ቮልስ ዋገን በኢትዮጵያ የመኪና ዋጋን ይቀንስ ይሆን?

የቮልስ ዋገን መለያ Image copyright Getty Images

የጀርመኑ መኪና አምራች ኩባንያ ቮልስ ዋገን በኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ መስኮች ለመስራት የሚያስችለውን የአዋጪነት ጥናት ለማከናወን የሚያስችለውን የመግባቢያ ስምምነት የጀርመን ፕሬዝዳንት በተገኙበት ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጋር ተፈራርሟል።

የኩባንያው የአዋጪነት ጥናት የሚያተኩረውም በኢትዮጵያ የመኪና መገጣጠሚያ ፋብሪካ የማቋቋም፣ ለኢትዮጵያ ተስማሚ የሆኑ መለዋወጫዎችን የማቅረብ፣ የስልጠና ማዕከል የመክፈትና ከመኪኖች ጋር የተያያዙ አዳዲስ የቴክኖሎጂ መገልገያዎችን የሚያስተዋውቅ ዓላማን የያዘ መሆኑን በስምምነቱ ተገልጿል።

ሃዩንዳይ የሚራመድ መኪና አምርቷል

ቮልስ ዋገን በዓለም ላይ ካሉ በቀዳሚነት ተጠቃሽ የመኪና አምራች ኩባንያዎች መካከል የሚገኝ ሲሆን በአፍሪካ ውስጥም ከ65 ዓመታት በፊት ጀምሮ ደቡብ አፍሪካ ውስጥ መኪናዎችን እያመረተ ይገኛል።

ከዚህ በተጨማሪም ድርጅቱ በአልጄሪያ፣ በሩዋንዳና በኬንያ ውስጥ በኢትዮጵያ ሊከፍት ያሰበው ዓይነት የመኪኖች መገጣጠሚያ ፋብሪካ ያለው ሲሆን በምዕራብ አፍሪካ በሚገኙት በጋናና በናይጄሪያም ለመክፈት ዕቅድ አለው።

በኢትዮጵያ ከቮልስ ዋገን ቀደም ሌሎች መኪና አምራቾች የመኪና መገጣጠሚያ ተቋማትን ከፍተው ሥራ የጀመሩ ቢሆንም በመኪኖች ገበያ ላይ ግን ያን ያህል ለውጥን እንዳላመጡ በዘርፉ የተሰማሩ ነጋዴዎች ይናገራሉ።

በተለይ ከመካከለኛው ምሥራቅ አረብ ሃገራት ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡት ጥቅም ላይ የዋሉ ተሽከርካሪዎች በሃገር ውስጥ ከተገጣጠሙት ይልቅ በስፋት ገበያው ላይ ስለሚገኙ ውድድሩን ከባድ እንዳደረጉባቸውና በዚህም ሳቢያ መገጣጠሚያዎቹ ባላቸው አቅም ማምረት ሳይችሉ እንደቀሩ ይነገራል።

ከጥቂት ዓመታት በፊት ዴሎይት በተሰኘ ተቋም በኩል የወጣ መረጃ እንደሚያመለክተው በኢትዮጵያ ሁለት መኪኖች ለአንድ ሺህ ሰዎች የሚደርስ ሲሆን ይህም ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ዝቅተኛ የመኪና ባለቤትነት ካለባቸው ሃገራት መካከል አንዷ አድርጓታል።

ለዚህ ደግሞ ዋነኛው ምክንያት ሃገሪቱ በመኪኖች ላይ የጣለችው ቀረጥ እንደሆነ አዲስ አበባ ውስጥ መኪኖችን ከውጪ በማስመጣትና በመሸጥ ሥራ ላይ የተሰማሩት አቶ ሔኖክ ደምሰው ይናገራሉ።

