ከአስር አመት በላይ ራሷን ሳታውቅ ኮማ ውስጥ ያለችን ታማሚ ያስረገዝው በቁጥጥር ስር ዋለ

ናታን ሱዘርላንድ Image copyright MARICOPA COUNTY SHERIFF'S OFFICE

አሜሪካ ውስጥ ከአስር ዓመት በላይ በህይወትና በሞት መካከል ሆና ራሷን የማታውቅ ታማሚ በህክምና ማዕከል ውስጥ ህጻን ልጅ መገላገሏ ከወደ አሪዞና መሰማቱ ብዙዎችን አስገርሞ ነበር።

ይህንን ተከትሎም የታማሚዎች መንከባከቢያን የሚያስተዳድረው ድርጅት ዋና ኃላፊ በገዛ ፈቃዳቸው ከስራቸው መልቀቃቸው ይታወሳል።

ፖሊስ ዛሬ እንዳስታወቀው ደግሞ ታማሚዋ ላይ ጾታዊ ጥቃት አድርሷል ያለውን በማዕከሉ የሚሰራ ግለሰብ በቁጥጥር ስር አውሏል።

ተጠርጣሪው ናታን ሱዘርላንድ የተባለ የ36 ዓመት ነርስ ሲሆን በጤና ማዕከሉ ውስጥ ስሟ ያልተጠቀሰችውን ታማሚ ከሚንከባከቡት ነርሶች መካከል አንዱ ነበር ተብሏል።

ታማሚዋ 'ሃሲዬንዳ' በተባለው የጤና ማዕከል ውስጥ ከአስር ዓመታት በላይ ህክምና ሲደረግላት የቆየ ሲሆን፤ ኮማ ውስጥ ስለሆነችም 24 ሰአት የዶክተሮች ህክምናና ክትትል ይደረግላታል ነበር።

በህክምና ስህተት የመከነው ህፃን

የ7 ዓመቷ ህፃን መፀዳጃ ቤት አልሰራልኝም ስትል አባቷን ከሰሰች

በህክምና ማዕከሉ የሚሰራ አንድ ግለሰብ እንደተናገረው ታማሚዋ ከሌላው ጊዜ በተለየ የማቃሰትና ህመም ውስጥ እንደሆነች የሚያሳዩ ምልክቶችን አሳይታ ነበር ብሏል። አክሎም ታማሚዋ ልጇን እስክትገላገል ድረስ የትኛውም የማዕከሉ ሰራተኛ ነፍሰጡር እንደሆነች እንዳላወቀ ገልጿል።

ፖሊስ በጉዳዩ በሰጠው መግለጫ በታማሚዋ ላይ ያለ ፍላጎቷና ከእውቅናዋ ውጪ ጾታዊ ጥቃት ተፈጽሞባታል ብሏል። በአሁኑ ሰዓት የተወለደው ህጻን ልጅ በጥሩ ጤንነት ላይ እንደሚገኝና የታማሚዋ ቤተሰቦች እየተንከባከቡት እንደሆነም ታውቋል።

ጋሪ ኦማን የተባሉት የድርጅቱ ምክትል ስራ አስኪያጅ ደግሞ በተፈጠረው አስነዋሪ ተግባር እጅግ ማፈራቸውን በመግለጽ ለሆነው ነገር ሁሉ ኃላፊነቱን እንደሚወስዱ አስታውቀው ነበር።

ህጻኑ ከተወለደ በኋላ ፖሊስ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ሁሉም የማዕከሉ ሰራተኞች የዘረመል ቅንጣት እንዲሰጡ ያደረገ ሲሆን በምርመራው ውጤት መሰረትም ተጠርጣሪው ናታን ሱዘርላንድ የልጁ አባት መሆኑ ተረጋግጧል።

ተጠርጣሪው ረቡዕ ዕለት ፍርድ ቤት የቀረበ ሲሆን 500 ሺ ዶላር አስይዞ ጉዳዩን ከውጪ ሆኖ እነዲከታተል ፍርድ ቤቱ ወስኗል።

ልጆችዎ ጤናማ ምግብ እንዲመገቡ ማድረጊያ መላዎች

ቁርስ የቀኑ እጅግ አስፈላጊ ምግብ ነውን?

በአሁኑ ሰዓት በማዕከሉ ከበድ ያሉ የደህንነት መጠበቂያ እርምጃዎች እየተወሰዱ እንደሆነ የድርጅቱ ምክትል ስራ አስኪያጅ ገልጸዋል።

ማንኛውም ወንድ የማዕከሉ ሰራተኛ ወደ ሴት ታማሚዎች ክፍል ሲገባ አንድ ተጨማሪ ሴት ሰራተኛ አብራው እንድትገባ እያደረጉ እንደሆነም ምክትል ስራ አስኪያጁ አክለዋል።