'ለሼህ አላሙዲ መፈታት የጠቅላይ ሚንስትሩ አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነበር'

'ለሼህ አላሙዲ መፈታት የጠቅላይ ሚንስትሩ አስተዋጽኦ ከፍተኛ ነበር' Image copyright IBTime

በትውልድ ኢትዮጵያዊ እና የሳዑዲ ዜግነት ያላቸው ቢሊየነሩ ሼህ ሞሐመድ ሁሴን አሊ-አላሙዲ ትናንት ከእስር ከተለቀቁ በኋላ ከሪያድ ወደ ጅዳ በማቅናት ከቤተሰባቸው ጋር ተቀላቅለዋል።

የሳዑዲ መንግሥት ያካሄደውን የፀረ-ሙስና ዘመቻን ተከትሎ ከበርካታ ንጉሣዊ ቤተሰቦች እና ከበርቴዎች ጋር ተይዘው ከ14 ወራት በላይ በእስር ያሳለፉት አላሙዲ እንዲፈቱ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን ጠበቃቸው አቶ ተካ አስፋው ለቢቢሲ ተናገረዋል።

አቶ ተካ ''ትናንት (እሁድ) በስልክ ተገናኝተናል። ጤናቸው በጣም ጥሩ ሁኔታ ላይ ይገኛል። ከቤተሰቦቻቸው ጋርም ተቀላቅለዋል'' ያሉ ሲሆን ወደ ኢትዮጵያ መቼ ሊመጡ ይችላሉ ተብለው ለተጠየቁት ''ወደ ኢትዮጵያ መምጣቸው አይቅርም፤ ነገር ግን መቼ እንደሚመጡ በእርግጠኝነት መናገር አልችልም'' ሲሉ የአላሙዲ ጠበቃ አቶ ተካ አስፋው ተናግረዋል።

አቶ በረከትና አቶ ታደሰ ፍርድ ቤት ቀርበው ምን አሉ?

ካለፈው ግንቦት 2009 ዓ.ም ጀምሮ አሊ-አላሙዲ ከእስር እንዲፈቱ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ጥረቶችን ሲያደርጉ እንደቆዩ የሚናገሩት አቶ ተካ ''ጠቅላይ ሚንስትራችን ከአንዴም ሁለቴ ቦታው ድረስ ተገኝተው ከሳዑዲ ባለስልጣናት ጋር ውይይት አድረገዋል። ከዚያም በኋላ በነበራቸው ግንኙነት ከፍተኛ ጥረት እንዳደረጉ ነው የምናውቀው። ለመፈታታቸው የእሳቸው ጥረት እንዳለበት ነው የተረዳነው'' ብለዋል።

የጠቅላይ ሚንስትሩ ጽ/ቤት የፌስቡክ ገጽ የባላሃብቱን ከእስር መፈታት ይፋ ባደረገበት ጽሁፍ፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ ግንቦት 2010 ዓ.ም ሞሐመድ ሁሴን አሊ-አላሙዲ ከእስር ለማስፈታት ጥረት እየተደረገ መሆኑን እና በቅርቡም ወደ አገራቸው ይመለሳሉ በማለት በሚሊኒያም አደራሽ ያደረጉትን ንግግር አስታውሷል።

የጠቅላይ ሚንስትሩ ጽ/ቤት ጨምሮም አሊ-አላሙዲ በሰላም እንዲመለሱ መልካም ምኞታችንን አንገልጻለን በማለት አስፍሯል።

ከ14 ወራት በፊት ከአላሙዲ ጋር በሙስና ወንጀሎች ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር ውለው ከነበሩት መካከል ጥቂት የማይባሉ ከበርቴዎች መጠኑ በይፋ ያልተገለጸ ነገር ግን ካላቸው ሃብት ከፍተኛ መጠን ያለውን ገንዘብ ለሳዑዲ መንግሥት ሰጥተው ከወራት በፊት ከእስር መውጣታቸው ይታወሳል።

