ፍርድ ቤት የቀረበው የጤፍ ባለቤትነት ጉዳይ

የጤፍ ምርቱን ማሳ ላይ እየለየ ያለ ገበሬ Image copyright Getty Images

የኢትዮጵያ መንግሥት ከጤፍ ባለቤትነት ጋር በተያያዘ የሆላንድ ድርጀትን በዓለም አቀፉ የግልግል ፍርድ ቤት ሊከስ ነው። ድርጅቱና የኢትዮጵያ መንግሥት ከአስር ዓመታት በላይ የባለቤትነት ይገባኛል ንትርክ ውስጥ የቆዩ ሲሆን የዓለም አቀፉ የግልግል ፍርድ ቤት ውሳኔ የኢትዮጵያን ጥያቄ የሚመልስ እንዲሆን በመንግሥት በኩል ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው።

ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በጤፍ ጉዳይ ፍርድ ቤት የሚሟገተው 'ሄልዝ ኤንድ ፐርፎርማንስ ፉድ ኢንተርናሽናል' የተባለው የሆላንድ ድርጅት እንግሊዝ፣ ጣልያን፣ ቤልጂየም፣ ኦስትሪያና ሆላንድ ውስጥ የጤፍ ባለቤትነት ፈቃድ አለው።

ጤፍን ሰዳ የምታሳድደው ኢትዮጵያ

ፈይሳ ቲክሴና ወንድ ልጁ በቢሾፍቱ ከተማ የሚገኘው የጤፍ ማሳቸውን እየተንከባከቡ ነበር ያገኘናቸው። ጤፍ ለእነሱ ዋነኛ የገቢ ምንጭ ከመሆኑ ባለፈ የአብዛኛው ኢትዮጵያዊ ቋሚ ምግብ ነው።

ይህ ተክል ከአምላክ የተሰጠን ገጸ በረከት ነው ይላል ፈይሳ። "በክረምት ወራት መሬቱን በደንብ እናርሰውና ጤፍ እንዘራበታለን። ከሽያጩ የምናገኘው ገቢ ለእኔና ለቤተሰቤ ከበቂ በላይ ነው። ሥራዬን እየሰራሁ ልጆቼን አስተምርበታለሁ። ጤፍ ታላቅ ተክል ነው።"

ለብዙ ዘመናት እንደ ፈይሳ ያሉ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ጤፍን በማመረት ላይ ህይወታቸውን መስርተዋል። ከዚህ በተጨማሪም ከጤፍ የሚዘጋጀውን እንጀራ ጋግረው በማቅረብ ሥራ ላይ ተሰማሩ በርካቶች ናቸው።

አዲስ አበባ ውስጥ የሚገኘው የእንጀራ መጋገሪያ ምርቶቹን ወደ አሜሪካ ይልካል። ትልልቅ ማሽኖች የጤፍ ዱቄትና ውሃን ቀላቅለው መጋገሪያዎች ላይ ያዘጋጃሉ። ይሄ ሁሉ ሂደት ሰባት ደቂቃ ብቻ ነው የሚፈጀው።

ጤፍ ሃገሩ የት ነው? ደቡብ አፍሪካ? አውስትራሊያ? . . .

በዚህ ድርጅት ጤፍ ለእንጀራነት ብቻ ሳይሆን ዳቦ፣ፓስታ፣ ብስኩትና ፒዛ ለማምረት አገልግሎት ላይ ይውላል። ታዲያ የዚህ አይነት ምርቶችም ጭምር ናቸው በኢትዮጵያ መንግሥትና በሆላንዱ ድርጅት የይገባኛል ፍጥጫ መካከል ተጎጂ የሚሆኑት።

በብዙ የአውሮፓ ሃገራት እውቅና የተሰጠውን የሆላንድ ድርጅት የጤፍ ባለቤትነትና ምርቶችን የማከፋፈል መብትን ለማስነሳት የኢትዮጵያ መንግሥት ለአስራ አራት ዓመታት ሲታገል ቆይቷል።

