አቶ በረከት ስምኦንና እና አቶ ታደሰ ካሳ በቁጥጥር ስር ውለው ወደ ባህር ዳር ተወሰዱ

አቶ በረከት ስምኦን እና አቶ ታደሰ ካሳ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተዘገበ

አቶ በረከት ስምኦን እና አቶ ታደሰ ካሳ ዛሬ አዲስ አበባ ከሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የአማራ ጸረ ሙስና ኮሚሽን አስታውቋል።

የአማራ ክልል ፀረ ሙስና ኮሚሽነር አቶ ዝግአለ ገበየሁ በሰጡት መግለጫ፤ ግለሰቦቹ የተጠረጠሩበት ወንጀል የተፈፀመው በክልሉ በመሆኑ ጉዳያቸው በክልሉ ፍርድ ቤት ስለሚታይ ሁለቱ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ወደ ባህር ዳር መወሰዳቸውን ተናግረዋል።

ኮሚሽኑ በእስካሁኑ ሂደት በግለሰቦቹ ላይ ክስ ለመመስረት የሚያስችለኝን ከበቂ በላይ ማስረጃ ሰብስቢያለሁም ብሏል።እንደ መግለጫው ከሆነ አቶ በረከት ስምኦን እና አቶ ታደሰ ካሳ በቁጥጥር ስር የዋሉት በጥረት ኮርፖሬት የሃብት ብክነት ፈጽመዋል በመባል ተጥርጥረው ነው።

በቀድሞ ስሙ ብአዴን እና በአሁኑ መጠሪያው የአማራ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ አቶ በረከት ስምኦን እና አቶ ታደሰ ካሳ ከማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት መታገዳቸው ይታወሳል።

የብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ አቶ በረከት ስምኦንን እና አቶ ታደሰ ካሳን ከማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት ማገዱን ያስታወቀው ነሐሴ 18/2010 ዓ.ም ነበር።

ከኢህአዴግ ከፍተኛ አመራሮች አንዱ የነበሩት አቶ በረከት የቀድሞ የማስታወቂያ ሚንስቴር ሚንስትር በኋላም የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ሚኒስትር እንዲሁም በኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ምርምር ማዕከል የኢንዱስትሪ ዘርፍ መሪ ሚኒስትር በመሆን አገልግለዋል።

የአማራ ክልል የጸረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ዝግአለ ገበየሁ በሰጡት መግለጫ "የአዋጭነት ጥናት ሳይከናወን ግዥ መፈፀሙ ጥረትን ለኪሳራ ዳርጎታል፤ ቀሪ ምርመራ የሚጠበቅ ሆኖ፤ እነዚህ እስካሁን የያዝናቸው ማስረጃዎች ክስ ለመመስረት የሚስችሉ ናቸው ብለን እናምናለን" ብለዋል።

ከዚህ በተጨማሪም ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ስር የዋሉት ምርመራውን የበለጠ ለማቀላጠፍ ሲሆን ሌሎች ተጠርጣሪዎችም እንደሚኖሩ አክለዋል።

"የዳሸን ቢራ ፋብሪካ ጉዳይ ጋር በተያያዘ የዳሸን ቢራ ሽያጭ የወሰኑት አቶ በረከት ብቻ ሊሆኑ አይችሉም። በቦርድ ስለሆነ የሚወሰነው ሌሎች ተጠያቂዎች ይኖራሉ'' ሲሉ ተደምጠዋል ኮሚሽነሩ።

"ግለሰቦች በሕዝብ ሃብት፤ በጥረት ሃብት ያለአግባብ እንዲጠቀሙ ተደርጓል። ኃላፊዎቹ ሥራቸውን በአግባቡ ባለመወጣታቸው ምክንያት በጥረት ስር ባሉ በአምስቱም ኩባንያዎች ላይ ኪሳራና ዕዳ ነው የሚታየውም ብለዋል።

''ተጠርጣሪዎቹን በቁጥጥር ስር የማዋሉ ሥራ ጊዜ የወሰደብን ደግሞ ለፍርድ ቤት በሚቀርብ መልኩ ኦዲቱ በአግባቡ መደራጀት ስለነበረበት ነው" በማለት ጉዳዩን አስረድተዋል ኮሚሽነር ዝግአለ።

አቶ በረከት ከጥቂት ወራት በፊት ከቢቢሲ አማርኛ ጋር የነበራቸውን ቆይታ ለመመልከት ከዚህ በታች ያለውን ማስፈንጠሪያ ይከተሉ።

በትግል ስማቸው 'ጥንቅሹ' ተብለው የሚታወቁት እና የጥረት ዋና ሥራ አስፈጻሚ የነበሩትን አቶ ታደሰ ካሳም ከአቶ በረከት ስምኦን ጋር ከብአዴን ማዕከላቂ ኮሚቴ መታገዳቸው ይታወሳል።

ቢቢሲ አማርኛ አቶ ታደስ በጥረት ኮርፖሬሽን ውስጥ የነበራቸው ተሳትፎ ምን ይመስል እንደነበረ እና የብአዴንን ውሳኔውን እንዴት አገኙት ጥያቄ አቅርቦላቸው ነበር። ከአቶ ታደሰ ጋር የነበረንን ቆይታ ከዚህ በታች መመልከት ይችላሉ።