በረከት ስምኦን ከየት ተነስተው እዚህ ደረሱ

በረከት ስምኦን Image copyright AFP

አቶ በረከት ስምኦን ወታደራዊውን መንግሥት ከሥልጣን ያስወገደው የትጥቅ ትግል ውስጥ በተለያዩ ቡድኖች ውስጥ ከተሳተፉ አንጋፋ ታጋዮች መካከል የሚጠቀሱ ናቸው።

ከትጥቅ ትግሉ ማብቃት በኋላ በተለያዩ የፓርቲውና የመንግሥት ከፍተኛ ኃላፊነቶች ላይ ያገለገሉ ሲሆን ጎልተው መውጣት የጀመሩት ግን በ1993 የኢህአዴግ ዋነኛ አካል በነበረው ህወሓት ውስጥ የተከሰተውን ክፍፍል ተከትሎ በበላይነት የወጡት የወቅቱ የድርጅቱ ሊቀ መንበርን አቶ መለስ ዜናዊን ደግፈው ከቆሙ በኋላ ነበር።

በወቅቱ ቁልፍ በፓርቲውና በመንግሥት ኃላፊነቶች ላይ ከፍተኛ ሚና የነበራቸው አንጋፋ የህወሓት አመራር አባላት ይዘውት ከነበሩበት ቦታ ገለል ሲደረጉ ክፍተቱን ለመሸፈን ወደፊት ከመጡትና የጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ የቅርብ ሰው ለመሆን ከቻሉት ሰዎች መካከል አቶ በረከት ቀዳሚው ናቸው።

አቶ በረከት ስምኦን ሥልጣን ለመልቀቅ ጥያቄ አቀረቡ

አቶ በረከት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ቀጥለው በፓርቲውና በመንግሥት ጉዳዮች ላይ በተለያዩ መድረኮች ላይ ወጥተው የሚናገሩ ሁለተኛው ሰው ናቸው። ሃሳባቸውን አደራጅተው በመናገርና የፓርቲውን የርዕዮተ ዓለም የመንግሥትን ፖሊሲዎች በመተንተን በኩልም ከሌሎች ባለሥልጣናት ጎልተው የሚታዩ መሆናቸውም ይነገርላቸዋል።

ለፓርቲው ቅርበት ያላቸው ሰዎች እንደሚናገሩትም የኢህአዴግ የርዕዮተ ዓለም ልሣን በሆነችው "አዲስ ራዕይ" መጽሔት ላይ በብዕር ስም ከሚጽፉት ከአቶ መለስ ዜናዊ ቀጥለው ወቅታዊና ፖለቲካዊ ትንታኔዎችን ከሚያዘጋጁ ጥቂት ሰዎች መካከል አቶ በረከት አንዱ ናቸው።

በ1997 የተካሄደውና ለበርካታ ሰዎች ሕይወት ማለፍና ሃገሪቱን ወደ ከባድ ቀውስ አድርሷት በነበርው ምርጫ ወቅት አቶ በረከት ዋነኛው የኢህአዴግ ፊት ነበሩ።

በቅድመ ምርጫ ወቅት በተካሄዱ ክርክሮች ላይ ከሌሎቹ የፓርቲው ተወካዮች በተለየ የኢህአዴግን ፖሊሲዎች ይዘው ሲከራከሩ እንደነበር ይታወሳል። ከዚያም በኋላ በተከሰቱት አወዛጋቢ ጉዳዮች ዙሪያ በሁሉም መድረኮች ላይ ለማለት በሚያስደፍር መልኩ በረከት ከፊት ቀዳሚ ነበሩ።

በደብረማርቆስ 'ባለስልጣኑ አርፈውበታል' የተባለው ሆቴል ጥቃት ደረሰበት

አቶ በረከት በ1997 ምርጫ ሰሜን ወሎ ቡግና ውስጥ ፓርቲያቸውን ወክለው የተወዳደሩ ሲሆን በቀዳሚው የምርጫ ውጤት በተቃዋሚ ተፎካካሪያቸው መሸነፋቸው ተነግሮ ቢሆንም ፓርቲያቸው ያቀረበውን ቅሬታ ተከትሎ በተደረገው የድጋሚ ምርጫ ወደ ምክር ቤት ለመግባት ችለዋል።

