ኦነግና ኦዴፓ የእርቀ ሰላም ውይይት አካሂደዋል

የኦነግና የአዴፕ የእርቀ ሰላም ውይይት

በኦሮሞ ነፃነት ግንባርና በመንግስት መካከል የተከሰተውን አለመግባበበት ለማስታረቅ የተቋቋመው የእርቅና የሰላም ኮሚቴ ዛሬ ሁለተኛ ስብሰባውን በአምቦ ዩኒቨርሲቲ ግቢ ውስጥ አካሂዷል።

የኦነግ ሊቀመንበር አቶ ዳዉድ ኢብሳ፣ የኦዴፓ ከፍተኛ አመራሮች፣ አባገዳዎችና ምሁራን በተሳተፉበት ስብሰባ፤ ኮሚቴው ሁለቱም ወገኖች ለሰላም በቁርጠኝነት እንዲሠሩና ሰላም በዘላቂነት እንዲወርድ ውሳኔ አስተላልፏል።

"በረከትና ታደሰ በሙስና መጠርጠራቸው አስደንቆኛል" አቶ ጌታቸው ረዳ

የጂግጂጋ ነዋሪ ጥንዶች ስጋት ላይ ነን እያሉ ነው

በእርቀ-ሰላም ጉባዔው ከተላለፉት ዋና ዋና ውሳኔዎች መካከል፦

• ማንኛውም ዓይነት ፕሮፓጋንዳ በሁለቱም በኩል እንዲቆምና ቅሬታ ቢኖራቸው እንኳን ለኮሚቴው ማቅረብ እንጂ ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠት እንደማይችሉ፤

• ኦነግ ወታደሮቹን በ20 ቀናት ውስጥ ወደ ካምፕ ጠቅልሎ እንዲያስገባና ወታደሮቹ የጀግና አቀባበል እንዲደረግላቸው፤

• ወታደሮቹ ወደ ካምፕ በሚገቡቡት ወቅት ምንም ዓይነት ችግር እንዳይፈጠር የሃገር መከላከያ ሰራዊት አባላት ለሶስት ተከታታይ ቀናት ጥበቃ እንዲያደርጉ፤

• ወታደሮቹ የሚሠፍሩባቸው ካምፖች ከዚህ በፊት ችግር ተነስቶባቸው ከነበሩ ቦታዎች የራቁ እንዲሆኑና ኮሚቴው በማንኛውም ሰዓት ሄዶ መጎብኘት እንዲችል፤

• ወታደሮቹ በካምፕ ውስጥ ከሁለት ወራት በላይ እንዳይቆዩ፤

በተካሄደው የእርቅ ውይይትም በኦሮሞ ባህል መሰረት ኮርማ በሬ ታርዶ ሰላም እንዲወርድ ሁሉም መስማማታቸውን በቦታው የተገኘው ባልደረባችን ነግሮናል።

የኦሮሞ አባገዳዎች ምክር ቤት ዋና ሰብሳቢ አቶ በየነ ሰንበቶ ''የመጨረሻው እርቅ ተካሂዷል፤ ሰላምም ወርዷል'' ብለዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የኮሚቴው አባል አቶ ሃይሌ ገብሬ ደግሞ ''ከዛሬ በኋላ ለነጻነት በሚል የሚተኮስ አንድም ጥይት አይኖርም" ሲሉ ተደምጠዋል።

በምዕራብ ኦሮሚያ የኦነግ ጦር አዛዥ ስለወቅታዊው ሁኔታ ምን ይላል?

ኦዲፒ፡ ኦነግ እንደ አዲስ ጦር መልምሎ እያሰለጠነ ነው

የኦሮሞ ፌዴራል ኮንግረስ ምክትል ሊቀ መንበር አቶ በቀለ ገርባ በበኩላቸው ይህ ውሳኔ የመጨረሻ ስለሆነ ውሳኔውን የማይቀበል አካል ኦሮሚያ ውስጥ መኖር አይችልም ብለዋል።

ኮሚቴው ያሳለፈውን ውሳኔ መንግሥት ሙሉ በሙሉ የሚቀበለው መሆኑን የተናገሩት ደግሞ መንግሥትን ወክለው የኮሚቴው አባል የሆኑት አቶ ሞገስ ኢደኤ ናቸው።

አክለውም በአጭር ጊዜ ውስጥ የኦነግን ሰራዊት ብንቀበል ደስውታውን አንችለውም ብለዋል።

የአምቦ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት ዶክተር ታደሰ ቀነአ፤ ሁሌም ችግር ሲፈጠር የሚጎዳው ህዝቡ ስለሆነ ለህዝቡ ሰላም ሲባል ሁለቱም ወገኖች ሁሉንም ነገር ትተው እጅ ለእጅ ተያይዘው መስራት እንዳለባቸው አሳስዋል።