ለወሲብ ትክክለኛው ዕድሜ የቱ ነው?

አብዛኛዎቹ ወሲብ የጀመሩት 18 ዓመት ሳይሞላቸው ሲሆን የተቀሩት ደግሞ በ16 ዓመታቸውን ነው
አጭር የምስል መግለጫ አብዛኛዎቹ ወሲብ የጀመሩት 18 ዓመት ሳይሞላቸው ሲሆን የተቀሩት ደግሞ በ16 ዓመታቸውን ነው

እንግሊዝ ውስጥ ስለ ግብረ ሥጋ ግንኙነት የተሠራ ጥናት እንደሚያሳየው፤ በለጋ ዕድሜያቸው ድንግልናቸውን ያጡ ወጣቶች የኋላ ኋላ ይቆጫሉ።

በጥናቱ ከተሳተፉት በአፍላ ዕድሜ የሚገኙ አንድ ሦስተኛ ሴቶችና አንድ አራተኛ ወንዶች፤ ለመጀመሪያ ጊዜ ወሲብ የፈጸሙት በትክክለኛው ዕድሜ እንዳልነበር ይናገራሉ።

በእንግሊዝ ሕግ መሠረት በፍቃደኝነት ላይ የተመሰረት ወሲብ መፈጸም የሚቻለው ጥንዶቹ 16 እና ከዚያ በላይ ሲሆኑ ብቻ ነው።

በየአሥር ዓመቱ የሚከናወን ጥናት ግን በዚህም ዕድሜ ለወሲብ ዝግጁ መሆን አይቻልም ይላል።

ውጤቱ በቅርቡ ይፋ ለተደረገው ጥናት መረጃ የተሰበሰበው ከ3000 ወጣቶች ሲሆን፤ እ.አ.አ ከ2010 እስከ 2012 ባለው ጊዜ ለንደን ባሉ ሳይንቲስቶች የተሰራ ነው።

የጥናቱ ውጤቱ

ከጥናቱ ተሳታፊዎች 40% የሚሆኑት ሴቶችና 26% የሚሆኑት ወንዶች ለመጀመሪያ ጊዜ ወሲብ ሲፈፅሙ በተገቢው ዕድሜ ላይ እንዳልነበር ተናግረዋል። ተሳታፊዎቹ ትንሽ ዘግይተው ቢሆን ኖሮ ደስ ይላቸው እንደነበረም ገልፀዋል።

አብዛኛዎቹ ወሲብ ማድረግ የጀመሩት 18 ዓመት ሳይሞላቸው ሲሆን፤ ቢያንስ አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት ደግሞ 16 ዓመት ሳይሞላቸው የግብረ ሥጋ ግንኙነት አድርገዋል።

ፈቃደኝነት

ጥናቱ ግብረ ሥጋ ግንኙነት የማድረግ አቅምና ዝግጁነትንም ጭምር ተመለከተ ነው። ማለትም አንድ ሰው አመዛዝኖ፣ በእውቀት ላይ የተመሠረተ ውሳኔ ማድረግ ይችላል ወይ? የሚለው ከግምት ገብቷል።

የማመዛዘን ብቃት ሲለካ፤ ከአሥር ሴቶች መካከል ከግማሽ በላይ የሚሆኑትና ከወንዶቹ ደግሞ አራቱ ሳይልፉ ቀርተዋል።

ከአምስት ሴቶች አንዷና ከአስር ወንደች አንዱ ለመጀመሪያ ጊዜ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ያደረጉት ብዙም ፈቃደኛ ሳይሆኑና በፍቅረኛቸው ተገፋፍተው እንደነበረ ይናገራሉ።

የ'ናትሳል' ጥናት መሥራች የሆኑት ፕሮፌሰር ካዬ ዌሊንግስ እንደሚሉት፤ ለግብረ ሥጋ ግንኙነት ሕጋዊ ተብሎ የተቀመጠው ዕድሜ አንድ ሰው ለግብረ ሥጋ ግንኙነት ዝግጁ ወይም ብቁ ነው ማለት አይደለም ይላሉ።

