ወደ ካናዳ መሄድ አስበዋል? ከአጭበርባሪዎች ይጠንቀቁ

የካናዳ ሰንደቅ ዓላማ በቶሮንቶ ካናዳ Image copyright Roberto Machado Noa
አጭር የምስል መግለጫ የካናዳ ሰንደቅ ዓላማ በቶሮንቶ ካናዳ

''. . . ማታለል እንደሆነ ግልጽ ነበረ። ጓደኛዬ በእርግጠኛነት ይሆናል ብትለኝም አጥብቄ አለመጠየቄ አሁንም ይቆጨኛል'' ይህን ያለችው ወደ ካናዳ እንልክሻለን በሚሉ አጭበርባሪዎች ከ30ሺህ በላይ ዶላር የተታለለችው ኑአሚን መኩሪያ ነች።

ሰሜን አሜሪካዊቷ ሃገረ ካናዳ በቀጣዮቹ ሦስት ዓመታት ወደ 1 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎችን ከተለያዩ ሃገራት እንደምትቀበል አስታውቃለች። ይህን እድል በመጠቀም ህይወታቸውን በካናዳ ለማደላደል ጥረት እያደረጉ ያሉ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከፍተኛ እንደሆነ ይነገራል።

የካናዳ መንግሥት ውሳኔን እና የሰዎች ፍላጎት ተከትሎ ወደ ካናዳ እንልካለን የሚሉ ሐሰተኛ የኢሚግሬሽን ባለሙያዎች የማጭበርበር ሥራን እያጧጧፉ ይገኛሉ።

ካናዳ ዕፀ ፋርስን ህጋዊ አደረገች

ከቤተሰቦቿ አምልጣ ካናዳ የገባችው የሳዑዲዋ ወጣት፡ 'ምንም የሚጎልብኝ የለም'

ኑአሚን መኩሪያ በሰላሳዎቹ መጀመሪያ ላይ ትገኛለች። የዛሬ ዓመት ገደማ ካናዳ እንወስድሻለን ያሉ ሰዎች ሰላሳ ሺህ ዶላር እንዳጭበርበሯት ትናገራለች።

የጉዞ ሂደቱን የጀመረችላት ካናዳ የምትኖር ጓደኛዋ ነበረች። ጓደኛዋ ኑአሚንን ወደ ካናዳ እንወስዳለን ብለው የነበሩትን ሰዎች በአካል አግኝታቸው አታውቅም።

እንደዚያም ሆኖ ኑአሚን እና ጓደኛዋ በሰዎቹ በተሰጣቸው የባንክ ሂሳብ ቁጥር ገንዘብ አስገብተው ነበር። ኑአሚንን እንወስዳታለን የሚሉት ሰዎች ግን እጥፍ ተጨማሪ ገንዘብ ሲጠይቁ፤ "ከዚህ በኋላ ምንም ዓይነት ገንዘብ አልጨምርም" በማለት ነገሩን በዚያው እንዳቆመች ኑአሚን ትናገራለች።

በወቅቱ ሰላሳ ሺህ ዶላሩ የተከፈለው በተለያየ አገር ላሉ የባንክ ሂሳቦች እንደሆነ ኑአሚን ትናገራለች።

እሷ አራት ሺህ ዶላር (በብር መንዝራ) ሃገር ውስጥ ባለ የባንክ ሂሳብ ስታስገባ ጓደኛዋ ደግሞ ካናዳ፣ ጣልያን፣ ዱባይና ኬንያ በሚገኙ የባንክ ሂሳቦች ቀሪውን ገንዘብ አስተላልፋለች።