ድርጅታቸውን ኢህአዴግንና እርሳቸውን ለሚተቹና ለሚቃወሙ ሰዎች ትዕግስት እንደሌላቸው የሚነገርላቸው አቶ በረከት በተለይ ጋዜጠኞችን ቢሯቸው ድረስ ጠርተው እንደሚያስጠነቅቁና ጠንከር ያሉ ቃላትን ይሰነዝሩ እንደነበር ችግሩ የደረሰባቸው ይናገራሉ።

አንዳንዶች ደግሞ አቶ በረከት በሃገሪቱ የነፃ ፕሬስ እንቅስቃሴ እንዲዳከምና ለጋዜጠኞች መታሰርና ከሃገር መሰደድ ቁልፍ ሚና እንደነበራቸው በተለያዩ አጋጣሚዎች ስማቸውን ሲያነሱ ቆይተዋል።

አቶ በረከት ማናቸው?

አቶ በረከት ስምኦን ጎንደር ውስጥ ነዋሪ ከነበሩ ከኤርትራዊያን ቤተሰቦቻቸው ጎንደር ውስጥ ተወልደው እንዳደጉ ይነገራል። ቤተሰቦቻቸው ያወጡላቸው ስም መብራህቱ ሲሆን የአባታቸው ስም ደግሞ ገብረሕይወት እንደሆነ በቅርብ የሚያውቋቸው ሰዎች ይናገራሉ።

በቀዳሚነት የታላቅ ወንድማቸውን ፈለግ በመከተል የኢህአፓ አባል ሆነው ወደ ትግሉ ከገቡ በኋላ የስም ለውጥ እንዳደረጉም እነዚሁ ሰዎች ያስታውሳሉ። ስማቸውን ለምን እንደለወጡ የሚታወቅ ነገር ባይኖርም የሌላ ታጋይ ስም እንደወሰዱ ግን ይነገራል።

አቶ በረከት ስምኦን ከብአዴን ማእከላዊ ኮሚቴ አባልነት ታገዱ

ይህም በረከት ስምኦን የሚባል የኢህአፓ ታጋይ እንደነበርና በትግሉ ወቅት ባልታወቀ ምክንያት ከትግሉ ሜዳ ድንገት በመሰወሩ በርካታ የኢህአፓ አባላት የተገደለ መስሏቸው ነበር። በነበረው ልምድም ይህን ታጋይ ለማስታወስ መብራህቱ ገብረህይወት በረከት ስምኦን የሚለውን ሙሉ ስም እንደወሰደ ይነገራል።

አቶ በረከት ከየት ወደየት?

አቶ በረከት ስምኦን ወደ ትግል የገቡት በመጀመሪያ የኢህአፓ አባል ሆነው ሲሆን ድርጅቱ በዋናነት ከደርግና ከሌሎች ተቀናቃኝ ድርጅቶች በገጠመው ጥቃት በተዳከመበት ወቅት በውስጡ የተፈጠረውን መከፋፈል ተከትሎ ከሌሎች ጓዶቻቸው ጋር ድርጅቱን ጥለው ወጡ።

ከኢህአፓ የተለዩት አቶ በረከት ከትግሉ ጠቅልለው ግን አልወጡም ከጓዶቻቸው ጋር ብዙም ያልቆየውን ኢትዮጵያ ኮሚኒስት ፓርቲ (ኢኮፓ) አቋቁመው የነበረ ሲሆን ቀጥለውም አሁን የአማራ ክልል ገዢ ፓርቲ የሆነው አዴፓ መነሻ የሆነውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄን (ኢህዴን) በመመሥረት ከህወሓት ጋር ግንባር ፈጥረው ደርግን ታግለዋል።

"...ባለሐብቶችን ለቅመህ እሰር ብሎኝ ነበር" አቶ መላኩ ፈንታ

ከደርግ ውድቀት በኋላ የብሔር ድርጅቶች ጎልተው በመውጣታቸው ኢህዴን የአማራ ሕዝብ ውክልናን ለመውሰድና ተቀባይነትን ለማግኘት እራሱን የብሔረ አማራ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ኢህዴን) በሚል ስያሜ እራሱን መልሶ አዋቅሮ ለረዥም ዓመታት የኢህአዴግ አባል ፓርቲ በመሆን ቆይቷል።

