"ከዐብይ በኋላ የሚመጣውን ሰውዬ እንዴት እናውርደው?" ነብይ መኮንን

Image copyright Rom Agger

...ስንት ንጉስ ይንገስ…ስንት ንጉስ ይምጣ

ጸጥ ያለው መንደሬ ….ተንጦ ተንጦ ቅቤ እንዲያወጣ ?፤ አሁንም እዚያው ነኝ… ያልተተነተነ ብርቱ ጥያቄ አለኝ ጸጥ እረጭ እያለ …ቀየው ያወጋኛል

በዝምታው መሃል… ታሪክ ይነግረኛል ታሪክ እየበላ ….ታሪኬን ነጥቆኛል፤

ሳንጃው ጎረቤቴም እንዲህ ያወጋገኛል "የድሮ ዝምታ የድሮ ዝምታ...

ወር በገባ በመጀመሪያው ረቡዕ በራስ ሆቴል በሚካሄደው የጦቢያ ግጥም በጃዝ መድረክ ለመታደም ብዙዎች ቀን ይቆጥራሉ። አዳራሹ ሁሌም ሙሉ ነው። ቦታ ላለማጣት አንድ ጊዜ የዓመት ከፍለው የመድረኩ ታዳሚነታቸውን የሚያረጋግጡም ጥቂት አይደሉም።

"ኢትዮጵያዊ ታሪኮችን ወደ ዓለም አቀፍ የፊልም መድረክ ማምጣት ፈታኝ ነው" ዘረሰናይ መሐሪ

ምሁራን፣ ፖለቲከኞች፣ ፀሃፊያንና ሌሎችም በርካታ ታዋቂ ሰዎች የመድረኩ ፈርጥ ነበሩ።

ካላይ ያለው በጦቢያ ግጥም በጃዝ በገጣሚ ምህረት ከበደ ከቀረበ ግጥም የተቀነጨበ ነው።

በተለይም ባለፉት ጥቂት ዓመታት በጦቢያ ግጥም በጃዝ የቀረቡ ግጥሞችም ሆኑ ዲስኩሮች ያለውን ስርአት የሚተቹ ነበሩ። የመንግስት አስተዳደር ስርዓት ብልሹነትና መውደቅ፣ ነፃነት ማጣት፣ ሙስና፣ ስራ አጥነትና የኑሮ ውድነት በመድረኩ የሚቀርቡ ስራዎች ማጠንጠኛዎች ነበሩ።

"ሌቱም አይነጋልኝ" የተባለላት የውቤ በረሃ ትዝታዎች

የታዳሚው ጭብጨባና ፉጨት ገጣሚያኑ አንደበት ሆነው የልቡን የነገሩለት ይመስል ነበር። መድረኩ የሃገሪቱ የፖለቲካ ልብ ትርታ ነበር ማለት ሁሉ ይቻላል።

ስለ ጠልሰም ወይም በተለምዶ የአስማት ጥበብ ተብሎ ስለሚጠራው ምን ያህል ያውቃሉ?

"የዘመኑ ሃሳብ ተጋብቶብን ነበር"

ከመድረኩ መስራቾች አንዷ የሆነችው ገጣሚ ምስራቅ ተረፈ የጦቢያ ግጥም በጃዝ ስራዎች ባለፉት ጥቂት ዓመታት ትኩረታቸው ፖለቲካ መሆን በጊዜውና መሬት ላይ የነበረው ሁኔታ የፈጠረው ተፅእኖ ነው ትላለች። "የነበረው ሁኔታ ሁላችንም ገጣሚዎች እንደዛ እንድናስብ አድርጎናል ብዬ አስባለሁ። የዘመኑ ሃሳብ ተጋብቶብን ነበር" በማለት በደርግ ጊዜ የነበሩ ግጥሞችም ያንን ጊዜ ፤ከዚያ በፊት የነበሩ ግጥሞችም ጊዜያቸውን ይመስሉ እንደነበር ትናገራለች።

