ኬንያ ውስጥ ጉዳት የደረሰበት ታካሚ 440 ሺህ ዶላር ካሳ ተወሰነለት

ታካሚ Image copyright Getty Images

በየቀዶ ህክምና ወቅት በተፈጸመ ቸልተኝነት ምክንያት የአንጎል ጉዳት ያጋጠመው ኬንያዊ ህመምተኛ ካሳ እንዲከፈለው በከፍተኛው ፍርድ ቤት ተወሰነለት።

በኬንያ መዲና ናይሮቢ ውስጥ በሚገኝ ሆስፒታል ከ14 ዓመት በፊት በተደረገለት ቀዶ ህክምና ጉዳት የደረሰበት ግለሰብ 440 ሺህ የአሜሪካ ዶላር ካሳ እንዲከፈለው ነው የተወሰነለት።

ፍርድ ቤቱ በሰጠው ውሳኔ ደረጃውን ባልጠበቀው የቀዶ ህክምና ምክንያት ግለሰቡ በአንጎሉ ላይ ጉዳት ስለደረሰበት ለሰውነት ክፍሎቹ የሚደርሰው ኦክስጂን ላይ እክል አጋጥሞታል ብሏል።

ቀዶ ህክምና በአፍሪካ ስጋት መሆኑ ከፍ ብሏል

በርካቶች ከምጥ ይልቅ በቀዶ ህክምና መውለድን እየመረጡ ነው

ለዚህም ምክንያቱ ለታካሚው ማደንዘዣ የሰጡት የናይሮቢ ሆስፒታል ሃኪሞች ቸልተኝነት እንደሆነ 'ዘ ስታር' ጋዜጣ በዘገባው አመልክቷል።

በአንጎሉ ላይ የደረሰው ጉዳት የግለሰቡን የአእምሮ ብቃት በከፍተኛ ደረጃ ዝቅ በማድረግ የስድስት ዓመት ታዳጊ ያለበት ደረጃ ላይ ስላደረሰው፤ ክሱን የመሰረቱት ጉዳቱ የገጠመው ታካሚ ቤተሰቦች መሆናቸውን 'ሲቲዝን' የተሰኘው የቴሌቪዥን ጣቢያ ዘግቧል።

በጉዳዩ ላይ ብይን የሰጡት የከፍተኛው ፍርድ ቤት ዳኛ ጆርጅ ኦዱንጋ ጨምረውም ለግለሰቡ ቤተሰቦች 100 ሺህ ዶላር እንዲያገኙ ወስነዋል።

ፍርድ ቤቱ የወሰነውን የካሳ ገንዘብ የናይሮቢ ሆስፒታልና ማደንዘዣውን የሰጠው ሃኪም ለተጎጂው ግለሰብና ቤተሰቡ እንዲከፍል ወስኗል።