ቶዮታ ያለአሽከርካሪ የሚንቀሳቀሱ መኪናዎችን ሊያሰማራ ነው

አቶ ሄኖክ የቮልስ ዋገን መገጣጠሚያ በኢትዮጵያ መከፈቱ መልካም አጋጣሚ መሆኑን ቢናገሩም አሁንም በድጋሚ "ለመኪኖች ዋጋ መናር ሃገሪቱ የጣለችው ቀረጥ ዋነኛ ምክንያት በመሆኑ፤ አሁንም ቮልስ ዋገን በአገር ውስጥ የሚኖረውን ዋጋ ካላስተካከለ በስተቀር በዋጋ ላይ ለውጥ ይኖራል ብዬ አላስብም" ሲሉ ደጋግመው የቀረጥን ጉዳይ ያነሱታል።

እንደ እርሳቸው ልምድ ከሆነ የቮልስ ዋገን ምርቶች ወደ አገር ውስጥ በብዛት ይገባሉ፤ ነገር ግን የመለዋወጫ እጥረት ስለሚያጋጥማቸው ብዙዎች ሲማረሩም ሰምተዋል። አሁን ግን ካምፓኒው ፋብሪካውን ለመክፈት መስማማቱ እነዚህን ችግሮች ለማስወገድ እንደሚረዳ ያስረዳሉ።

ቢሆንም ግን በመኪና ዋጋ ላይ ግን ለውጥ ያመጣል የሚል እምነት እንደሌላቸው ይናገራሉ -ትልቁ ችግር ቀረጥ መሆኑን በማንሳት።

"በመኪኖች ላይ የሚጣለው ቀረጥ ከፍተኛ በመሆኑ በዋጋው ላይ ከፍተኛ ጭማሪን ያስከትላል ስለዚህም ሰዎች መኪና ለመግዛት ብዙም አይበረታቱም" ይላሉ።

የውጪ ኩባንያዎች በሎጂስቲክስ ዘርፍ እንዲሰማሩ ተፈቀደ

በኢትዮጵያ ውስጥ ለንግድና ለግል ግልጋሎት ተብለው ወደሃገር ውስጥ የሚገቡ ተሽከርካሪዎችን በተመለከተ አምስት አይነት የተለያዩ የቀረጥ ሁኔታዎች አሉ።

በግል መኪኖች በኩል ተሽከርካሪዎቹ ባላቸው የሞተር ጉልበት አኳያ ከፍተኛ የሆኑት ከ60-100 በመቶ ቀረጥ እንዲከፍሉ እንደሚደረግ ከጉምሩክ ባለሙያዎች የተገኘው መረጃ ያመለክታል።

ወደ ሃገር ውስጥ የሚገቡትን መኪኖች በተመለከተ የሚያስፈልገው ቀረጥ በሙሉ ከተከፈለ በኋላ ለመኪናው የወጣው ወጪ ሲሰላ ከተመረተበት ዋጋ ከሦስት እጥፍ በላይ አድጎ ይገኛል።

ይህም በመኪና ገዢዎች ላይ ከፍ ያለጫና ስለሚፈጥር መኪኖችን ለመግዛት ፍላጎት ያላቸው ኢትዮጵያዊያን ላይ ጫናን በመፍጠር ምኞታቸውን የማይደረስበት ህልም ያደርግባቸዋል።

የዓለምን ትራንስፖርት የቀየረው ዲዚል ሞተር

ምንም እንኳን የመኪኖች ዋጋ ከፍተኛ ቢሆንም በተለይ በአዲስ አበባ ውስጥ ከዕለት ዕለት እየጨመረ የሚመጣው የተሽከርካሪዎች ቁጥር በህዝቡ የመኪና ባለቤት የመሆን ፍላጎትን ያሳያል።

በግል ንግድ ላይ ተሰማርታ የምትገኘው ወ/ት ከዲጃ ሃሰን ሥራዋንና እንቅስቃሴዋን ለማቀላጠፍ የሚረዳትን መኪና ለመግዛት ማሰብ ከጀመረች አራት ዓመታት ያህል የተቆጠሩ ቢሆንም የዋጋው ውድነቱ ዕቅዷን ሳታሳካ እንድትቆይ እንዳስገደዳት ትናገራለች።

