በኔፓል እናትና ልጇቿ ለወር አበባ በተገለለ ጎጆ ህይወታቸው አለፈ

የወር አበባ የሚያዩ ሴቶች ከሚገለሉበት ጎጆዎች አንዱ Image copyright AFP

ኔፓላዊት እናትና ሁለት ልጆቿ ለወር አበባ በተከለለ ጎጆ ውስጥ ጭስ አፍኗቸው ህይወታቸው እንዳለፈ ተዘግቧል።

በኔፓል ሴት ልጅ የወር አበባ በምታይበት ወቅት ከሰው ተገልላ በተከለለ ጎጆ ውስጥ መቀመጥ አለባት።

ይህንንም ተከትሎ አንዲት እናት ከሁለት ልጆቿ ጋር በተከለለ ጎጆ ውስጥ ሆነው የክረምቱን ቅዝቃዜ መቋቋም ስላልቻሉ እሳት አቀጣጠሉ።

'የወር አበባ ላይ ስለነበርኩ ለአያቴ ሐዘን መቀመጥ አልቻልኩም'

የወር አበባ ለምን በአንዳንድ ሴቶች ላይ ህመም ያስከትላል?

በነጋታውም ሶስቱም ሞተው የተገኙ ሲሆን፤ በጭስ ታፍነው ሳይሞቱ እንዳልቀሩም የአካባቢው ባለስልጣናት ለቢቢሲ ኔፓሊ ገልፀዋል።

በባህሉ መሰረት ሴት የወር አበባ በምታይበት ወቅት በተገለለ ቦታ ማስቀመጥ በኔፓል የታገደ ቢሆንም አሁንም ቢሆን በገጠሪቷ ክልል መከናወኑ አልቀረም።

ይህ አሳዛኝ ሁኔታ የመጀመሪያ አይደለም ከዚህ ቀደምም ታፍና እንዲሁም በእባብ ተነድፈው የሞቱ ሴቶችም ይገኙበታል።

ይህንንም ተከትሎ ነበር ከሁለት አመት በፊት አግልሎ ማስቀመጥ ወንጀል እንዲሆን የተደረገው።

በዚህም መሰረት የሶስት ወር እስራትና 810 ብር ቅጣትም ያስከትላል።

በጥንታዊ ሂንዱይዝም እምነት መሰረት የወር አበባ እያዩ ያሉ ሴቶችና የወለዱ ሴቶች ቆሻሻ ተደርገው ከመታየት በተጨማሪ መጥፎ እድል ያመጣሉ ተብለው ስለሚታመኑ ለብቻቸው በተከለለ ጎጆ ወይም በእንስሳት በረት እንዲቆዩ ይገደዳሉ።

ከብቶችንና ሰዎችን መንካት የማይፈቀድላቸው ሲሆን ከዚህም በተጨማሪ የተወሰኑ ምግቦች ይከለከላሉ፤ በቤት ውስጥ የሚገኙ መታጠቢያ ቤትና ልብስ ማጠቢያ ቦታ ስለማይፈቀድላቸው ረዥም መንገድ መጓዝ አለባቸው።

ጥበብን በወር-አበባና በአጽም

ሴት ተማሪዎችም ወደ ትምህርት ቤት ከመሄድ ይታቀባሉ።

ለከፍተኛ ቁር መጋለጥ፣ የወንጀለኞች ጥቃት ከሚደርሱባቸው መካከል የተወሰኑት ናቸው።

በቅርብ የሞቱት እናትና ልጆችን አሟሟት ምርመራ እየተደረገ ነው።

እናቲቱ ለብሳው የነበረው ብርድ ልብስ በከፊል የተቃጠለ ሲሆን እግሯም ላይ ቃጠሎ እንደደረሰባትም ኤኤፍፒ ፖሊስን ጠቅሶ ዘግቧል።

ልጆቹም የ12ና ዘጠኝ አመት ዕድሜ ያላቸው ሲሆን አስከሬናቸውም ለቤተሰቦቻቸው ተመልሷል።