አሜሪካ የቬንዙዌላ መንግሥትን አሰጠነቀቀች

የቬንዚዌላ ፕሬዚዳንት ኒኮላስ ማዱሮ በጦር ልምምድ ላይ Image copyright EPA
አጭር የምስል መግለጫ የቬንዚዌላ ፕሬዚዳንት ኒኮላስ ማዱሮ በጦር ልምምድ ላይ

አሜሪካ በዲፕሎማቶቿ እና በተቃዋሚ መሪው ጁአን ጉአኢዶ ላይ የሚደርሱ ማናቸውም አይነት ማስፈራሪያዎች ''የማያዳግም እርምጃ ያስወስዳሉ'' ስትል የቬንዙዌላ መንግሥትን አስጠነቀቀች።

የብሔራዊ ደህንነት አማካሪው ጆን ቦልተን ማስፈራራት የሕግ ጥሰት ነው ሲሉ ተናግረዋል።

ተቃዋሚው ጁአን ጉአኢዶ የቬንዙዌላ ጊዜያዊ ፕሬዚዳንት አድርገው እራሳቸውን መሾማቸውን ተከትሎ አሜሪካ እና ካናዳን ጨምሮ ከ20 ሃገራት በላይ እውቅና ማግኘታቸው ይታወሳል።

ማዱሮ የቬንዝዌላ ምርጫን አሸነፉ

እሁድ ጠዋት በአሜሪካ የቬንዙዌላ ጦር ከፍተኛ ተወካይ የሆኑት ኮሎኔል ጆሴ ሉዊስ ሲልቫ ለተጠባባቂው ፕሬዚዳንት እውቅና በመስጠት የማዱሮን መንግሥት ክደዋል።

የቬንዙዌላው ፕሬዚዳንት ኒኮላስ ማዱሮ የሃገሪቱ ጦር፣ ሩሲያ እና ቻይና ከእሳቸው ጎን መሆናቸውን በተደጋጋሚ ገልጸዋል።

እራሳቸውን ጊዜያዊ ፕሬዚዳንት ብለው የሰየሙት ጁአን ለረቡዕ እና ቅዳሜ ለተቃውሞ ሰልፍ ደጋፊዎቻቸውን አደባባይ ጥርተዋል።

ስፔን፣ ጀርመን፣ ፈረንሳይ እና እንግሊዝን ጨምሮ በርካታ የአውሮፓ ሃገራት በቬንዙዌላ በስምንት ቀናት ውስጥ ምርጫ ካልተጠራ ለተቃዋሚው የፕሬዚዳንትነት እውቅና እንሰጣለን ብለዋል።

ቬኔዙዌላ ምናባዊ ገንዘብ ይፋ አደረገች

ፕሬዚዳንት ማዱሮ ግን የአውሮፓውያኑን ሃገራት ማስጠንቀቂያ አጣጥለውታል።

''ቬንዙዌላ ከአውሮፓ ሃገራት ጋር ጠንካራ ቁርኝት የላትም። ይህ ከፍተኛ ንቀት ነው'' ሲሉ ለሲኤንኤን ቱርክ ትናንት ተናግረዋል።

ፕሬዚዳንት ማዱሮ እሁድ ዕለት የጦር ልምምድ ላይ የተገኙ ሲሆን ''አንድነት፣ ሥነ ሥርዓት እና መግባባት'' ያስፈልጋናል ያሉ ሲሆን፤ በተቃዋሚው ጉአኢዶ አማካይነትወ የመፈንቅለ መንግሥት ሙከራ እየተፈጸመ ነው ብለዋል።

አሜሪካ ለተቃዋሚው እውቅና መስጠቷን ተከትሎ ማዱሮ ከአሜሪካ ጋር ያላቸውን ግንኙነት በማቋረጥ የአሜሪካ ዲፕሎማቶች በሦስት ቀናት ውስጥ ቬንዙዌላን ለቀው እንዲወጡ ትዕዛዝ ሰጥተዋል።

ካናዳ የቬንዝዌላን አምባሳደር አባረረች

ማዱሮ ያስቀመጡት ቀነ ገደብ ቅዳሜ እለት ሊያበቃ ሲቃረብ የቬንዙዌላ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ዲፕሎማቶቹን ከሃገር የማባረር ዕቅዱ ውድቅ መደረጉን በመጠቆም የሁለቱ ሃገራት ፍላጎት ማስፈጸሚያ ቢሮዎች በ30 ቀናት ውስጥ እንዲከፍቱ ይደረጋል ሲል አስታውቋል።

ሁለት ሃገራት ዲፕሎማሲያዊ ግነኙነት ሳይኖራቸው ሲቀር ፍላጎላት ማስፈጸሚያ ቢሮዎች እንዲከፈቱ ይደረጋል።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