የሱዳኑ ፕሬዝዳንት አልበሽር በማህበራዊ ሚዲያ የተቀሰቀሰባቸውን ተቃውሞ ተቹ

ኦማር አልበሽር Image copyright REUTERS

የሱዳኑ ፕሬዝዳንት ኦማር አልባሽር ማህበራዊ የመገናኛ መድረኮችን በመጠቀም በመንግሥታቸው ላይ እየተካሄደ ያለውን ተቃውሞ በቀሰቀሱት ተቃዋሚዎቻቸው ላይ ተሳለቁ።

"መንግሥትን ወይም ፕሬዝዳንቱን በምርጫ ብቻ ካልሆነ በዋትስአፕ እና በፌስቡክ መፈታተን አይቻልም" በማለት ለደጋፊዎቻቸው ተናግረዋል።

ፕሬዝዳንቱ ይህንን የተናገሩት እንደ አዲስ የተቀሰቀሱ የተቃውሞ ሰልፎች በዋና ከተማዋ ካርቱም ከተካሄዱ በኋላ ነው።

ወደ ካናዳ መሄድ አስበዋል? ከአጭበርባሪዎች ይጠንቀቁ

ሱዳን ውስጥ የዳቦና የነዳጅ ዋጋ ንሮብናል ያሉ ዜጎች ከፖሊስ ጋር ተጋጩ

ሰልፎቹ የተጀመሩት ህዳር ላይ መንግሥት በዳቦ ላይ የሚያደርገው ድጎማ ማንሳቱመን በመቃወም ሲሆን ኋላ ላይ ቁጣው ወደ ፕሬዝዳንቱ ዞሯል።

ፕሬዝዳንት አልባሽር በምሥራቃዊ ሱዳን በምትገኘው ከሰላ ከተማ በደጋፊዎቻቸው በተካሄደ ሰልፍን ላይ ነበር በተቃዋሚዎቻቸው ላይ የተሳለቁበትን ንግግር ያደረጉት።

በንግግራቸው ተቃዋሚዎች የመንግሥት ለውጥ ማምጣት የሚችሉት በምርጫ ብቻ ነው ብለዋል። "ይህ በሱዳን ሕዝብ ፊት የምንገባው የማይለወጥ ቃላችን ነው። ውሳኔው የብዙሃኑ የሱዳን ሕዝብ መብት ነው" ሲሉ ተናግረዋል።

በተቃውሞው ወቅት የሱዳን መንግሥት ባለስልጣናት የማህበራዊ መገናኛ ብዙሃን መድረኮችን ለመዝጋት ሞክረው ነበር። ነገር ግን ሱዳናዊያን ያሉበትን ስፍራ የሚደብቅ ዘዴን በመጠቀም የመንግሥትን እገዳ በማለፍ ሲጠቀሙ ቆይተዋል።

በተጨማሪም ፕሬዝዳንቱ ከኤርትራ ጋር በምትዋሰነው የከሰላ ከተማ ባደረጉት ንግግር ለአንድ ዓመት ገደማ ተዘግቶ የነበረው ድንበርም እንደሚከፈት ተናግረዋል።

የቮልስ ዋገን መምጣት የመኪና ዋጋን ይቀንስ ይሆን?

ሱዳን በምሥራቅ በኩል ያለውን ድንበሯን የዘጋችው ሕገ ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን ለመግታት በሁለት ግዛቶቿ ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅን ስትደነግግ ነበር።

የተቃውሞ ሰልፎቹ መካሄድ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ 30 ሰዎች እንደተገደሉ የሱዳን መንግሥት ቢናገርም፤ የሰብአዊ መብት ቡድኖች ግን የሟቾቹን ቁጥር ከ40 በላይ ያደርሱታል።