አቶ በረከትና አቶ ታደሰ በባህር ዳሩ ፍርድቤት

ባህር ዳር

ረቡዕ እለት ከአዲስ አበባ በፖሊስ ተይዘው የነበሩት አቶ በረከት ስምኦንና አቶ ታደረሰ ካሳ ዛሬ ባህር ዳር ውስጥ ፍርድ ቤት ቀረቡ።

ሁለቱ ግለሰቦች ባህር ዳር በሚገኘው የባህርዳር አካባቢ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቀረቡ ሲሆን አቃቤ ህግ ለምርመራ የ14 ቀናት የጊዜ ቀጠሮ ጠይቆ ነበር።

አቶ በረከትና አቶ ታደሰ ለምን ከአዲስ አበባ ተይዘው ጉዳያቸው ባህር ዳር ውስጥ እንዲታይ እንደተደረገና ዋስትና ተሰጥቷቸው ጉዳያቸውን በውጪ ሆነው እንዲከታተሉ ጠይቀው ነበር።

"በረከትና ታደሰ በሙስና መጠርጠራቸው አስደንቆኛል" አቶ ጌታቸው ረዳ

አቃቤ ሕግም የተጠረጠሩበት ጥፋት የተፈፀመው በአማራ ክልል ውስጥ በመሆኑ ጉዳያቸው መታየት ያለበት ባህር ዳር ውስጥ እንደሆነ ጠቅሶ የተጠረጠሩበት ድርጊት ከባድ በመሆኑና በዋስትና ቢለቀቁ መረጃና ሰነዶችን ሊያጠፉ ይችላሉ በማለት ጥያቄታቸውን ተቃውሞታል።

ጉዳዩን ለመመልከት የተሰየሙት ዳኞችም ለጥቂት ደቂቃዎች በቀረቡት ጥያቄዎችና መልሶች ላይ ከመከሩ በኋላ አቃቤ ህግ የጠየቀውን የጊዜ ቀጠሮ በመፍቀድ አቶ በረከትና አቶ ታደሰ በእስር ቤት እንዲቆዩ ወስኗል።

አቶ በረከት ስምኦን እና አቶ ታደሰ ካሳ ወደ ባህር ዳር ተወሰዱ

የሁለቱ ተጠርጣሪዎችን ጉዳይ ለመመልከትም ለየካቲት 01/2011 ቀጠሮ ሰጥቷል።

በዛሬው የመጀመሪያ ችሎት ለአቶ በረከትና አቶ ታደረሰ ክሳቸው በጽሑፍ ቀርቦላቸዋል። በክሱ ላይ አስተያየታቸውን የተጠየቁት አቶ በረከት ሕገ መንግሥቱንና የፍትህ ሥርዓቱን በሚፃረር መልኩ ችግር እንደገጠማቸው ተናግረዋል።

"ባለሁበትና በሌለሁበት በተደጋጋሚ የደቦ ፍርድ ገጥሞኛል" ያሉት አቶ በረከት በደብረ ማርቆስ ከተማ የገጠማቸውን ችግር በምሳሌነት አንስተዋል። ትናንት ለምርመራ በፖሊስ ጣቢያ ሲንቀሳቀሱ "ሌባ፣ ነፍሰ ገዳይና ወንጀለኛ" ሲባሉ እንደነበርም በተጨማሪም ትናንት ፍርድ ቤት ያልቀረቡት የፀጥታ ስጋት አለ ተብሎ እንደሆነም ተናግረዋል።

ቤተሰቦቻቸው የፍርድ ሂደታቸውን እንዳይከታተሉ መደረጉንና የቀረበባቸውን ክስ ጠበቆች ይዘው ለመከራከር ዝግጁ እንደሆኑ እንዲሁም ጉዳያቸውን ውጪ ሆነው መከታተል እንዲችሉ አቶ በረከት ፍርድ ቤቱን ጠይቀዋል።

በረከት ስምኦን ከየት ተነስተው እዚህ ደረሱ

"ያለ ፍርድ ቤት ተፈርዶብኝ የታሰርኩ ያህል ይሰማኛል" ያሉት አቶ ታደሰ ካሳ ደግሞ በባለሥልጣናት እና በመገናኛ ብዙሃን "ሌቦች እና ዘራፊዎች" መባላቸውን ጠቅሰው በቀረበባቸው ክስ ላይ ለመከራከር ዝግጁ መሆናቸውን ተናግረዋል።

አክለውም "ጉዳዩ ከ90 በመቶ በላይ ተጠናቋል ስለተባልን የ14 ቀን ቀጠሮ መጠየቅ ተገቢ አይደለም" ብለው ውጪ ሆነው መከራከር እንዲችሉ እንዲፈቀድላቸው ጠይቀዋል።

አቶ ታደሰ በተጨማሪም የዳሽን ቢራ ዋና መሥሪያ ቤት አዲስ አበባ በመሆኑ ጉዳያቸው ከባህር ዳር ይልቅ አዲስ አበባ እንዲታይ አመልክተው ፤ በሽተኛ መሆናቸውንና ቤተሰባቸውም ያለው አዲስ አበባ መሆኑን ጠቅሰው ምግብም በሥርዓት እየቀረበላቸው አለመሆኑን ተናግረዋል።

አቃቤ ሕግ በበኩሉ የተጠረጠሩበት ወንጀል ሰፊ ምርመራ እና በተለያዩ አካባቢዎች ያሉ ምስክሮችን ማናገር ስለሚያስፈልግ የተጠየቀው የጊዜ ቀጠሮ እንዲፈቅድ ጠይቋል።

በተጠርጣሪዎቹ ለተነሱት የተለያዩ ጥያቄዎች አቃቤ በሰጠው ምላሽም ትናንት ፍርድ ቤት ፋይል ቢከፈትም ጊዜው ስላልበቃ እንዳልቀረቡ፣ ከምግብ ጋር ተያይዞ አቅም በሚችለው ሁኔታ አየቀረበ መሆኑንና ቤተሰቦቻቸው ምግብ እንዲያቀርቡ እንደሚመቻች ገልጿል።

ግራ ቀኙን የተመለከተው ፍርድ ቤትም ተመዘበረ የተባለው ሃብት የክልሉ በመሆኑ የክልሉ ፍርድ ቤት ጉዳዩን ማየት እንደሚችልና ከተፈፀመው ወንጀል ከባድነት እና ከሰነድ ማሰባሰብ አንፃር የ14 ቀን ቀጠሮውን ፈቅዷል።

ፍርድ ቤቱ ጨምሮም ግለሰቦቹ የነበራቸውን ስልጣን ከግምት በማስገባት ልዩ ጠበቃ የሚያስፈለልጋቸው መሆኑን ጠቅሶ ጥንቃቄና አስፈላጊው ጥበቃ እንዲደረግላቸው ትዕዛዝ ሰጥቷል።

ተያያዥ ርዕሶች