በፔሩ የመሬት መንሸራተት 15 የሠርግ ታዳሚዎችን ገደለ

ጉዳት የደረሰበት ሆቴል ከአደጋው በኋላ Image copyright INDECI
አጭር የምስል መግለጫ ጉዳት የደረሰበት ሆቴል ከአደጋው በኋላ

በደቡብ ምሥራቅ ፔሩ ያጋጠመ የመሬት መንሸራተት በአንድ ሆቴል ላይ ባደረሰው አደጋ በሆቴሉ ውስጥ እየተከናወነ በነበረ የሠርግ ድግስ ላይ የታደሙ ቢያንስ 15 ሰዎችን መግደሉን ባለስልጣናት አስታወቁ።

በሆቴሉ አቅራቢያ የደረሰው የመሬት መንሸራተት የሠርግ ሥነ ሥርዓቱ ታዳሚዎች በፌሽታ ላይ የነበሩ ሰዎችን ያስተናግድ የነበረውን ሆቴል ግድግዳዎችና ጣራው እንዲደረመስ በማድረጉ ነው አደጋው የተከሰተው።

የሥራ እረፍት ወስዶ ውሃ አጣጭ ፍለጋ

እሁድ ዕለት በደቡብ አሜሪካዋ ሃገር ፔሩ አባንካይ ከተማ የደረሰውን አደጋ ተከትሎ ከሞቱት በተጨማሪ ከፍርስራሽ ውስጥ እንዲወጡ የተደረጉ 29 ሰዎች የመቁሰል አደጋ እንደደረሰባቸው ባለስልጣናት ተናግረዋል።

የሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን እንደዘገቡት አደጋው የደረሰው በአካባቢው እየጣለ በነበረው ከባድ ዝናብ ወቅት ነው።

አደጋው በደረሰበት ጊዜ በሆቴሉ ውስጥ 100 የሚደርሱ እንግዶች እንደነበሩ የፔሩ የአደጋ ጊዜ አገልግሎት ሃላፊ የሆኑት ዮርጌ ቻቬስ ለሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ገልጸዋል።

መስታወት መፃዒውን ጊዜ ለማየት እንደሚያስችል ያውቃሉ?

ጨምረውም ከሠርጉ ታዳሚዎች ውስጥ 50 የሚሆኑት በአደጋው ጊዜ ከተደረመሱት ግድግዳዎች ወደ አንዱ ተጠግተው ነበር ተብሎ እንደሚታመን ተናግረዋል።

የአደጋ ጊዜ መስሪያ ቤቱ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ያሰራጫቸው ምስሎች የነፍስ አድን ሰራተኞች በፍርስራሾች ውስጥ ፍለጋ ሲያደርጉና የተጎዱ ሰዎችን በቃሬዛ ሲያጓጉዙ የሚያሳዩ ናቸው።

"ጫትን ማገድ ፈፅሞ የሚቻል አይደለም" ዶ/ር ዘሪሁን መሃመድ

አደጋው የደረሰባት ከተማ አባንካይ ከንቲባ የሆኑት ጉይዶ ቻሁዋይላ እንደተናገሩት የነፍስ አድን ሰራተኞች በፍርስራሾች ውስጥ ተቀብረው የነበሩ ሰዎችን ለማውጣት አስፈላጊውን ሁሉ ጥረት አድረገዋል። ጨምረውም የመቁሰል አደጋ የደረሰባቸው ሰዎች በአቅራቢያ ወደሚገኝ ሆስፒታል መወሰዳቸውን ገልጸዋል።

አንድ የሃገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን አደጋው የደረሰበት ሆቴል የተገነባው ተዳፋት በሆነ ስፍራ ላይ በመሆኑ የተደረመሰው ግድግዳ ህንጻውን ከሚንሸራተት ጭቃና አለት ለመከላከል የተገነባ እንደነበር ዘግቧል።