"ሌሎች ሴቶች ላይ የአሲድ ጥቃት ሳይ ይረብሸኛል፤ ህመሜን ያስታውሰኛል" ካሚላት መህዲ

ከዚህ አንጻር ሼህ አላሙዲንም ከእስር ለመፈታት ከፍተኛ ገንዘብ ከፍለዋል ወይ ተብለው የተጠየቁት ጠበቃቸው አቶ ተካ ''ከፍለዋል ብዬ ለመናገር ይከብደኛል። የተፈቱበትን አኳኋን ዝርዝር ሁኔታ ሰለማላውቅ ይሄ ነው ብዬ መናገር አልችልም። እኔ ግን ከፍተኛ ገንዘብ ከፍለዋል ብዬ አላምንም። ጠቅላይ ሚንስትሩ ግን ለመፈታታቸው የማይናቅ አስተዋጽኦ አበርክተዋል'' ብለዋል።

ጥቂት ስለሼህ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አላሙዲ

እንደ ፎርብስ መጽሔት ከሆነ ሼህ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ ከሳዑዲ ዜጋው አባታቸው እና ከኢትዮጵያዊት እናታቸው በደሴ ከተማ ነው የተወለዱት።

ፎርብስ የአሊ አል-አሙዲን እድሜን 72 የሚያደርስ ሲሆን የሃብት ምንጫቸውን ሲገልጽ ''የነዳጅ ዘይት፣ የተለያዩ ምንጮች እና በእራሳ ጥረት'' ሲል ያስቀምጠዋል።

የሳውዲ አረቢያ ዜግነት ያላቸው ሼህ ሞሃመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ ቋሚ የመኖሪያ አድራሻቸው ጂዳ ሳዑዲ አረቢያ ሲሆን፤ መጋቢት 2017 በነበረው በፎርብስ የቱጃሮች ዝርዝር ውስጥ አሊ አል-አሙዲ የተጣራ 10.3 ቢሊዮን ዶላር ንብረት በስማቸው በማስመዝገብ ከዓለም 159 ደረጃ ላይ ተቀምጠው ነበር።

ይሁን እንጂ ፎርብስ እአአ ማርች 2018 ላይ ሼህ ሞሃመድ ሁሴን አል-አሙዲን ሃብታቸው የትኛው እንደሆነ በትክክል ማጣራት አልቻልኩም በማለት ከቢሊየነሮች ዝርዝር ውስጥ ሰርዟቸዋል።

ሳዑዲ ለሮቦት ዜግነት ሰጠች

የደርግ ሥርዓት ተወግዶ ኢህአዴግ አገሪቷን ከተቆጣጠረ በኋላ ወደ ትውልድ ሃገራቸው በመምጣት መዋዕለ ንዋያቸውን የፈሰሱት ሼህ ሙሐመድ ሁሴን አሊ አል-አሙዲ፤ በኢትዮጵያ በተለያዩ የመዋዕለ ነዋይ ዘርፎች ተሰማርተው ግዙፍ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴን የሚያካሂዱ በርካታ ኩባንያዎች አሏቸው።

ሼህ ሙሐመድ የሐብት ምንጭ በዋነኛነት የነዳጅ ዘይት ይሁን እንጂ በማዕድን፣ በግብርና፣ በሆቴል፣ በግንባታ፣ በሪልስቴት፣ በሆስፒታል፣ በሥልጠናና ምርምር፣ በፋይናንስ እና በመሳሰሉት ዘርፎች በተለይ በአሜሪካ፣ በአፍሪካ፣ በመካከለኛው ምሥራቅና በስዊድን ተሰማርተው ይገኛሉ።

ግለሰቡ በዓለም ዙሪያ ባሏቸው ኩባንያዎቻቸው ውስጥ ከ200 ሺ በላይ ለሆኑ ሠራተኞች ሥራ መፍጠር የቻሉ ሲሆን፤ በኢትዮጵያ የሚገኙ ተቋሞቻቸው ቁጥርም ከ70 በላይ መድረሱን በዚህም ከ40ሺ በላይ ለሚሆኑ ኢትዮጵያዊያን የሥራ ዕድል ማስገኘታቸውን መረጃዎች ያመለክታሉ።