"ሂደቱ ማታለል እንደሆነ ግልጽ ነው። ጓደኛዬ በእርግጠኛነት ይሆናል ብትለኝም አጥብቄ አለመጠየቄ ይቆጨኛል" ትላለች።

የኑአሚን እና የጓደኛዋን ታሪክ የሚጋሩ በርካቶች አሉ። በተሻለ ስፍራ የተሻለ ህይወት መመስረት የሁሉም ፍላጎት ነው ማለት ማጋነን ላይሆን ይችላል። ይሁን እንጂ ይህን ፍላጎት በትክክለኛው መንገድ እንዴት ወደ እውነታ መለወጥ ይቻላል የሚለው ሊታሰብበት ይገባል።

የካናዳ መንግሥት ይፋ ባደረገው ፕሮግራም መሰረት አንድ ሰው በየትኛው ዘርፍ የዕድሉ ተጠቃሚ መሆን እንደሚቻል ጠንቅቆ ማወቁ፤ እራስን ከአጭበርባሪዎች ለመጠበቅ ያስችላል።

በዚህም መሰረት በቋሚነት ወደ ካናዳ ሊኬድ የሚቻልባቸው ዋና ዋና አማራጮች ከዚህ በታች እንደሚከተለው ቀርበዋል።

የቤተሰብ ስፖንስርሺፕ

በካናዳ እድሜያቸው 18 ዓመት እና ከዚያ በላይ ሆነው፤ የካናዳ ዜግነት ወይም የመኖሪያ ፍቃድ ያላቸው ሰዎች መስፈርቱን በሟሟላት የቅርብ የቤተሰብ አባላትን በዚህ ፕሮግራም ወደ ካናዳ ማምጣት ይችላሉ። የካናዳ የኢሚግሬሽን ይፋዊ ድረ-ገጽ እንደሚለው በዚህ ፕሮግራም የትዳር አጋር፣ ልጆች፣ ወላጆች፣ አያቶች እና የጉዲፈቻ ልጆች መካተት ይችላሉ።

ከላይ የተጠቀሱት የቤተሰብ አባላት ዝርዝር ወደ ካናዳ ለማቅናት ማሟላት የሚኖርባቸው የየራሳቸው የሆነ መስፈርቶችን እና ልዩ የሆኑ ሥርዓት መከተል ይኖርባቸዋል።

ለምሳሌ የትዳር አጋሯን ወደ ካናዳ ለማምጣት የምታስብ አንዲት ሴት የካናዳ ዜጋ ወይም ነዋሪ መሆን ይኖርባታል። ከዚህ በተጨማሪም የመህበራዊ ድጋፍ ከመንግሥት የማትቀበል፣ ወደ ካናዳ ለምታመጣው የትዳር አጋር መሰረታዊ ፍላጎት ማሟላት የምትችል እና የገቢ መጠኗም በመንግሥት ዝቅተኛ ደረጃ ተብሎ ከተቀመጠው በላይ መሆን ይኖርበታል።

የቮልስ ዋገን መምጣት የመኪና ዋጋን ይቀንስ ይሆን?

ወደ አዲስ አበባ ሊጓዝ የነበረው እስረኛ ጥቃት ደረሰበት

በሌላ መልኩ ወደ ካናዳ እንዲሄድ የሚፈለገው ሰው በካናዳ ተቀባይነት ያለው መሆን ይኖርበታል። ለሃገር ደህንነት አስጊ የሆኑ፣ በሰብዓዊ መብት ጥሰት የተሳተፉ፣ በመንግሥት ስልጣን ላይ ያሉ ወይም ሳሉ ግፍ የፈጸሙ፣ በአልኮል እና በዕፅ ተጽእኖ ሥር ሆነው ያሽከረከሩ ወይም መሰል ወንጀል የፈጸሙ መሆን የለባቸውም።

በተጨማሪም የጤና ሁኔታቸው ለሃገር አስጊ ከሆነ ወይም ከፍተኛ ህክምና እና ክትትል የሚያስፈልገው ህመም ያለባቸው እንዲሁም ወደ ካናዳ ለመግባት ሐሰተኛ መረጃ ያቀረቡ ሰዎች በካናዳ ተቀባይነት የሌላቸው ሰዎች ተብለው ይፈረጃሉ።

