ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያዎቹ ምንጫቸው ከወዴት ነው?

በቅርቡ በአዲስ አበባ ከተማ በቁጥጥር ሥር ዋለ የተባሉ የጦር መሳሪያዎች Image copyright Addis Ababa Police
አጭር የምስል መግለጫ በቅርቡ በአዲስ አበባ ከተማ በቁጥጥር ሥር ዋለ የተባሉ የጦር መሳሪያዎች

ሽጉጥ፣ ጥይት፣ መትረየስ፣ ቦምብ. . . በቦቴ፣ በአይሱዙ ሲዘዋወሩ ተያዙ የሚሉ ወሬዎችን ጆሯችን የተላመደው ይመስላል። የጦር መሳሪያዎች መሃል ሃገር የሚገኙ ከተሞችን ጨምሮ በተለያዩ ቦታዎች በተደጋጋሚ የመያዛቸው ነገር ደግሞ በርካቶችን እያሳሰበ ያለ ጉዳይ ሆኗል።

በቅርቡ እየተስፋፋ ለመጣው የሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር ተጠያቂው ማነው? ተብለው የተጠየቁት የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጀነራል እንደሻው ጣሰው፤ "የሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውሩ የሚከናወነው ለውጡን በማይደግፉ አካላት ነው" ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ኮሚሽነር እንደሻው ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውሩ አሁን ያለበትን ደረጃ ሲያስረዱ ''በአንዳንድ የሃገሪቱ ስፍራዎች የጦር መሳሪያ ዝውውሩ እንደጨመረ እና በሌሎች አካባቢዎች ደግሞ በተደረገው ቁጥጥር የዝውውር መጠኑ ቀንሷል" ይላሉ።

ሕገወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር መበራከት ምንን ያመለክታል?

በተደጋጋሚ እየተከሰተ ያለው ሕገ-ወጥ መሳሪያ ዝውውር ምንጩ አንድ ብቻ ሳይሆን በርከት ያለ እንደሆነ ይታመናል። በመንግሥት እጅ የነበሩ ጦር መሳሪያዎችም በዚህ ውስጥ እንደሚገኙ ኮሚሽነሩ ያመለክታሉ ''ሕገ-ወጥ መሳሪያዎች ከውጪ ብቻ አይደለም የሚመጡት። ሃገሪቱ ውስጥ ካሉ የመሳሪያ ግምጃ ቤቶች ውስጥ በተለያዩ ኃይሎች ተዘርፈው የተወሰዱም ይገኙበታል።''

እንደ ኮሚሽነሩ ከሆነ፤ ከሃገር ውስጥ ከተዘረፉ መሳሪያዎች ውጪ ከደቡብ ሱዳን፣ ከጅቡቲ እና ከሶማሊያ ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ሕገ-ወጥ መሳሪያዎችም መጠናቸው ቀላል የሚባል አይደለም።

በምዕራብ ኦሮሚያ የኦነግ ጦር አዛዥ ስለወቅታዊው ሁኔታ ምን ይላል?

የሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን ለመግታት ከህብረተሰቡ ጋር በተቀናጀ መልኩ ጥረት እየተደረገ እንደሆነ የሚናገሩት ኮሚሽነር እንደሻው ጣሰው፤ ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ ወደ ስልጣን መምጣትን ተከትሎ የጦር መሳሪያ ዝውውር መጨመሩን ያምናሉ።

ኮሚሽነሩ ለዚህ እንደ ማሳያ የሚያቀርቡት ''ከለውጡ በፊት የነብስ ወከፍ የጦር መሳሪያ ዝውውር እንደነበረ መረጃዎች ያሳያሉ። አሁን ግን ከነብስ ወከፍ መሳሪያዎች አለፍ ብሎ መትረየስና ቦምብን የመሳሰሉ የቡድን ጦር መሳሪያዎች በሕገ-ወጥ ዝውውር ውስጥ እየታዩ ነው'' ይላሉ።