ከውጪ ቋንቋዎች አረብኛ፣ እንግሊዝኛና ጣሊያንኛ ይናገራሉ። ከአገር ውስጥ ደግሞ አማርኛ እና ትግርኛ ቋንቋን አቀላጥፈው ይናገራሉ።

አላሙዲ በስዊዲንና ሞሮኮ የነዳጅ ማጣሪያዎችን በመግዛትና ቅርንጫፎችን በመክፈት ሥራቸውን ከማስፋፋታቸው በፊት በኮንስትራክሽን (ሪልስቴት) ዘርፍ ተሰማርተው ነበር። በአሁኑ ወቅት በስዊድን ስመጥር ከሆኑ የውጪ ባለሃብቶች መካከል የሚጠቀሱም ናቸው።

የንጉሣዊያን ቤተሰቦችና ቱጃሮች እስር

ከሳዑዲ አረቢያ መንግሥት ስለታሳሪዎቹ ማንነት ዝርዝር የሆነ ይፋዊ መግለጫ ባይሰጥም ከጥቅምት 26/2010 ዓ.ም ጀምሮ በሳዑዲ በሙስና ተጠርጥረው ታስረው የነበሩት ልዑላን፣ ሚኒስትሮችንና የቀድሞ ሚኒስትሮችን እንዲሁም ሼህ ሙሐመድ አሊ አላሙዲንን ጨምሮ ነጋዴዎች ይገኙበት ነበር።

በተለያዩ መስኮች ተሰማርተው በሚገኙት ግዙፍ ተቋሞቻቸው ውስጥ በሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ቀጥረው የሚያሰሩት የባለጸጋው አላሙዲን መታሰር በተሰማበት ጊዜ በድርጅቶቻቸው ውስጥ ስጋትና ግራ መጋባትን አስከትሎ ነበር።

ሳዑዲ ሴቶች እንዳያሽከረክሩ ጥላ የነበረችውን እገዳ ልታነሳ ነው

የባለሃብቱ ተቋማት ለሃገሪቱ ኢኮኖሚ ያላቸውን አስተዋጽኦ በተለያዩ አጋጣሚዎች ሲያወድስ የሚሰማው የኢትዮጵያ መንግሥትም፤ ግለሰቡ ድንገት መታሰር የተሰማውን ብዙም ሳይዘገይ ነበር ይፋ ያደረገው።

በወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ኃይለማርያም ደሳለኝ ከግለሰቡ መታሰር ከቀናት በኋላ ስልጣናቸውን ከቋፍ ላይ አድርሶት ከነበረው ሕዝባዊ ተቃውሞ ጋር አያይዘው በሰጡበት መግለጫ ላይ መንግሥታቸው ጉዳዩን በተመለከተ እጁን አጣምሮ እንዳልተቀመጠ ገልጸው ነበር።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስለአላሙዲ የእስር ምክንያት ባይናገሩም ''ሳዑዲ አረቢያ ሉዓላዊ ሃገር ነች እኛ ጣልቃ መግባት አንችልም። በዲፕሎማሲያዊ መንገድ ስለ ጉዳዩ ማጣራት እያካሄድን ነው" በማለት እስሩ በኢትዮጵያ ባላቸው ሥራ ላይ ምንም እንቅፋት እንደማይፈጥር መንግሥታቸው እምነቱ እነደሆነ ተነግረው ነበር።

ከወራት በኋላ ኃይለማሪያምን ተክተው የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን መንበር የተረከቡት ዐብይ አህመድም ወደ ሳዑዲ አረቢያ በተጓዙበት ወቅት ስለሼህ አላሙዲ ጉዳይ ከሃገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት ጋር መነጋገራቸውንና በቅርቡ ከእስር እንደሚወጡ ቃል እንደገቡላቸው ተናግረው ነበር።

