ትራምፕ፡ ቱርክ በኩርድ ታጣቂዎች ላይ ጥቃት ከፈጸመች ኢኮኖሚዋ እንዳልነበር ይሆናል

ትራምፕ ቱርክ በኩርድ ታጣቂዎች ላይ ጥቃት ከፈጸመች ኢኮኖሚዋ እንዳልነበር ይሆናል ብለዋል Image copyright EPA

አሜሪካ ጦሯን ከሶሪያ የማስወጣት ያላትን ዕቅድ ተከትሎ ቱርክ በሶሪያ የሚንቀሳቀሱ የኩርድ ታጣቂዎች ላይ ጥቃት ብትሰነዝር ከፍተኛ የኢኮኖሚ ውድቀት ያጋጥማታል ሲሉ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ የቱርክ መንግሥትን አስጠነቀቁ።

ትራምፕ እሁድ ዕለት በትዊተር ገጻቸው ላይ የኩርድ ታጣቂዎችም ቢሆኑ ከቱርክ መንግሥት ጋር እሰጣ ገባ ውስጥ እንዳይገቡ አስጠንቅቀዋል።

የአሜሪካ ጦር ከኩርድ ሚሊሻዎች ጋር በመጣመር በሶሪያ የሚንቀሳቀሰውን ኢስላሚክ ስቴት (አይኤስ) ሲወጋ ከርሟል።

የሳዑዲው ጋዜጠኛ ለመገደሉ ቱርክ አሳማኝ ማስረጃ እንድታቀርብ አሜሪካ ጠየቀች

በሶሪያ ግጭት የቱርክ ኃይሎች ላይ ከባድ ጥቃት ተሰነዘረ

«ካሾግጂ ወዲያው ነበር የታነቀው» ቱርክ

ቱርክ በበኩሏ የኩርድ ሚሊሻ ስብስብን አሸባሪ ስትል ፈርጃለች።

የቱርኩ ፕሬዚዳንት ረሲፕ ታየር ኤርዶጋን አሜሪካ ለኩርድ ታጣቂዎች የምታደርገውን ድጋፍ አምረረው ይቃወማሉ። ኤርዶጋን ከዚህ ቀደም የአሜሪካንን ድጋፍ ለማስቆም የተቻላቸውን ሁሉ እንደሚያደርጉ ተናግረው ነበር።

ትራምፕ በትዊተር ገጻቸው ላይ ጨምረው እንዳሰፈሩት አሜሪካ በሶሪያ ውስጥ በነበራት ተሳትፎ፤ ሩሲያ፣ ኢራን እና ሶሪያ ተጠቃሚዎች ሆኖዋል ብለዋል።

ትራምፕ የአሜሪካ ጦርን ከሶሪያ የማስወጣት እቅዳቸውን ከአንድ ወር በፊት ይፋ ባደረጉበት ወቅት ከአጋር ሀገሮች ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሟቸው ነበር።

በመካከለኛው ምስራቅ ይፋዊ የሥራ ጉብኝነት እያደረጉ የሚገኙት የአሜሪካው የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ማይክ ፖምፔዎ፤ ከቱርክ አቻቸው ጋር በስልክ እንደተወያዩ ተናግረው፤ ለኩርድ ታጣቂዎች ከለላ ለመስጠት ከቱርክ መንግሥት ጋር ስምምነት ላይ ሊደረስ እንደሚቻል ተናግረዋል።

Image copyright Reuters
አጭር የምስል መግለጫ የአሜሪካው የውጪ ጉዳይ ሚንስትር ማይክ ፖምፔዎ እና የሳዑዲው አቻቸው አደል አል-ጁቤር ሪያድ ሳዐዲ

ፖምፔዎ አቡ ዳቢ ላይ ለጋዜጠኞች ሲናገሩ የቱርክ ሕዝብ እና ኤርዶጋን ሃገራቸውን ከአሸባሪዎች የመከላከል መብታቸውን የአሜሪካ መንግሥት ያከብራል ሆኖም ግን ከአሜሪካ ጎን ሆነው ሲፋለሙ የነበሩ ታጣቂዎች ጥበቃ ሊደረግላቸው ይገባል ብለዋል።

አሜሪካ ወደ ሰሜናዊ ሶሪያ ወደ 2ሺህ የሚጠጉ ወታደሮችን ማሰማራቷ ይነገራል። የቀድሞ የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ከአራት ዓመታት በፊት ለኩርድ ታጣቂዎች ስልጠና የሚሰጡ ልዩ ኃይል ወደ ሶሪያ ልከው ነበር።

ባለፉት ዓመታት በሶሪያ የተሰማራ የአሜሪካ ጦር ቁጥር በፍጥነት ጨምሯል።