በጂግጂጋ በተከሰተ ግጭት ሁለት ሰዎች ተገደሉ

ጂግጂጋ Image copyright BBC Somali
አጭር የምስል መግለጫ ጂግጂጋ ከተማ ሰኔ 9 2010 ዓ.ም

ትናንት በሶማሌ ክልል መዲና- ጂግጂጋ የሃይማኖት ክብረ በዓልን ተከትሎ በተፈጠረ ግጭት ሁለት ሰዎች መገደላቸው ተነገረ።

የከተማዋ ነዋሪዎች የኦርቶዶክስ ዕምነት ተከታይ የሆኑ የጂግጂጋ ከተማ ነዋሪዎች የአስተርዮ ማርያም ክብረ በዓልን ከጂግጂጋ ከተማ 35 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በምትገኘው ጉርሱም ወረዳ አክብረው ወደ ከተማው ሲመለሱ በተደራጁ ወጣቶች በድንጋይ መደብደባቸውን ነግረውናል።

በስፍራው የሚገኘው የቢቢሲ ሶማልኛ ጋዜጠኛም ሁለት ሰዎች መገደላቸውን እና አራት ሰዎች ደግሞ ለጉዳት መዳረጋቸውን ዘግቧል።

የበዓሉ ተሳታፊ የነበሩ አንድ የሃይማኖት አባት "ከቤተክርስቲያን መልስ ከተማው መግቢያ ላይ የተደራጁ ወጣቶች ድንጋይ በመወርወር ሰዎች ፈነከቱ፤ መኪኖችንም ሰባበሩ" ብለዋል።

የሃይማኖት አባቱ እንደሚሉት በጥይት ተመትተው የሞቱት ሁለቱ ሰዎች የኦርቶዶክስ ዕምነት ተከታዮች ናቸው፤ ግጭቱን ለመበተን ከመጡ የጸጥታ አስከባሪዎች ጋር በተከሰተ ግጭት ሁለቱ ሰዎች መገደላቸውንም አስረድተዋል።

በሶማሌ ክልል ከ10 የሚበልጡ አብያተ ክርስትያናት ጥቃት ደረሰባቸው

ሌላው ያነጋገርናቸው የጂግጂጋ ዩኒቨርሲቲ መምህር ትናንት ከአዲስ አበባ ወደ ጂግጂጋ እየተመለሱ እንደነበረ በማስታወስ ትናንት አመሻሽ ላይ ሐረር ከተማ ሲደርሱ ወደ ጂግጂጋ ከተማ ዘልቀው መግባት እንደማይችሉ ከተነገራቸው በኋላ ሐረር ከተማ ለማደር መገደዳቸውን ይናገራሉ።

የዩኒቨርሲቲ መምህሩ እንደሚሉት ዛሬ ጠዋት ወደ ጂግጂጋ እንደተመለሱ እና ከተማዋ ላይ የተለመደው ዓይነት እንቅስቃሴ እንደሌለ ይናገራሉ።

የሃይማኖት አባቱ በበኩላቸው በከፊል መንገዶች ዝግ እንደሆኑ እና የመኪና እና የንግድ እንቅስቃሴ በከተማዋ አይታይም ብለዋል።

የግጭቱ መንስኤ እና ጥቃቱ እንዴት እንደተፈጸም እንዲያስረዱን በስልክ የጠየቅናቸው የኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊው አብዱላሂ ሞሃመድ መውሊድ ''ጉዳዩን እያጣራን ስለሆነ አሁን አስተያየት መስጠት አልችልም'' የሚል ምላሽ ሰጥተውናል።

ከዚህ ቀደም በጂግጂጋ ተከስቶ ለነበረው ሃይማኖት ተኮር ግጭት መንግሥት 'ሄጎ' ተብሎ የሚጠራውን ቡድን ተጠያቂ አድርጎ ነበር።

ሐምሌ 27፣ 2010 ዓ. ም. ጂግጂጋን ጨምሮ በክልሉ የተለያዩ ከተሞች 96 ሰዎች መሞታቸውን እና ለግድያውም 'ሄጎ' የተባለው ቡድን ተጠያቂ እንደሆነ በወቅቱ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጄኔራል የነበሩት ዘይኑ ጀማል ለቢቢሲ ገልጸው ነበር።

የቀድሞ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነር ሄጎ የሚባለውን ቡድን የፈጠሩትና እቅዱን ያቀነባበሩት የቀድሞ የክልሉ ከፍተኛ የመንግሥት ባለስልጣናት ናቸው ብለው ነበር።

በ96 ሰዎች ግድያ የ'ሄጎ' ቡድን አባላት እጅ አለበት፡ ፖሊስ

በተመሳሳይ መልኩ ከቀናት በፊት በምስራቃዊቷ ከተማ ድሬዳዋ የእግዜርአብ ታቦት ገብቶ ሲመለስ የተፈጠረ ግጭት ለቀናት መዝለቁ ይታወሳል።

በወቅቱ ደውለን ያነጋገርናቸው የድሬዳዋ ነዋሪዎች እንደነገሩን ከሆነ አርብ ዕለት ከማለዳ ጀምሮ ወጣቶች ሰልፍ ሲያካሄዱ፣ የተቃሞው ድምጾችን ሲያሰሙ፣ አልፎ አልፎም ድንጋይ ሲወራወሩ ነበር ብለውናል።

ሠላም የራቃት ድሬዳዋ

የወጣቶች ጥያቄ እየሰፋ መጥቶ የሥራ አጥነት፣ የመልካም አስተዳደር፣ የፍትህና የእኩልነት ጥያቄዎች ጎልተው መውጣት ጀምረዋል። በተለይም የድሬዳዋን ፍቅር አታደፍርሱ፣ በብሔር አትከፋፍሉን፣ «40/40/20» የተሰኘው የአስተዳደር ቀመር ይውደም፣ የሚሉ ተቃውሞዎች ሲሰሙ ነበር።

ተያያዥ ርዕሶች

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