የትራምፕ አማካሪ፡ የሜክሲኮ ግንብ ውጥን ውድቅ ከተደረገ ሰነባብቷል

የትራምፕ አማካሪ፡ የሜክሲኮ ግንብ ኃሳብ ውድቅ ከተደረገ ሰነባብቷል

የፎቶው ባለመብት, Reuters

በአሜሪካ እና ሜክሲኮ ድንበር ላይ ይገነባል ተብሎ የነበረው የኮንክሪት ግንብ ሃሳብ ውድቅ የተደረገው በትራምፕ የመጀመሪያዎቹ የፕሬዚዳንትነት ወራቶች ነው ሲሉ በቅርቡ ከሥራቸው የሚሰናበቱት የፕሬዚዳንቱ አማካሪ ተናገሩ።

ዶናልድ ትራምፕ ከምርጫ ቅስቃሳቸው ጀምሮ በሁለቱ ሃገራት አዋሳኝ ድንበር ላይ የኮንክሪት ግንብ ማቆም ስደተኞችን ለመግታት ሁነኛ አማራጭ ነው ይሉ ነበር።

የትራምፕ አማካሪ ጆን ኬሊይ አስተያየት ግን ከፕሬዚዳንት ትራምፕ ጋር ይቃረናል።

ትራምፕ በዚህ ወር ብቻ በትዊተር ገጻቸው ላይ ''ግንብ'' የሚለውን ቃለ ከ59 ጊዜያት በላይ ተጠቅመውታል።

ተሰናባቹ የትራምፕ አማካሪ ጆን ኬሊይ ምን አሉ?

ፕሬዚዳንት ትራምፕን ለ17 ወራት ሲያማክሩ የቆዩት ተሰናባቹ አማካሪ ለኤልኤ ታይምስ በሰጡት ቃል፤ ከሜክሲኮ ወደ አሜሪካ የሚሻገሩ ስደተኞችን ለመቆጣጠር የትራምፕ አስተዳደር ከሚመለከታቸው ባለሙያዎች ምክርን ተቀብሎ ነበር።

''ባለሙያዎቹ ያሉት፤ 'አዎን በአንዳንድ ቦታዎች የሰዎችን እንቅስቃሴ የሚገድቡ አጥሮች ያስፈልጉናል። ቴክኖሎጂ እና በርከት ያለ የሰው ኃይል ነው የሚያስፈልገው ነው።'' ብለዋል ተሰናባቹ የፕሬዚዳንቱ አማካሪ።

''ፕሬዚዳንቱ አሁንም ስለ ''ኮንክሪት ግንብ'' ነው የሚያወሩት። ወዲፈት ግን ''የብረት አጥር'' የሚለውን ሃረግ መጠቀም ይጀምራሉ። አስተዳደሩ የኮንክሪት ግንብ ሃሳብን ውድቅ ካደረገው ወራት ተቆጥረዋል'' በማለት አስረግጠዋል።

ትራምፕ ምን ብለው ነበር?

''ግዙፍ ግንብ እገነባለሁ፤ ማንም ሰው ከእኔ የተሻለ ግንብ መገንባት አይችልም። እመኑኝ። ከሜክሲኮ በሚያዋስነው ደቡባዊው ድንበር ላይ እጅግ ግዙፍ የሆነ ግንብ፤ በጣም አነስተኛ በሆነ ወጪ እገነባለሁ። የግንቡን ግንባታ ወጪ ሜክሲኮ እንድትሸፍን አደርጋለሁ።''

ይህን ያሉት ፕሬዚዳንት ትራምፕ ከሶስት ዓመት ገደማ በፊት የምርጫ ቅስቀሳቸውን ባስጀመሩበት ጊዜ ነበር።

በጊዜ ሂደት ግን ትራምፕ በግንቡ ግንባታ ላይ ያላቸውን አቋም እያለሰለሱ መጥተዋል። መስከረም ላይ ይገነባል ተብሎ የነበረው ግንብ ሙሉ ለሙሉ የኮንክሪት ሳይሆን የብረት ወይም የሽቦ አጥርን እንደሚጨምር ተናግረዋል።

ፕሬዚዳንት ትራምፕ የኮንክሪት ግንቡንም ይሁን የብረት አጥሩን ለማስጀመር የሚያስችላቸውን በጀት ማግኘት አልቻሉም። ኮንግረሱ የግንቡን ግንባታ የካተተ የፍይናንስ ፍቃድ ለመስጠት ፍቃደኛ አልሆነም።

ይህን ተከትሎም የትራምፕ አስተዳደር ለግንቡ ወይም ለአጥሩ ግንባታ በጀት እንዲያስገኝላቸው በማሰብ በሰሞኑ የበዓላት ወቅት አንዳንድ የአሜሪካ መስሪያ ቤቶች አገልግሎት መስጠት እንዲያቆሙ አስደርገዋል።

ይህም ብቻ አይደልም፤ ትራምፕ የጠየቁት በጀት የማይጸድቅ ከሆነ ከሜክሲኮ ጋር የሚያዋስነውን ድንበር እንደሚዘጉ አስጠንቅቀዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱን መቀመጫ አብላጫ ቁጥር የያዙት ዲሞክራቶች እንደመሆናቸው መጠን ትራምፕ የጠየቁትን በጀት የማግኘታቸው ነገር አጠያያቂ ነው ተብሏል።