አዲስ አበባ ውስጥ የታክሲና የሕዝብ ትራንስፖርትን በመጠቀም ካሰቡበት ቦታ በተፈለገው ሰዓት መድረስ አስቸጋሪ እየሆነ መምጣቱን የምትናገረው ከዲጃ የመኪና መኖር በአገር ውስጥ ያለውን የንግድ እንቅስቃሴ ያቀላጥፋል፤ ወጪንም ይቀንሳል ትላለች።

"መደበኛ ታክሲ ለመያዝ ያለው ወረፋ ጊዜን የሚገድል ሲሆን የኮንትራት ታክሲን መጠቀም ደግሞ ዋጋው አይቀመስም፤ የግል መኪና ካለ ግን ሥራን ለማቀላጠፍ በጣም ይጠቅማል" ስትል መኪና ቅንጦት እንዳልሆነ ትናገራለች።

ቢሆንም ግን የመኪና ዋጋ ውድ መሆን ከዲጃን ብቻ ሳይሆን በርካቶችን መኪና ስለመግዛት ከማሰብ እንዲቆጠቡ አድርጓቸዋል። እርግጠኛ ባትሆንም "ቮልስ ዋገንን የመሰሉ መኪና አምራቾች በሃገር ውስጥ መኪና መስራት ከጀመሩ በገበያው ዋጋ ላይ ቅናሽ ሊኖር ይችላል ብዬ አስባለሁ" ትላለች።

ኢትዮጵያ ውስጥ የጠፉት ጀርመናዊ ፕሮፌሰር ዱካ አልተገኘም

አቶ መኮንን ኃይሉ የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር የቮልስ ዋገን በኢትዮጵያ የመኪና መገጣጠሚያውን መከፈቱ በኢትዮጵያ ውስጥ ምርቱን ከማቅረብ ባሻገር ለምስራቅ አፍሪካ ሃገራት እንዲተርፍ በማድረግ በኢኮኖሚ ላይ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ማምጣት ያስችላል ይላሉ።

ከዚህም በተጨማሪ ለበርካቶች እንጀራ መብያ እንደሚሆን እንዲሁም ለዘመናዊ የቴክኖሎጂ ሽግግር የአገር ውስጥ ባለሃብቶችም የራሳቸውን ኢንቨስትመንት እንዲያካሂዱ እድል ይፈጥራልም ብለዋል ዳይሬክተሩ።

በሌላም በኩል ስምምነቱ ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት ምቹ የሆነች አገር እንደሆነ ያመላክታል ያሉት ዳይሬክተሩ ሌሎች አለም አቀፍ ካምፓኒዎችን ለመሳብም የራሱ ድርሻ ይኖረዋል ብለዋል።

"የቮልስዋገን ምርት የሆኑ መኪኖች በብዛት ወደ አገር ውስጥ ይገባሉ፤ ፋብሪካው በኢትዮጵያ ለመክፍት ስምምነት ላይ መደረሱ የውጭ ምንዛሬ እጥረትም ይቀንሳል" ሲሉ ለቢቢሲ ገልፀዋል።

ከዚህ ቀደም በአገር ውስጥ ምርታቸውን መገጣጠም የጀመሩት እንደ ቶዮታና ሊፋን ሞተርስ ያሉ ካምፓኒዎች በኢትዮጵያ ረዘም ያለ ጊዜ የቆዩ ሲሆን በዘርፉ አዋጭ በሆነ መልኩ እየሰሩ እንደሆነና የዜጎችን ፍላጎትም እያሟሉ እንደሆነ ጠቁመዋል።

የመግባቢያ ስምምነቱ ላይ ሥራው በተቻለ ፍጥነት በቶሎ እንደሚጀመር ከማሳወቁ ውጪ የት የሚሉና ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮች ለጊዜው አለመነሳታቸውን ጠቅሰው ካምፓኒው ያመቸኛል በሚለው ሥፍራ ሊገነባ ይችላል ብለዋል።

በዚህ ዘገባ ላይ ተጨማሪ መረጃ