በዚህ የጦር መሳሪያ ዝውውር ውስጥ በሽብር ተግባር ላይ እንደተሰማራው አል-ሻባብን አይነት የውጪ ቡድኖች ከተሞች ውስጥ ጉዳት ለማድረስ ባላቸው ፍላጎት የተነሳ እጃቸው ሊኖር ይችላል የሚሉት የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽነሩ ከዚህ በተጨማሪ "በጦር መሳሪያ ንግድ መክበር የሚፈልጉ ግለሰቦችም ለጦር መሳሪያ ዝውውሩ መጨመር ተጠያቂ ናቸው" ይላሉ።

ወደ ካናዳ መሄድ አስበዋል? ከአጭበርባሪዎች ይጠንቀቁ

በተለያዩ ቦታዎች የሚያጋጥሙት አለመረጋጋቶች ዜጎች ደህንነት እንዳይሰማ እያደረገ ሲሆን፤ ይህም የጦር መሳሪያ ፍላጎት እንዲጨምር እንዳደረገ ይታመናል። "በዜጎች ላይ እና በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች ላይ ጉዳት ለማድረስ ፍላጎት በመኖሩ የጦር መሳሪያ ፍላጎት መጨመሩን" ኮሚሽነር እንደሻው ይናገራሉ።

የፀጥታ ጉዳዮች ተንተኝ የሆኑት አቶ ዳደ ደስታ ደግሞ በሃገሪቱ ውስጥ የሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር የተበራከተው በኢትዮጵያ ያለውን የፖለቲካ እና የመዋቅር ለውጥ ተከትሎ የወንጀል መከላከል መዋቅሮች በመዳከማቸው እንደሆነ ይጠቁማሉ።

ሳዑዲ የፀረ-ሙስና ዘመቻዬን አጠናቀቅኩ አለች

አቶ ዳደ ከዚህ በተጨማሪ በአንዳንድ ክልሎች የሚሰራጩ መረጃዎች ለሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውር መበራከት ምክንያት ሆነዋል ይላሉ። ለዚህም እንደምሳሌ የሚያስቀምጡት መሳሪያ ማስመዝገብ ይቻላል ተብሎ በስፋት መወራቱ ሰዎች የጦር መሳሪያ እንዲገዙ እንዳበረታታ ያምናሉ።

''በተጨማሪም አሁን ካለንበት ተጨባጭ ሁኔታ በመነሳት በግለሰቦች ዘንድ ስጋት አለ። በዚህም የጦር መሳሪያ የመታጠቅ እሽቅድድም አለ። የጦር መሳሪያ መታጠቅ ፍላጎት የሌለው ሰው እንኳ ቢሆን በዙሪያው ያለ ሰው መሳሪያ ይዞ ሲያይ እሱም መሳሪያ ለመያዝ ይፈልጋል'' ሲሉ ያስረዳሉ።

በሃገሪቱ ውስጥ በስፋት የሚዘዋወሩት የጦር መሳሪያዎች ምንጭን በተመለከተ የፀጥታ ጉዳዮች ተንታኙ አቶ ዳደ፤ ''የጦር መሳሪያ ከየት መጣ ብለን መጠየቅ አንችልም። ምክንያቱም የምንገኝበት ቀጠና ለረዥም ዓመታት ከፍተኛ የሆነ የእርስ በስርስ እና ደንበር ዘለል ጦርነቶች ሲካሄድበት የነበረ ቀጠና ነው'' በማለት በርካታ ምንጮች እንዳሉ አመልክተዋል።

በየእለቱ ከሚወጡት ዘገባዎች አንጻር ከአራቱም የሃገሪቱ አቅጣጫዎች ሕገ-ወጥ የጦር መሳሪያ እንቅስቃሴ እንዳለ አመልካቾች ናቸው። በፀጥታ ኃይሎች የተያዙት የጦር መሳሪያዎች መጠን ከፍተኛ ቢሆንም፤ ሳይያዙ ወደ ተለያዩ ሰዎች እጅ የገቡት ቁጥር ምን ሊያስከትሉ እንደሚችሉ አለመታወቁ በርካቶችን ስጋት ላይ ጥሏል።

ተያያዥ ርዕሶች