Image copyright AFP

በፈረንጆቹ 2000 አካባቢ ኢትዮጵያ ከድርጅቱ ጋር ስምምነት ስትፈራረም የጤፍ ምርትን ማሳደግና የቴክኖሎጂ ሽግግርን ከግምት ውስጥ በማስገባት ነበር። ነገር ግን ለድርጅቱ የተሰጠው ፈቃድ ኢትዮጵያ የጤፍ ምርትን ወደ ውጪ ከመላክ ያግዳታል።

ይህን በተመለከተ አቶ ኤርሚያስ የማነብርሃን የኢትዮጵያ አእምሮአዊ ንብረት ጽህፈት ቤት ሃላፊ ናቸው። "በኔዘርላንድስ ኤምባሲ በኩል ከድርጅቱ ጋር ለመደራደር ሞክረናል። ነገር ግን አንድ ግለሰብ በመሆኑ ተቀባይነት ሳይገኝ ቀርቷል። እስካሁን ስንሰራው የቆየነው የባለቤትነት ፈቃዱ መጥፎ እንደሆነ ማሳየት ነው" ይላሉ።

የከተሜን ህይወት ቀላል ለማድረግ ጤፍን ፈጭቶ መሸጥ!

ከዚህ አንጻር ኢትዮጵያ እያደረገችው ያለውን ጥረት ከባድ የሚያደርገው ደግሞ 'ሄልዝ ኤንድ ፐርፎርማንስ ፉድ ኢንተርናሽናል' የተባለው የሆላንድ ድርጅት ከፈረሰ መቆየቱ ነው።

በወቅቱ የድርጅቱ ባለቤት ነበር የተባለው ግለሰብ ጃንስ ሩዝጀን በአሁኑ ሰዓት የሌላ ድርጅት ዋና ሃለፊ እንደሆነ ነው የሚታወቀው። ቢቢሲ ድርጅቱን ለማነጋገር ቢሞክርም ምንም አይነት አስተያየት ከመስጠት ተቆጥቧል።

የጤፍ ባለቤትነትን በተመለከተ ኢትዮጵያ መንግሥትና የእኔ ነው በሚለው ድርጅት መካከል ያለው ውዝግብ ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው እንደሆነ በርካታ ኢትዮጵያዊያን ይናገራሉ።

እውን እንጀራ ሱስ ያስይዛል?

በአንድ ምግብ ቤት ውስጥ ያናገርናቸው ኢትዮጵያዊያንም ይህንኑ ነው አስረግጠው የሚናሩት። አንደኛው አስተያየት ሰጪ "ጤፍ ኢትዮጵያ ውስጥ ብቻ እንደሚገኝ አውቃለው። ምናልባት ወደ ውጪ ተልኮ ካልሆነ ሌላ ቦታ አታገኘውም። በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኝና ህይወቴን ሙሉ ሳጣጥመው የነበር ምግብን አንድ የሆላንድ ድርጅት መጥቶ ባለቤቱ እኔ ነኝ ቢለኝ ተቀባይነት የለውም'' ብለዋል።

Image copyright Getty Images

ሌላኛው ደግሞ "ጤፍ በቅድመ አያቶቻችን ዘመንም ነበር። ከጥቂት ዓመታት በፊት የውጪ ተመራማሪዎች ጤፍ ምንም ፕሮቲን የለውም ሲሉ አስታውሳለው። አሁን ደግሞ ጥቅሙን ስላወቁ ተመልሰው አስፈላጊ ተክል ነው እያሉ ነው። የሆላንዱ ድርጅት የባለቤትነት መብቱን ማግኘቱ ትልቅ ችግር ነው። በፍጹም ልቀበለው አልችልም" ሲሉ ተናግረዋል።

እነዚህን ጨምሮ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ከመንግሥታቸው ጎን ቢቆሙ አስገራሚ አይደለም። ምንም እንኳን ጉዳዩን በተመለከተ ብዙ የተወሳሰቡ ሕጋዊ ጉዳዮች ቢኖሩም ኢትዮጵያ በቀላሉ ተስፋ ቆርጣ የምትተወው አይመስልም።