ክህሎትን መሰረት ያደረገ ፕሮግራም (ኤክስፕረስ ኢንትሪ)

ኤክስፕረስ ኢንትሪ ክህሎትን መሰረት ያደረገ ፕሮግራም ሲሆን እውቀት፣ ልምድ እና የቋንቋ ችሎታን በመጠቀም በቀጣሪዎች አማካኝነት ወደ ካናዳ የሚኬድበት መንገድ ነው።

በሙያዬ በቂ ልምድ እና እውቀት አካብቻለሁ፤ በቋንቋ ችሎታዬም እተማመናለሁ የሚል እና ፍላጎት ያለው በኤክስፕረስ ኢንትሪው ተሳታፊ ሊሆን ይችላል።

በቅድሚያ ወደ ይፋዊ ድረ-ገጹ በመሄድ የግል መረጃዎትን ያስገባሉ። በሰጡት መረጃ መሰረትም ነጥብ ያስመዘግባሉ። ከዚያም ባስመዘገቡት ነጥብ መሰረት ከተቀሩት አመልካቾች ጋር ይመዘናሉ። ያስመዘገቡት ውጤት፣ የሥራ ልምድዎ እና የቋንቋ ችሎታዎ የቀጣሪዎችን ቀልብ ከሳበ፤ በካናዳ ለመኖር የሚያስችል የጥሪ ድብዳቤ ይደርስዎታል። በዚህ ላይ በመመስራት የመኖሪያ ፍቃድ ይጠይቃሉ።

በስደተኝነት

በካናዳ ሕግ ስመሰረት ስደተኛ (ሪፊዩጂ) ማለት በፖለቲካ አመለካከት፣ በሐይማኖት፣ በብሔር ወይም በጾታ ግነኙነት ፍላጎታቸው ምክንያት የደረሰባቸውን ወይም የሚደርስባቸውን ክስ እና ጥቃት ሸሽተው ከሃገራቸው የወጡ ሆነው ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች ወደ ሃገራቸው መመለስ የማይችሉ ሰዎች ማለት ነው።

በስደተኛ ወይም 'ሪፊዩጂ' እና 'በኢሚግራንት' መካከል ሰፊ ልዩነት አለ። ኢሚግራትን ማለት አንድ ሰው በውጫዊ ጫና ውስጥ ሳይወድቅ በራሱ ፍቃድ በቋሚነት በሌላ ሃገር መኖር የሚፈልግ ሰው ማለት ነው። ስደተኛ ወይም 'ሪፊዊጂ' ማለት ግን ተገዶ ከሃገሩ የወጣ ሰው ነው።

ለምሳሌ አንድ ኢትዮጵያዊ በስደተኞች ፕሮግራም ወደ ካናዳ መሄድ ቢፈልግ ከኢትዮጵያ ውጪ ባሉ ሃገራት ውስጥ ሆኖ በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞ ከፍተኛ ኮሚሽን 'ስደተኛ' ተብሎ መመዝገብ ይኖርበታል።

ከዚያም ስደተኛ ተብሎ የተሰየመው ግለሰብ በተባበሩት መንግሥታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን አማካኝነት ወደ ካናዳ ለመሄድ የሚያደርገውን ጥረት ይጀምራል ማለት ነው። ስደተኞች ወደ ካናዳ ለመሄድ ለካናዳ መንግሥት በቀጥታ ማመልከት አይችሉም። ጥያቄያቸው የሚያቀርቡት በተባበሩት መንግሥታት በኩል ብቻ ነው።

በግል-ሥራ በመተዳደር (ሰልፍ-ኢምፕሎይድ ፐርሰንስ)

ሰልፍ-ኢምፕሎይድ ፐርሰንስ ፕሮግራም መስፈርቱን የሚያሟሉ በግል-ሥራ የሚተዳደሩ ሰዎች ወደ ካናዳ በማቅናት ኗሯቸውን በቋሚነት እንዲመሰርቱ ያስችላል።

