በሱዳኑ ተቃውሞ ዶክተርና ታዳጊ በጥይት ተገደሉ

የሱዳን ሰልፈኞች Image copyright Reuters

የሱዳኑን ፕሬዚዳንት ኦማር አልበሽርን ተቃውመው ሰልፍ ከወጡ ግለሰቦች መካከል ዶክተርና ታዳጊ በዛሬው ዕለት ተገድለዋል።

የፀጥታ ኃይሎች በሰልፈኞቹ ላይ በመተኮሳቸው እንደተገደሉ የሱዳን የዶክተሮች ማህበር አባል የሆነ ግለሰብ ለቢቢሲ ተናግሯል።

ሰልፈኞቹ ተቃውሟቸውን ለመግለፅ በመዲናዋ ካርቱም በሚገኝ ሆስፒታል የተቀመጡ ሲሆን በግጭቱም ዘጠኝ ግለሰቦች ቆስለዋል።

ሱዳን ውስጥ የዳቦና የነዳጅ ዋጋ ንሮብናል ያሉ ዜጎች ከፖሊስ ጋር ተጋጩ

"ከዐብይ በኋላ የሚመጣውን ሰውዬ እንዴት እናውርደው?" ነብይ መኮንን

ከሽብር ጥቃቱ ጋር በተገናኘ 9 ሰዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

ቁጥራቸው በርካታ የሆኑ ግለሰቦች ታፍሰው እንደታሰሩ የተለያዩ ሰብዓዊ መብት አቀንቃኞች እየገለፁ ነው።

በመንግሥት ላይ የተነሳው ተቃውሞ አምስተኛ ሳምንቱን ያስቆጠረ ሲሆን "ከመጀመሪያው ጀምሮ የፀጥታ ኃይሎች ያላግባብ ኃይላቸውን በመጠቀም ሰልፈኞቹ ላይ ተኩሰዋል" በማለት ዶ/ር አምጀድ ፋሪድ ያለውን ሁኔታ ገልፆታል።

የሞተው ዶክተር ሰውነቱ በአስራ አራት ጥይት ተበሳስቶም እንደሆነ ዶክተሩ ተናግሯል።

Image copyright Reuters

የኤኤፍፒ ዜና ወኪል እንደዘገበው በዛሬው ዕለት በነበረው ተቃውሞ ሶስተኛ ሰው መገደሉን ነው።

ሀዘን ላይ የተቀመጡ ሰዎችም ላይ የፀጥታ ኃይሎች ተኩስ እንደከፈቱም ሮይተርስ ዘግቧል።

ዶክተሮች ለምን ኢላማ ሆኑ?

አንድ የህክምና ባለሙያ ለቢቢሲ እንደገለፀው ዛሬ የተገደለው ዶክተር ከሰልፈኞች ጋር በአንድ ቤት ውስጥ ተቀምጦ ነበር።

የፀጥታ ኃይሎች ከቤቱ እንዲወጡ አስለቃሽ ጋዝ የረጩ ሲሆን፤ ቤት ውስጥ መቀመጥ ባለመቻላቸውም ዶክተሩ በድፍረት በሩን ከፍቶ ሰላማዊ ሰው መሆኑንም እጆቹን ወደላይ አድርጎ ለፖሊሶቹ ካሳየ በኋላ የህክምና ዶክተር መሆኑን መግለፁን ይኸው የህክምና ባለሙያ ገልጿል።

ለተጎዱ ሰዎችም የህክምና አገልግሎት እየሰጠ መሆኑን በመግለፅ ላይ እያለ ፖሊሶቹ በምላሹ "የህክምና ዶክተር ነህ? አንተንማ ስንፈልግህ ነበር" ብለው እንደተኮሱበት የህክምና ባለሙያው ተናግሯል።

ባለሙያው እንደሚናገረው በሱዳን ውስጥ የህክምና ዶክተር መሆን አደገኛና በተለይም ለፀጥታ ኃይሎች መንገር ህይወታቸውን አደጋ ላይ እንደጣለው ነው። ለዚህም ምክንያቱ የህክምና ባለሙያዎች ሃገር አቀፍ የስራ ማቆም አድማና አመፅን እየመሩ በመሆኑ እንደሆነ ይናገራል።

ተቃውሞው ወደ ስድስት ከተሞች የተስፋፋ ሲሆን፤ የሰብዓዊ መብት አቀንቃኞችም ከመጪው ሰኞ ጀምሮ ሌላ አዲስ ሰልፍ ጠርተዋል።

በተቃውሞው 24 ሰዎች እንደሞቱ መንግሥት መረጃ ቢሰጥም የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ቁጥሩን ከፍ ያደርጉታል።

ተያያዥ ርዕሶች