አቶ በረከት ስምኦንም በብአዴን ውስጥ ቁልፍ ሚና ከነበራቸው ሰዎች መካከል ቀዳሚው በመሆን ቆይተዋል። በኢህአዴግ ውስጥም የብአዴን ዋነኛ ሰው በመሆን አድራጊ ፈጣሪ እንደነበሩ ይነገራል።

አቶ በረከት የነበሩባቸው ቁልፍ የመንግሥት ኃላፊነቶች

  • የማስታወቂያ ሚኒስትር
  • የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ሚኒስትር
  • የጠቅላይ ሚንስትሩ የፖሊሲ ጥናት እና ምርምር አማካሪ ሚንስትር
  • በሚኒስትር ማዕረግ የፖሊሲ ጥናትና ምርምር ማዕከል ምክትል ዋና ዳይሬክተር
  • የኢትዮጵያ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ቦርድ ሰብሳቢ
  • የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የቦርድ ሊቀ መንበር

የአቶ በረከትና ፓርቲያቸው

አቶ በረከት ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ህልፈት በኋላ በስፋት ይታዩበት ከነበረው የፖለቲካ መድረክ የራቁ ሲሆን በፖሊሲ አማካሪነትና በጥናትና ምርምር ከማዕከል ውስጥ ተገድበው ቆይተዋል።

በ2010 ዓ.ም መጀመሪያ ወራት ውስጥም ሳይታሰብ ድንገት ምክንያታቸውን ባልገለጹበት ሁኔታ ለጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማሪያም ደሳለኝ መልቀቂያ ማስገባታቸው ሲነገር ተመልሰው የመነጋገሪያ ርዕስ ለመሆን ችለው ነበር። ነገር ግን ከጥቂት ጊዜ በኋላ ያቀረቡትን መልቀቂያ በማንሳት ወደ ሥራ መመለሳቸውን አሳውቀው ነበር።

ከዶ/ር ብርሃኑ ነጋ ጋር የፍቅር ግንኙነት አለዎት?

በሃገሪቱ ለዓመታት የዘለቀው ሕዝባዊ ተቃውሞ ከፍተኛ ደረጃ ላይ በደረሰበት ጊዜ የጠቅላይ ሚኒስትሩን ሥልጣን መልቀቅ ተከትሎ በፓርቲያቸው ኢህአዴግ ውስጥ የተካሄደው ለውጥ በእናት ድርጅታቸው ብአዴን ውስጥም ለውጥን አምጥቷል።

ይህ ለውጥ ግን ለአቶ በረከት አዎንታዊ ነገርን ይዞ የመጣ አልነበረም። ባለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ላይ የድርጅታቸው ማዕከላዊ ኮሚቴ አመራር በነበሩበት የጥረት ኮርፖሬት ላይ ፈጸሙት ባለው ጥፋት ከብአዴን ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት አግዷቸዋል።

ብአዴንም በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ ባካሄደው ጉባኤ ፓርቲውን በድጋሚ መልሶ በማዋቀር ለሁለተኛ ጊዜ የስም ለውጥ አድርጎ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) የሚል ስያሜን ያዘ።

አቶ በረከትም ከፓርቲው ከታገዱ በኋላ እራሳቸውን ያግልሉ አሊያ ይባረሩ በይፋ ሳይገለጽ በለውጡ ሂደት ከፓርቲው ወደ ጎን ተገፍተው ቆይተዋል።

በመጨረሻም ፈጸሙት ከተባለው ጥፋት ጋር በተያያዘ አዲስ አበባ ውስጥ ከሚገኘው ቤታቸው ጥር 15/2011 ዓ.ም ተይዘው ከድርጅቱ አብረዋቸው ታግደው ከነበሩት አቶ ታደሰ ካሳ ጋር ወደ ባህርዳር ተወስደዋል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