የኢትዮጵያ አየር ኃይል ሶማሊያ ውስጥ በአል-ሻባብ ይዞታ ላይ ጥቃት ፈፀምኩ አለ

አየር ኃይል Image copyright Tech. Sgt. Cecilio M. Ricardo Jr

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ሶማሊያ ውስጥ ባለው ጽንፈኛ እስላማዊ ቡድን አል-ሻባብ ይዞታ ላይ ባካሄደው የአየር ድብደባ ከባድ ጉዳት እንዳደረሰ አስታወቀ።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ላይ ጥቃቱን የፈጸመው ባለፈው ሳምንት ከባይደዋ ከተማ በስተምሥራቅ 75 ኪሎ ሜትሮች እርቆ በሚገኘውና ቡርሃይቤ በተባለ የአል-ሻባብ ይዞታ ላይ እንደሆነም አመልክቷል።

ሐሙስ ዕለት ጥር 16 ቀን 2011 ዓ.ም አየር ኃይሉ ፈጸምኩ ባለው የአየር ጥቃት በጽንፈኛ እስላማዊ ቡድኑ ላይ ከባድ ጉዳት ማድረሱን ገልጾ፤ በተዋጊ ሄሊኮፕተሮች በተፈፀመው በዚህ ጥቃት 35 የአልሻባብ ታጣቂዎች ተገድለዋል ብሏል።

ለናይሮቢው የሽብር ጥቃት አልሸባብ ኃላፊነቱን ወሰደ

የኢትዮጵያ አየር ኃይል አልሸባብ ላይ ጥቃት ፈጸመ

ከተገደሉት የአል-ሻባብ አባላት መካከልም የቡድኑ የዘመቻ ኃላፊና በፈንጂ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን የሚያቀናብረው ቡድን መሪ እንደሚገኙበት መረጋገጡን መግለጫው አመልክቷል።

አየር ኃይሉ በአልሻባብ ላይ አካሄድኩት ባለው በዚህ ድብደባ አራት የሚደርሱ ተሽከርካሪዎችና አምስት ከባድ መትረየሶችን ማውደሙን ጨምሮ ገልጿል።

ይህንን ጥቃት በተመለከተ ማረጋገጫ ለማግኘት የሶማሊያ መንግሥት ባለስልጣናትን ለማናገር ያደረግነው ሙከራ ያልተሳካ ሲሆን አልሻባብም ስለጥቃቱ ምንም ያለው ነገር የለም።

ይህ ጥቃት አልሻባብ ሶማሊያ ውስጥ በሚገኙ የኢትዮጵያ ወታደሮች ላይ ለፈጸመው የደፈጣ ጥቃት አጸፋ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል።

የኢትዮጵያ አየር ኃይል ከዚህ ቀደም በተለያዩ ጊዜያትና ቦታዎች የአልሻባብ ይዞታዎችና ታጣቂዎች ላይ ጥቃት እንደፈጸመ ሲዘገብ ቆይቷል።

ተያያዥ ርዕሶች