በዚህ ፕሮግራም ውስጥ በተለይ በስፖርትና በጥበባት የሙያ መስኮች የተሰማሩ ሰዎች ጉዳይ በተለይ ይስተናገድበታል። በመስኮቹ ከሁለት ዓመት እና ከዚያ በላይ ልምድ ያላቸው፣ በዓለም አቀፍ መድረኮች የተሳተፉ፣ ልምድ እና እውቀታቸውን ለካናዳ ለማበርከት ፍቃደኛ የሆኑ፣ የጤና እና የደህንነት መርመራዎችን ማለፍ የሚችሉ መሆን ይኖርባቸዋል።

በተጨማሪም እድሜ፣ ልምድ፣ የትምህርት ደረጃ፣ የቋንቋ ችሎታ እና አዲስ ስፍራዎችን በቀላሉ የመላመድ ክህሎት ተጨማሪ ከግምት ውስጥ የሚገቡ መስፈርቶች ናቸው።

ከላይ ከተዘረዘሩት ፕሮግራሞች ውጪ በካናዳ ኢንቨስት በማድረግ፣ በሥራ ፈጠራ፣ የእንክብካቤ አገልግሎቶችን በመስጥት (ካናዳ ውስጥ ልምድ ላላቸው ብቻ) የሚሉ እና ሌሎች ወደ ካናዳ ሊኬድባቸው የሚቻሉባቸው ፕሮግራሞች አሉ።

ሐሰተኛ ማስረጃዎችን መጠቀም

በሰዎች መታለልም ይሁን ሆን ተብሎ ቪዛ እና የመኖሪያ ፍቃድ ለማግኘት ሲባል ሐሰተኛ ማስረጃዎችን መጠቀም ወይም በቃለ መጠይቅ ወቅት የኢሚግሬሽን ኃላፊዎችን መዋሸት እንደ ከፍተኛ ወንጀል ይቆጠራል።

ይህም ማመልከቻውን ውድቅ ከማድረግ አልፎ የወንጀል ክስ ሊያስመሰርት ይችላል። ሐሰተኛ ማስረጃ መጠቀማቸው የተረጋገጠባቸው እድሜ ልክ ወደ ካናዳ እንዳይገቡ እገዳ ሊጣልባቸው ይችላል።

እራሳችንን እንዴት ከአጭበርባሪዎች መጠበቅ እንችላለን?

የካናዳ ኢሚግሬሽን ድረ-ገጻ የትኛውም አካል የካናዳ ቪዛ ወይም ሥራ ለማስገኘት ቃል ሊገባልዎት አይችልም ይላል። የካናዳ መንግሥት የኢሚግሬሽን ኃላፊዎች፣ የካናዳ ኤምባሲዎች፣ ከፍተኛ ኮሚሽኖች እና ቆንስላዎች ብቻ ናቸው በቪዛ ጥያቄዎች ላይ ሊወስኑ የሚችሉት።

በእርግጠኝነት የካናዳ ቪዛ እንደሚሰጥዎ የሚያስተዋውቁ ግለሰቦች ወይም ድርጅቶች ሐሰተኛ የመሆናቸው እድል ከፍተኛ ነው ይላል ድረ-ገጹ።

ገንዘብዎን ወይም የግል መረጃዎችን ለማግኘት ሲባል ሐሰተኛ የኢሚግሬሽን ባለሙያዎች የማጭበርበር ሥራዎችን ይሰራሉ።

ጥንቃቄ ያድርጉ፤ ትክክለኛ የካናዳ መንግሥት የኢሚግሬሽን ባለሙያ በባንክ ገንዘብ ገቢ እንዲያደርጉ ወይም እንዲልኩ አይጠይቅም ወይም ለቅጽ ገንዘብ አያስከፍልም።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