ከናይሮቢው የሽብር ጥቃት ጋር በተገናኘ 9 ሰዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

ከናይሮቢው የሽብር ጥቃቱ ጋር በተገናኘ 9 ሰዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ Image copyright Reuters

21 ሰዎች ከተገደሉበት የናይሮቢው የሽብር ጥቃት ጋር በተገናኘ 9 ሰዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ።

የኬንያ ፖሊስ አምስቱን አሸባሪዎች ገድሎ የዱሲትዲ2ናይሮቢ ህንጻን ለመቆጣጠር የ19 ሰዓታት ኦፕሬሽን ማካሄድ ነበረበት። ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ፤ ''አሸባሪዎቹ በሙሉ ተገድለዋል፤ ኦፕሬሽኑም ተጠናቋል'' ሲሉ አሳውቀል።

ፖሊስ እንዳስታወቀው፤ የሽብር ጥቃቱን በማቀነባበር እና በገንዘብ የደገፉ ግለሰቦችን ማደኑን ተያይዞታል።

አል ሸባብ ኃላፊነቱን እወስዳለሁ ባለው የሽብር ጥቃት የሟቾች ቁጥር 21 መድረሱ ይታወሳል።

ከሽብር ጥቃቱ በኋላ ምን ተከሰተ?

ስለ ጥቃት አድራሾቹ ምን እናውቃለን?

የኬንያ መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት፤ ከጥቃት አድራሾቹ መካከል የአንደኛው ታጣቂ ሚስት ኪያምቡ ተብሎ በሚጠራው ግዛት ውስጥ በቁጥጥር ሥር ውላለች።

ጥቃት አድራሾቹ ወደ ሆቴሉ የመጡበት መኪና የአንደኛውን አሸባሪ ማንነት እንድለይ ረድቶኛል ሲል ፖሊስ አስታውቋል።

መኪናዋ ከሆቴሉ አቅራቢያ ቆማ በቴሌቪዥን መስኮት የተመለከቱ ነዋሪዎች ለፖሊስ ስለመኪናዋ ባደረሱት ጥቆማ ከጥቃት አድራሾቹ መካከል እንዱ አሊ ሳሊም ጊቹንጌ መሆኑ ታውቋል።

የአሊ ሳሊም ጊቹንጌ ጎረቤቶች 'ዘ ስታንዳርድ' ለተሰኘ ጋዜጣ በሰጡት ቃል፤ ጥቃት አድራሹ እና ባለቤቱ ከጥቂት ወራት በፊት በስፍራው መኖር መጀመራቸውን እና ሚስጥራዊ መሆናቸውን ተናግረዋል።

ጎረቤቶቹ ጨምረውም 'በዚህ ሳምንት ከናይሮቢ ልንወጣ ነው' በማለት የቤት እቃዎቻቸውን ለሽያጭ አቅርበው ነበረ ብለዋል።

ከሽብር ጥቃቱ በኋላ ምን ተከሰተ?

ሮይተርስ እንደዘገበው፤ አል ሸባብ "ይህን ጥቃት የሰነዘርኩት ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ እየሩሳሌምን የእስራኤል ዋና ከተማ አድርገው በመቁጠራቸው ምላሽ እንዲሆን ነው" ብሏል።

በጥቃቱ ከተገደሉት 21 ሰዎች መካከል የፖሊስ አባል እንደሚገኝበትም ታውቋል።

የሽብር ጥቃቱ ማክሰኞ ከሰዓት 9 ሰዓት ገደማ ነበር የጀመረው። ፖሊስ እንደሚለው ታጣቂዎቹ ወደ ሆቴሉ እንደተቃረቡ ወደ መኪና ማቆሚያ ስፍራ የእጅ ቦንቦችን ወረወሩ፤ ከዚያም አንዱ ታጣቂ እራሱን አፈነዳ።

የሲሲቲቪ ካሜራ ምስሎች አራት ታጣቂዎች ተኩስ ሲከፍቱ አሳይተዋል። እየወጡ ያሉ ሪፖርቶች እንደሚጠቁሙት ጥቃት አድራሾቹ ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ወደ ሆቴሉ ተጠቃሚ በመምሰል ይመላለሱ ነበረ።

ባለ አምስት ኮከቡ ሆቴል 101 ክፍሎች ያሉት ሲሆን፤ ህንጻውም ከሆቴል በተጨማሪ የቢሮ አገልግሎቶችንም ይሰጣል።

ተያያዥ ርዕሶች