ቢሆንም እንደተባለው ግለሰቡ ከእስር ሳይወጡ ለወራት ሳዑዲ አረቢያ ውስጥ ቆይተው ባለፈው ሳምንት መረሻ ላይ ነው መለቀቃቸው የተሰማው። ቢሆንም ግን የሼህ አላሙዲን የቅርብ ሰዎች ለቢቢሲ እንደተናገሩት ለግለሰቡ መፈታት የጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ሚና ከፍተኛ ነው።

ከእስሩ ጀርባ ያሉ ጥርጣሬዎች

በተለያዩ ዘርፎች ላይ ተሰማርተው የሚገኙ የሳዑዲ አረቢያ ሃያላን ግለሰቦችን ወደ እስር ቤት ወደተቀየረው ቅንጡው የሪትዝ ካርልተን ሆቴል ያስገባቸው የእስር ዘመቻ ከተካሄደ በኋላ የሳዑዲ መንግሥት ባወጣው መግለጫ የፀረ ሙሳና እንቅስቃሴው ''ገና የመጀመሪያው'' ነው በማለት ቀጣይነት እንደሚኖረው ፍንጭ ሰጥቶ ነበር።

ይህ እርምጃም የሳዑዲን የመንግሥት ከፍተኛ ስልጣን በቅርቡ የተቆናጠጡት ልዑል አልጋ ወራሽ ሞሐመድ ቢን ሰልማን አዲሱን የፀረ-ሙስና ቡድን በመምራት በሃገሪቱ ሊያመጡ ላሰቡት ለውጥ ምን ያህል ስልጣን እንዳላቸውና ተፅዕኖ መፍጠር እንደሚችሉ ያሳያል ተብሎ ነበር።

የዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕም የፀረ-ሙስና ቡድኑን ተግባር ደግፈዋል። ትራምፕ በትዊተር ገጻቸው ''በልዑል አልጋ ወራሹ ላይ ትልቅ መተማመን አለኝ የሚሰሩትን ያውቃሉ'' ሲሉ አስቀምጠው ነበር።

በሳዑዲ 'አንድ ወንድ እኩል ይሆናል ሁለት ሴት'

ሳዑዲ አረቢያን በቅርበት የሚያውቃት የቢቢሲው የደህንንት ዘጋቢ ፍራንክ ጋርድነር ከሙስና ጋር በተያያዘ በርካታ ቱጃሮች በቁጥጥር ሥር በዋሉበት ወቅት "አሁን በሳዑዲ አረቢያ እየተካሄደ ያለውን ማወቅ እና የወደፊቱን መገመት እጅግ አስቸጋሪ ነው። በሳውዲ ከ85 ዓመታት ወዲህ ታይቶ የማይታወቅ አይነት ለውጥ እየታየ ነው" ሲል ተናግሮ ነበር።

"የልዑሎቹ፣ የሚንስትሮቹ አልያም የነጋዴዎቹን እስር ከሦስት ዓመት በፊት ሆኖ ማሰብ አይቻልም ነበር" የሚለው ፍራንክ የልዑል አልጋ ወራሸ ሞሐመድ ቢን ሳላህ ወደ ስልጣን መምጣት ሃገሪቱን ወደተለየ አቅጣጫ እየወሰደ ይገኛልም ብሏል።

የዘመቻ እስሩ መካሄዱን ተከትሎ በታሳሪዎቹ ስም ተመዝግቦ የሚገኝ ገንዘብም ሆነ ንብረት እንዳይንቀሳቀስ እገዳ እንደተጣለ የሳዑዲ የማስታወቂያ ሚኒስቴር ገልጾ ነበር።

ከዚህ በተጨማሪም ዘመቻውን የሚያካሂደው የፀረ-ሙስና ቡድን በማንኛውም ግለሰብ ላይ የእስር ትዕዛዝ ማውጣት እና የጉዞ እገዳ የመጣል ስልጣን ተሰጥቶት ስለነበር ከእስር ውጪ የሚገኙ ባለስልጣናትና ባለሃብቶች በስጋት ውስጥ ከዓመት በላይ ቆይተዋል።