ምስራቅ እንደምትለው በመድረኩ የሚቀርቡ ስራዎች ፖለቲካ መሆን የታዳሚው ፍላጎትን የተከተለ ወይም በመድረኩ አዘጋጆች መመሪያ የሆነም አልነበረም።

ነገር ግን ታዳሚውም ገጣሚውም የሚያየውና የሚሰማው በጥቅሉ የሚኖርበት ሁኔታ ተመሳሳይ መሆን የገጣሚውንና የታዳሚውን ፍላጎት አንድ አድርጎታል። "በአንድ አይነት መንገድ እንድናስብ ሆነን ተገኝተናል" ትላለች ምስራቅ።

"ታዳሚው ተፅእኖ ያደረገብን ይመስለኛል"

ተፅእኖው የታዳሚው ነው ? ወይስ ግጥሙ የፈጠረው?

ገጣሚ ነብይ መኮንን በጦቢያ ግጥም በጃዝ በተጠቀሱት ጊዜያት የቀረቡ ስራዎች ትኩረት በአብዛኛው ፖለቲካ መሆንና የሚጨበጨብላቸውም እንደዚህ ያሉ ስራዎች መሆን በአብዛኛው የታዳሚው ተፅእኖ ውጤት እንደሆነ ያምናል።

ግጥሙ እየቀረ ፕሮፖጋንዳ እየበዛ ከመጣ አንድ የግጥም ወይም የኪነጥበብ ስርዓት አደጋ ላይ ነው ይላል።

"ምስራቅ ስለ ፅጌረዳ ግጥም ፅፋ ብትመጣ ማንም ሰው ሳያጨበጭብ እንለያያለን ማለት ነው "በማለት ነገሩን ለማስረዳት ይሞክራል።

የግጥም ውበትን እየተው ይዘቱ ላይ ማተኮር፤ ይዘቱም ፖለቲካ ብቻ ሲሆን ለነብይ ከባድ ችግር ነው። ስለ ነፃነት ስለ ሰላም ሲፃፍ የግጥም ስነ ውበት ሳይዘነጋ መሆን እንዳለበት ያስረዳል ነብይ።

"ግጥም ያለ ስነውበት ከንቱ ነው ምክንያቱም ማንም ፕሮፖጋንዲስት እንዲሁ ሊለው ይችላል" ይላል።

ለነብይ ይልቁንም ተፅእኖ መምጣት ያለበት ከገጣሚው ነው።

"ፀጋዬ ገብረ መድህን ስለ ጆኒ ዎከር የሚለው አንድ ነገር አለው። ዮሃንስ አራምዴ ይለዋል ጆኒ ዎከርን። ዮሃንስ አራምዴም በዘመኑ ታምቶ ነበር ከመራመድም አራምደሃል ተብሎ ይላል" በማለት ህብረተሰብ ውስጥ የኪነጥበብ ሰው መሆን ያለበት አራማጅ ነው ብሎ እንደሚያምን ያስረዳል።

ሌላው የነብይ ነጥብ የኪነጥበብ ሰው በጊና በሁኔታ መገደብ የለበትም የሚል ነው። "በተገደበ ዘመን አንቆምም። የተገደበውን አልፈን ምናልባት ሰው እንዲያልፍ እናግዝ ይሆናል" በማለት 'ከዓብይ በኋላ የሚመጣውን ሰውዬ እንዴት እናውርደው?' የሚል ግጥም መፃፉን ይናገራል።

Image copyright Rom Agger

"ፍለጠው ግደለው የሚል የፖለቲካ ግጥም የለም"

