የቬንዙዌላ ፍርድ ቤት በተቃዋሚ መሪው ላይ የጉዞ እገዳ ጣለ

ጁአን ጉአኢዶ Image copyright AFP/Getty Images
አጭር የምስል መግለጫ እራሳቸውን ጊዜያዊ ፕሬዚዳንት ብለው የሰየሙት ጁአን ጉአኢዶ

የቬንዙዌላ ጠቅላይ ፍርድ ቤት የተቃዋሚ መሪ ጁአን ጉአኢዶ ከሃገር እንዳይወጡ የጉዞ እገዳ እና የባንክ ሂሳብ እንዳያንቀሳቅሱ ገደብ ጣለ።

የተቃዋሚ መሪው ጁአን ጉአኢዶ ባለፈው ሳምንት እራሳቸውን የቬንዙዌላ ተጠባባቂ ፕሬዚዳንት አድርገው መሾማቸው ይታወሳል።

የተቃዋሚ መሪው የአሜሪካ እና የካናዳ መንግሥትን ጨምሮ የበርካታ ሃገራት እውቅናን አግኝተዋል። ፕሬዚዳንት ኒኮላስ ማዱሮ ደግሞ የሩሲያ እና የቻይና ድጋፍ እንዳልተለያቸው ይናገራሉ።

አሜሪካ በዲፕሎማቶቿ እና በተቃዋሚ መሪው ጁአን ጉአኢዶ ላይ የሚደርሱ ማናቸውም አይነት ማስፈራሪያዎች ላይ ''የማያዳግም እርምጃ ያስወስዳሉ'' ስትል የቬንዙዌላ መንግሥትን አስጠንቅቃ ነበር።

አሜሪካ የቬንዙዌላ መንግሥትን አሰጠነቀቀች

ቬኔዙዌላ ምናባዊ ገንዘብ ይፋ አደረገች

ቬንዙዌላ ለረዥም ጊዜ የዘለቀ ምጣኔ ሃብታዊ ቀውስ ውስጥ የምትገኝ ሲሆን ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ ከፍተኛ ህዝባዊ ተቃውሞዎችን እያስተናገደች ትገኛለች።

እጅግ የተጋነነ የዋጋ ግሽበት፣ መድሃኒት እና ምግብን ጨምሮ የመሰረታዊ ቁሶች እጥረት በርካቶች ሃገሪቱን ለቀው እንዲሰደዱ ምክንያት እየሆኑ ነው።

ኒኮላስ ማዱሮ በቅርቡ በሃገሪቱ የተካሄደውን ምርጫ አሸንፊያለሁ በማለት ከ20 ቀናት በፊት ነበር ሁለተኛ ዙር የስልጣን ዘመናቸውን የጀመሩት። ማዱሮ አሸነፍኩ ባሉበት ምርጫ በርካታ ተቃዋሚዎች በምርጫው እንዳይሳተፉ ተደርገው ነበር።

ለፕሬዚዳንት ማዱሮ ታማኝ ነው የሚባለው የሃገሪቱ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የተቃዋሚ መሪው ጁአን ጉአኢዶ ''በሪፐሊኩ ሰላም እንዲደፈርስ በማድረጋቸው'' ቅድመ ምርመራዎች እስኪጠናቀቁ ''ሃገር ለቀው እንዳይወጡ ተከልክለዋል'' ሲል ውሳኔውን አስተላልፏል።

የተቃዋሚ መሪው በጉዳዩ ላይ ለጋዜጠኞች አስተያየታቸውን ሲሰጡ ''ይህ አዲስ አይደለም'' ያሉ ሲሆን ጨምረውም ''ስጋት አለኝ፤ ይሁን እንጂ ማድረግ ያለብንን እያደረግን ነው'' ብለዋል።

ካናዳ የቬንዝዌላን አምባሳደር አባረረች

የአሜሪካ ብሔራዊ ደህንነት አማካሪው ጆን ቦልተን ማስፈራራት የሕግ ጥሰት ነው ሲሉ የቬንዙዌላን መንግሥት አስጠንቅቀው ነበር።

በተጨማሪ ''ሁሉም አማራጮች በጠረጴዛ ላይ ናቸው'' በማለት የኃይል እርምጃ ከአማራጮቹ መካከል አንዱ እንደሆነ ጠቁመው አልፈዋል።

እራሳቸውን ጊዜያዊ ፕሬዚዳንት ብለው የሰየሙት ጁአን ለረቡዕ እና ቅዳሜ ለተቃውሞ ሰልፍ ደጋፊዎቻቸውን አደባባይ ጥርተዋል።

ስፔን፣ ጀርመን፣ ፈረንሳይ እና እንግሊዝን ጨምሮ በርካታ የአውሮፓ ሃገራት በቬንዙዌላ በስምንት ቀናት ውስጥ ምርጫ ካልተጠራ ለተቃዋሚው የፕሬዚዳንትነት እውቅና እንሰጣለን ብለዋል።

ፕሬዚዳንት ማዱሮ ግን የአውሮፓውያኑን ሃገራት ማስጠንቀቂያ አጣጥለውታል።

ተያያዥ ርዕሶች