"ሁሉም ወጣት የተለያ ነው። አንዳንድ የ15 ዓመት ወጣቶች ዝግጁ ቢሆኑም አንዳንዶች ደግሞ በ18 ዓመታቸው ብቻ ዝግጁ እንደሆኑ ሊሰማቸው ይችለላል"

ሌላዋ አጥኚ ዶ/ር ሜሊሳ ፓልመር፤ "ግኝታችን እንደሚያሳየው አብዛኛውን ጊዜ ሴቶች ከወንዶች በበለጠ በፍቅረኛቸው ግፊት የግብረ ሥጋ ግንኙነት ማድረጋቸውን ነው" ይላሉ።

በጥናቱ መሰረት፤ ከአሥር ወጣቶች ዘጠኙ መከላከያ ቢጠቀሙም፤ "ለወደፊትም ወጣቶች ከበሽታ እንዲጠበቁ ለጤናቸው ትኩረት መሰጠት አለበት" ብለዋል።

በተጨማሪም የወጣቶች የመጀመሪያ የግብረ ሥጋ ግንኙነት ጤናማ እንዲሆን ትምህርት ቤቶች ተገቢውን የጤና ጥበቃ አገልግሎት እንዲሁም ትምህርት መስጠት አለባቸው ብለዋል።

የግብረ ሥጋ ግንኙነት ማድረግ ያለብን መቼ ነው?

የግብረ ሥጋ ግንኙነት ሊያደርጉ ከሆነ ለራስ እነዚህን ጥያቄዎች መሰንዘር ያሻል፡

  • የሚሰማኝ ትክክለኛ ስሜት ነው?
  • አብሬው ከምተኛው ሰው ፍቅር ይዞኛል?
  • ያፈቅረኛል/ታፈቅረኛለች?
  • ከኤችአይቪና ሌሎችም ተላላፊ በሽታዎች ራሳችንን ለመከላከል ኮንዶም ስለመጠቀም ተነጋግረናል?
  • ካልተፈለገ እርግዝና ለመጠበቅ የወሊድ መከላከያ አዘጋጅተናል?
  • ሃሳቤን መቀየር ብፈልግ በማንኛውም ሰዓት እምቢ የማለት አቅም አለኝ? ፍቅረኛዬስ ይህን ውሳኔ ያከብራል?

ለእነዚህ ጥያቄዎች ምላሹ አዎ ከሆነ ወሲብ ለመፈጸም ትክክለኛው ጊዜ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ከዚህ በታች ላሉት ጥያቄዎች መልሱ አዎ ከሆነ ትክክለኛው ጊዜ ላይሆን ይችላል፡

  • ከጓደኞቼ ወይም ከፍቅረኛዬ ግፊት እየተሰማኝ ነው?
  • በኃላ ሊቆጨኝ ይችላል?
  • አሁን ወሲብ ማድረግ የፈለኩት ከጓደኞቼ እኩል ለመሆን ወይም እነሱን ለማስደሰት ነው?
  • ግንኙነት ለማድረግ ፈቃደኛ የሆንኩት ከፍቅረኛ ጋር ላለመለያየት ብዬ ነው?

ኢዛቤል ኢንማን ስለ ወሲብ ትምህርት በሚሰጥ መጽሐፍ ይህን ብለዋል፡

"ወሲብ ለመፈጸም ተገቢ ስለሆነው ዕድሜና ጊዜ ለወጣቶች ትምህርት መሰጠት አለበት። ሲያድጉ የሚበጃቸው ውሳኔ ላይ ለመድረስ አይቸገሩም። ትምህርቱ በትምህርት ቤቶች መሰጠት ቢጀመርም ጠቃሚ ነው።"

ተያያዥ ርዕሶች