አራት ህጻናትን በአንዴ ያገኘው ቤተሰብ ተጨንቋል

የተወለዱት ህጻናት

የፎቶው ባለመብት, በሰሜን ወሎ ዞን የራያ ቆቦ ወረዳ ኮሙኒኬሽን

ከዚህ በፊት የአንድ ልጅ እናት የነበሩት ወይዘሮ እቴናት ሲሳይ ባለፈው አርብ ምሽት ምጥ ጀምሯቸው ቅዳሜ ጠዋት ወደ ሃኪም ቤት ተወስደው አራቱን ልጆቻቸውን ተገላግለዋል።

አቶ ፈንታ ሰገድ ለቢቢሲ እንደተናገሩት ባለቤታቸው ከወራት በፊት የእርግዝና ክትትል ሲያደርጉ በአካባቢያቸው ባሉ ባለሙያዎች እርግዝናቸው መንታ ሊሆን እንደሚችል ተነግሯቸው እንደነበር አስታውሰዋል።

ባለፈው አርብ እኩለ ሌሊት አካባቢ ምጥ የጀመራቸው እናት ቅዳሜ ጠዋት ወደ ቆቦ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ተወስደው እንዲወልዱ ሲደረግ የህክምና ባለሙያዎቹ ጭምር አራት ልጆች ይወልዳሉ ብለው አልጠበቁም ነበር።

ወይዘሮ እቴናት ወደ ሆስፒታሉ ከመጡ በኋላ በባለሙያዎች ድጋፍ ያለችግር በተፈጥሯዊ መንገድ አራቱን ልጆች ተገላግለዋል። እናትየውና ሦስቱ ህፃናት በመልካም ጤንነት ላይ ሲሆኑ፤ አንደኛው ጨቅላ ግን የህክምና ክትትል የሚያስፈልገው እንደሆነ በሃኪሞች እንደተነገራቸው አባትየው አቶ ፈንታ ተናግረዋል።

በአንድ ጊዜ ሦስት ሴቶችና የአንድ ወንድ ልጅ አባት የሆኑት አርሷደር ፈንታ ሰገድ ተጨማሪ የህክምና ክትትል ከሚያስፈልገው አንደኛው ጨቅላ በተጨማሪ ልጆቹንና እናትየውን ለመንከባከብ ያላቸው አቅም ስለማይፈቅድላቸው እጅጉን እንደተጨነቁ ይናገራሉ።

ህጻናቱ ቅዳሜ ዕለት የተወለዱበት የቆቦ ሆስፒታል ተወካይ ሥራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ካሳሁን አዲሱ እንደሚሉት ከተወለዱት ህጻናት መካከል ሦስቱ ሴቶች በጥሩ ጤንነት ላይ የሚገኙ ሲሆን፤ አንደኛው ልጅ ግን ህክምና እየተከታተለ ነው።

ችግሩ የሆድ እቃዎቹ ሽፋን አለመኖር /ኢምፕሎሲ/ እነደሆነ በህክምና ስለተረጋገጠ ወደ ተሻለ ሆስፒታል ሄዶ በስፔሻሊሰት ሃኪሞች መታየት አለበት ብለዋል።

ነገር ግን ይላሉ አቶ ካሳሁን፤ ቤተሰቡ ወደሌላ ቦታ ሄዶ ህክምና ለማድረግ አይደለም እናትየውንና ጨቅላዎቹን ለመንከባበከብ የሚሆን ገንዘብ ስለሌለው ሁኔታው በጣም አስቸጋሪ ነው።

ልጆቹ ከተወለዱ በኋላ እናትየው ምንም አይነት የጤና ችግር እንዳላገጠማትና አሁን በጥሩ ሁኔታ ላይ እንደምትገኝም ባለሙያዎቹ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

እናትየው ከወሊድ በፊት ክትትላቸውን በሆስፒታሉ ባለማድረጋቸው ቤተሰቡ አራት ልጅ እንደሚወለድ አያውቅም ነበር፤ ይህ ደግሞ ያልታሰበ ዱብዳ እንዲሆንባቸው አድርጓል ብለውናል ተወካይ ሥራ አስኪያጁ።

የፎቶው ባለመብት, በሰሜን ወሎ ዞን የራያ ቆቦ ወረዳ ኮሙኒኬሽን

የራያ ቆቦ ወረዳ የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ተወካይ ሃላፊ የሆኑት አቶ ዝናቤ እያሱ በበኩላቸው ቤተሰቡ አራቱን ልጆች ለማሳደግ አቅም የሌለው ሲሆን፤ ወደፊት ልጆቹ የሚፈልጉትን ነገር በሙሉ ሟሟላት አስቸጋሪ ሊሆንባቸው ይችላል ይላሉ።

በአሁኑ ሰአት ልጆቹን ማጥባትና እናትየውን መንከባከብ በራሱ በግብርና ሥራ ለሚተዳደረው ቤተሰብ አዳጋች እንደሆነ አቶ ዝናቤ ነግረውናል።

ቤተሰቡን ለመርዳት እስካሁን የአካባቢው ነዋሪዎች መዋጮ እያደረጉ እንደሆነና የወረዳው አስተዳደር ቢሮም አቅሙ ያላቸው ሰዎች ለቤተሰቡ የቻሉትን እርዳታ እንዲያደርጉ ለማስተባበር ጥረት እያደረገ ነው።

ከዚህ በተጨማሪ በቆቦ የሚገኝ 'ካቶሊክ' የተባለ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ለህጻናቱ አልባሳትና ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችን ለማሟላት እንዲሁም በወር 500 ብር ለመስጠት ቃል እንደገባም ተናግረዋል።

''ከተወለዱት አራት ህጻናት መካከል አንዱ የጤና ሁኔታው ጥሩ ስላልሆነ የተሻለ ቦታ ተወስዶ ህክምና ማግኘት የሚችልበትን ሁኔታ ለማመቻቸትም እየሰራን ነው'' ብለዋል አቶ ዝናቤ።

''ችግሩ የተለመደና ተገቢውን ህክምና ካገኘ ህጻኑ ወደ ሙሉ ጤንነቱ እንደሚመለስ ከሆስፒታሉ ስለተነገረን ይህንን ለማሳካት እየተሯሯጥን ነው'' ሲሉ ያሉበትን ሁኔታ ያስረዳሉ።

ምንም እንኳን አራት ህጻነት በአንድ ጊዜ ማግኘታቸውን እንደ ጸጋ ቢመለከቱትም፤ አቶ ፈንታ ግን ልጆቹን እንዴት እንደሚያሳድጉ ሲያስቡ ከባድ ፈተና እነደሚሆንባቸው ያምናሉ።

ከቤተሰቦቻቸው ባገኟት ትንሽ መሬት ላይ እርሻ በማረስ ለሚተዳደሩት ባልና ሚስት ይህ ክስተት ከጥሩ ዜናነቱ ይልቅ አሳሳቢነቱ ጎልቶ ታይቷቸዋል።