የሙስና ምርመራውና እስሩ በሃገሪቱ ስር እየሰደደ የመጣውን ችግር ለመዋጋት የተጀመረ እንደሆነ ቢነገርም፤ የፖለቲካ ተንታኞች ግን ዘመቻው በሳዑዲ ንጉሣዊያን ቤተሰቦች መካከል ባለ የፖለቲካ ሽኩቻ ልዑል አልጋ ወራሽ ሞሃመድ ቢን ሰልማን ስልጣን ለመቆጣጠር የወሰዱት እርምጃ ነው ይላሉ።

ልዑል አልጋ ወራሽ ሞሃመድ ቢን ሰልማን ማናቸው?

Image copyright Anadolu Agency
አጭር የምስል መግለጫ ልዑል አልጋ ወራሽ ሞሃመድ ቢን ሰልማን

ወላጅ አባታቸው እአአ 2015 ንጉሥ ከመሆናቸው በፊት የ33 ዓመቱ አልጋ ወራሽ ብዙዎች ዘንድ አይታወቁም ነበር።

አባታቸው ንጉሥ ከሆኑ በኋላ ግን ሞሐመድ ቢን ሳላህ በነዳጅ ሃብቷ በበለጸገችው ሳውዲ ከፍተኛ ተጽእኖ ፈጣሪ መሆን ችለዋል።

የአጎታቸው ልጅ የሆኑትን ሞሐመድ ቢን ናይፍን በመተካት ነበር ልዑል አልጋ ወራሽ ተደርገው የተሾሙት።

ሞሐመድ ቢን ሰልማን እአአ ነሃሴ 1985 በሪያድ የተወለዱ ሲሆን የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን ከኪንግ ሳዑድ ዩኒቨርሲቲ በህግ አግኝተዋል።

በ2009 ዓ.ም የሪያድ አስተዳዳሪ ለነበሩት ወላጅ አባታችው ልዩ አማካሪ ሆነው እስከተሾሙበት ጊዜ ድረስ ሞሐመድ ቢን ሰልማን በተለያዩ የሥራ ድርሻዎች የሳዑዲ አረቢያን መንግሥት አገልግለዋል።

ሞሐመድ ቢን ሰልማን ወደ ስልጣን መምጣት የጀመሩት በ2013 በሚንስትር ማዕረግ ልዑል አልጋ ወራሽ ተብለው ከተሰመዩ በኋላ ነበር።

ኻሾግጂ የዓመቱ ምርጥ ሰው ዝርዝር ውስጥ ተካተተ

ከዚያ በፊት የሞሐመድ ቢን ናይፍ አባት የሆኑት ናይፍ ቢን አብዱል አዚዝ መሞታቸውን ተከትሎ ሞሐመድ ቢን ሰልማን አልጋ ወራሽ ተብለው ተሰይመው ነበር።

ሞሐመድ ቢን ሰልማን የመከላከያ ሚኒስትር ሆነው ከተሾሙ በኋላ የመጀመሪያ እርምጃቸው የነበረው እአአ በ2015 የየመን ፕሬዝዳንት በሁቲ አማጺያን ተገፍተው ሃገር ጥለው ከተሰደዱ በኋላ፤ ከሌሎች የአረብ ሃገራት ጋር በመሆን የጦርነት ዘመቻ የመን ላይ መክፍት ነበር።

ከዚህ በተጨማሪም ሞሐመድ ቢን ሰልማን ንጉስ ሰልማንን በመወከል በተለያዩ የዓለም ሃገራት ይፋዊ የሥራ ጉብኝቶችን አድርገዋል። በቻይናና በሩሲያን የጎበኙ ሲሆን በዋሺንግተንም ከፕሬዝዳንት ትራምፕ ጋር ተገናኘተው መክረዋል።