እንግሊዝ እና ፈረንሳይ ስደተኞችን ለመቆጣጠር የጋራ ቡድን አቋቋሙ

የድንበር ጠባቂዎች ጀልባ

የፎቶው ባለመብት, PA

እንግሊዝ እና ፈረንሳይ ስደተኞች አነስተኛ ጀልባዎችን በመጠቀም ወደ እንግሊዝ ለመግባት የሚያደርጉትን ጥረት ለመቆጣጠር የጋራ ቡድን ለማቋቋም ተስማሙ።

የእንግሊዝ የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚንስትሩ ከፈረንሳዩ አቻቸው ጋር በስልክ ውይይት ካደረጉ በኋላ ከዚህ ስምምነት ላይ መድረሳቸው ተነግሯል።

እሁድ ጠዋት ስድስት የኢራን ዜጎች አነስተኛ ጀልባ በመጠቀም ወደ እንግሊዝ ሊገቡ ሲሉ ዶቨር በተሰኘ የባህር ዳርቻ አቅራቢያ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውም ተዘግቧል።

የእንግሊዝ ባለስልጣናት እንደሚሉት ከሆነ የፈረንሳይ የጸጥታ ኃይል አባላት ቁጥጥር ባያደርጉ ኖሮ እሁድ ምሽት ላይ በርካታ ስደተኞች ወደ እንግሊዝ ለመሻገር ጥረት አድረገው ነበር።

የእንግሊዝ የሃገር ውስጥ ጉዳዮች ሚንስትር ጃቪድ ከፈረንሳዩ አቻቸው ጋር በስልክ ከተወያዩ በኋላ ''የተጠናከረና በፍጥነት ተግባራዊ ሊደረግ የሚችል ዕቅድ አውጥተናል'' ብለዋል።

ባለፉት ሁለት ወራት ከ220 በላይ ስደተኞች አነስተኛ ጀልባ በመጠቀም ወደ እንግሊዝ ዘልቆ ለመግባት ሙከራ አድረገዋል።

የፎቶው ባለመብት, Lewis Morris

በአነስተኛ ጀልባ በሕገ-ወጥ መንገድ ወደ እንግሊዝ ለመግባት ጥረት ከሚያደርጉት ይበልጥ ደግሞ በሕጋዊ መንገድ ከገቡ በኋላ ጥገግኝነት የሚጠይቁ ሰዎች ቁጥር ከፍ ያለ እንደሆነ ባለስልጣናቱ ይናገራሉ።

እ.አ.አ. በ2017 በእንግሊዝ 26,350 ሰዎች ጥገኝነት የጠየቁ ሲሆን፤ ይህም ማለት በአማካይ በአንድ ወር 2200 ሰዎች ማለት ነው።

ወደ እንግሊዝ በሕገ-ወጥ መንግድ ለመግባት ጥረት ከሚያደርጉ ስደተኞች መካከል አብዛኛውን ቁጥር የሚይዙት ኢራናውያን እና ሶሪያዊያን ናቸው።