ያህል የመምረጥ ፍላጎት እንደነበራቸው ማሳያ ነው ተብሏል።

በጠዋት ሊጀምር የነበረው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫው በከባድ ዝናብ ምክንያት እንዲዘገይ የተገደደ ሲሆን፤ በኪንሻሳ ግዛት ደግሞ የምርጫ ማካሄጃ ማሽኖቹ በጊዜ ባለመቅረባቸው ህዝቡ ቁጣውን እየገለጸ ነበር።

ጉዳዩን ለመከታተል ወደ ቦታው ያቀኑት የሃገሪቱ ምርጫ ኮሚሽን ሃላፊ ኮርኔል ናንጋ ከፍተኛ ተቃውሞ ተሰንዝሮባቸዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው አንዳንድ መራጮች በሂደቱ ደስተኛ ባይሆኑም ለ17 ዓመት ሃገሪቱን የመሩት ፕሬዝዳንት በሰላማዊ መንገድ ስልጣን ለማስረከብ በመወሰናቸውና የዚህ ታሪክ አካል መሆናቸው እንዳስደሰታቸው ገልጸዋል።

''በሃገራችን ለውጥ እንፈልጋለን፤ ሰላምና መረጋጋት ናፍቆናል፤ ብዙ የስራ እድልም ያስፈልገናል።'' በማለት ፊዴል ኢማኒ የተባለ መራጭ አስተያየየቱን ሰጥቷል።

በተለያዩ ያሃገሪቱ ክፍሎች ከጸጥታ ችግር እስከ አስመራⶐች በሰአት አለመገኘት፤ ከኢቦላ ወረርሽኝ ስጋት እስከ ከባድ ዝናብ በፈተኑት ታሪካዊ ምርጫ ምንም አይነት ጉዳት ሳይደርስ መጠናቀቁ ለብዙ የሃገሪቱ ዜጎች እፎይታን የሰጠ ሆኖ አልፏል።

የፎቶው ባለመብት, AFP/Reuters

የምስሉ መግለጫ,

ማርቲን ፋዩሉ፣ ፌሊክስ ሺሰኬዲ ሺሎምቦ እና ኢማኑኤል ራማዛኒ ሻዳሪ

ለፕሬዝዳንትነት የሚፎካከሩት እነማን ናቸው?

ምንም እንኳን 21 እጩዎች ለፕሬዝዳንትነት እየተፎካከሩ ቢሆንም፤ የማሸነፍ እድል ያላቸው ግን ሶስቱ ብቻ ናቸው።

  • ኢማኑኤል ራማዛኒ ሻዳሪ፡ የቀድሞ የሃገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትርና የቀድሞው ፕሬዝዳንት ካቢላ ታማኝ ሰው የነበሩ ሲሆን፤ በ2017 በተካሄዱ ህዝባዊ ተቃውሞዎች ወቅት ከባድ አፈና ፈጽመዋል የሚል ክስ በአውሮፓ ህብረት ቀርቦባቸዋል።
  • ማርቲን ፋዩሉ፡ የሃገሪቱ የነዳጅ ጉዳዮች ዋና ሃለፊ ሆነው አገልግለው ነበር። በቅስቀሳቸው ወቅትም የበለጸገች ኮንጎ ስለመፍጠር ይናገሩ ነበር።
  • ፌሊክስ ሺሰኬዲ ሺሎምቦ፡ የቀድሞው የተቃዋሚ መሪ ልጅ ሲሆኑ፤ ድህነትን ከሃገሪቱ ማጥፋት የመጀመሪያ ስራቸው እንደሆነ ተናግረዋል።

በጸጥታ ችግርና በኢቦላ ወረርሽኝ ምክንያት ምርጫው አይካሄድባቸውም በተባሉ ከተሞች የሚኖሩ ዜጎች ደግሞ የራሳቸውን የምርጫ ወረቀት በማዘጋጀት በሃገሪቱ ምርጫ ኮሚሽን እውቅና ያልተሰጠው ምርጫ ሲያካሂዱ እንደዋሉ ተገልጿል።