ሌላዋ የጦቢያ ግጥም በጃዝ መስራች ገጣሚ ምህረት ከበደ በተለይም ከ2001 ዓ.ም ወዲህ በመድረኩ የፖለቲካ ስራዎች መብዛታቸውን ታምናለች። በምስራቅ ሃሳብ የምትስማማው ምህረት ለረዥም ዓመታት በፑሽኪን ከዚያም በባህል ማእከል ግጥሞቻቸውን ሲያቀርቡ የነበሩባቸውን ጊዜአት በማስታወስ፤ ፖለቲካ ላይ ማተኮር ዘመን ይዞት የሚመጣ ነገር እንደሆነ ታስረግጣለች።

"ጋዜጠኛው፣ ፀሃፊውና ጓደኞችሽ ካጠገብሽ ሲታሰሩ ምን ትያለሽ? የተሰጠሽና ያለሽ መታገያ ፅሁፍም ከሆነ ስእል በዚያ ትታገያለሽ" ትላለች

እሷ እንደምትለው ፀሃፊው በውስጡ ለሚሰማው ነገር ታማኝ ከሆነ ውስጡ የሚኖረው ነገር በተገኘበት ቦታና ጊዜ ያለ እውነት ነው። በዚህ መልኩም የጦቢያ ግጥም በጃዝ ፀሃፊዎችና ታዳሚዎች ተገናኝተዋል።

የፖለቲካ ግጥሞችም ሲፃፉም እንዲሁ "ፍለጠው ግደለው " ሳይሆኑ ይልቁንም ጥበብ ያለው እንደሆነ የምትናገረው ምህረት "ሰምና ወርቅ ያለው ነው። ሰውም ይህን ይረዳል። ያገራችን ሰው ግጥም ቅርጥም አድርጎ የበላ ብዬ ነው የማምነው" ትላለች።

ፖለቲካው እለት በለት የሚጋጫቸው ነገር ስለሆነ የሚያመልጡት ነገር እንዳልሆነ ይልቁንም ጊዜው ገጣሚያኑን ይዞ የመሄድ ሃይል እንዳለው ትገልፃለች።

የጦቢያ ግጥም በጃዝ አስተባባሪ ፅዮን ሞላ ደግሞ ጥበብ በመሸጥ መልኩ ባይታይም ገዥና ሻጭ የተገናኙበት መድረክ እንደሆነ ትናገራለች።

"ታዳሚው ልቡ ውስጥ የሚተራመሰው ነገር የሚወጣበት፣ ሁሉም የሚተነፍስበት መድረክ ነው" ትላለች።

ጦቢያ ግጥም በጃዝ ዛሬ ላይ እንዲደርስ ለማድረግ መስዋእትነት መከፈሉን፤ የደህንነት አባሎች መድረኩን በመታደምና ፊልም በመቅረፅ በኋላ እንዴት የዚህ ወይም የዚያ አይነት ግጥም ይቀርባል ተብለው ይጠየቁ እንደነበር ይናገራሉ።

ባለፉት ሁለት የአስቸኳይ ጊዜ አዎጆች ወቅት ደግሞ ሶስት ሰዎች መታወቂያቸውን አስይዘው እንዲፈርሙ ይደረግ እንደነበርም ያስታውሳሉ።

ረቡዕ ጥር 1 በተካሄደው የዚህ ወር የጦቢያ ግጥም በጃዝ መድረክ የአዲስ አበባ ከንቲባ አቶ ታከለ ኡማ ተገኝተው የነበረ ሲሆን የጦቢያ ታዳሚ እንደነበሩም ተናግረዋል።

ጦቢያ ግጥም በጃዝ በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ከኢትዮጵያ የሳይንስ እና ከፍተኛ ትምህርት ሚንስትር ጋር በመላው ሀገሪቱ በሚገኙ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ " ኢትዬጵያን እና ኢትዬጵያዊነት ማድመቅ" በሚል መሪ ቃል ኪነ-ጥበባዊ መድርክ ለማዘጋጀት መስማማቱም የሚታወስ ነው።

በስምምነቱ መሰረትም የመጀመሪያው መድረክ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ፋኩልቲ ተካሂዷል።