ከተለያየ ጎሳ የተጋቡ የጂግጂጋ ጥንዶች ስጋት ላይ ነን እያሉ ነው

የተጋቡት ጥንዶች

በሶማሌ ክልል ዋና ከተማ ጂግጂጋ ባለፈው ሚያዚያ ወር ትዳር የመሰረቱት ጥንዶች ከከተማዋ እንዲለቁ በሃላፊዎች እየተገደዱ እንደሆነ ለቢቢሲ ገልጸዋል።

የሶማሌ ክልላዊ መንግሥት ግን ከሌላ ጎሳ ጋር ትዳር የመሰረቱ ጥንዶች ላይ ምንም አይነት ችግር ችንዲገጥማቸው እንደማይፈቅድና ይህንን ተግባር እየፈጸሙ ያሉት ሰዎች የክልሉን መንግሥት የማይወክሉ መሆናቸውን ገልጿል።

ሃዋ አብዱልቃድር ሙስታሂል ከሚባል አካባቢ ነው ወደ ጂግጂጋ የመጣችው። እሷ እንደምትለው ከሌላ ጎሳ ጋር ተጋብተው ለሚኖሩ ጥንዶች ከቤተሰብና ዘመዶች ራቅ ብሎ የከተማ ህይወት መኖር የተሻለ ይሆናል በሚል እሳቤ ነው ወደ ጂግጂጋ የመጣችው።

የዚምባብዌ ወታደሮች ዘዴያዊ ማሰቃየት ተጠቅመዋል ተባለ

የአልጀሪያዋ ቁንጅና አሸናፊዋ ዘረኝነት እንደማይበግራት ገለፀች

''ወደ ጂግጂጋ ስመጣ በጣም ደስ ብሎኝ ነበር። በከተማዋ ብዙ ከሌላ ጎሳ የተውጣጡ ጥንዶች በአንድ ላይ ሲዳሩ ከእነሱ መሃል ነበርኩ። ቤት ተሰጥቶንም ነበር። አሁን አሁን ግን ከቤታችሁ እናስወጣችኋለን የሚሉ ማስፈራሪያዎች በርክተዋል።''

በሶማሌ ክልል የጎሳ አወቃቀር እጅግ አስቸጋሪ ከሚባሉት መካከል ነው። ከተለያዩ ጎሳዎች የመጡ ጥንዶች ትዳር ሲመሰርቱ መመልከት የተለመደ አይደለም። ከፍተኛ ቦታ የሚሰጣቸው ጎሳዎች ወደታች ወርደው ከሌላ ጎሳ ማግባት አይችሉም፤ ደፍረው ቢያደርጉትም ብዙ የእንገላችኋለን ማስፈራሪያዎች ይከተላሉ።

በጎረቤት ሃገር ሶማሊያ የሚገኝ አንድ ግለሰብ ከፍ ያለ ቦታ ካለው ጎሳ ከተገኘች ሴት ጋር ትዳር በመመስረቱ በእሳት ተቃጥሎ እንዲሞት ተደርጎ ነበር።

የቀድሞው የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አብዲ ሞሃመድ ኦማር በጎሳዎች መካከል ያለውን ልዩነትና መከፋፈል ለመቀነስ በማለት ባለፈው ሚያዚያ ወር ላያ ከተለያዩ ጎሳዎች የተገኙ 29 ጥንዶችን አንድ ላይ ሰርግ ሥነ ሥርዓታቸውን እንዲፈጽሙ አድርገው ነበር።

የብሔር ግጭት የሚንጣት ሀገር

በእርጥብ ሳርና ቅጠል ጥቃትን ያስቆሙ አባቶች

ሁሉም ጥንዶች ከሰርጋቸው በኋላ በዋና ከተማዋ የመኖሪያ ቤት የተሰጣቸው ሲሆን ቃል ተገብቶላቸው የነበረው የሥራ ዕድል ግን እስካሁን ተግባራዊ እንዳልተደረገላቸው ገልጸዋል።

የቀድሞው ፕሬዝዳንት ከስልጣናቸው ከለቀቁ በኋላ ግን በአዲስ መልክ የተዋቀረው የክልሉ መንግሥት ቃል ተገብቶላቸው የነበረውን ነገር ለመፈጸምም ሆነ ደህንነታቸውን ለመጠበቅ እያደረገው ያለ ነገር እንደሌለም ለቢቢሲ ተናግረዋል።